የእለት ዜና

ኦነግ ሸኔ ንፁኃንን ጨፍጭፎ መግደል ብቻ ሳይሆን ከ60 በላይ መኖሪያ ቤቶችን ማቃጠሉ ተገለጸ

Views: 764

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጎጎላ ቃንቃ ቀበሌ ነዋሪዎች በኦነግ ሸኔ እንደተጨፈጨፉ እና የሕወሓት ድጋፍ እንዳለው ተገልጾ በጥቃቱ ከንፁኃን ዕልቂት በተጨማሪ ከ60 በላይ የአርሶ አደሮች መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዳረጋገጠ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ለመገናኛ ብዙኃን ግድያው በሕወሓት ድጋፍ በኦነግ ሸኔ መፈጸሙ ተረጋግጧል ብለዋል። ኦነግ ሸኔ እሑድ ጥቅምት 22 /2013 ባደረሰው ጥቃት 34 ንፁኃንን ሲገድል 11 ነዋሪዎች ደግሞ የት እንደደረሱ አለመታወቁን አስረድተዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የድርጊቱ ፈጻሚዎች መረዳት እንደተቻለው የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበር እና የተዘጉትን ‹‹ድምፀ ወያኔ›› እና ‹‹ኦኤምኤን›› ሚዲያዎችን በመጠቀም የጥቃት ቅስቀሳ ያደርጉ እንደነበር መግለጻቸውን ኮሚሽነር ጄኔራሉ አስታውቀዋል ቡድኑን ከሥሩ ለማፅዳት ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው አካባቢውን ለማረጋጋትም እየተሠራ መሆኑን አክለዋል።

በምዕራብ ወለጋ በንፁኃን ላይ የተፈጸመው ማንነት ላይ ያነጣጠረ ድርጊት በርካታ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል ከመንግሥት የሚጠበቀው የሐዘን መግለጫ ማውጣት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድና የመኖር ዋስትናን ማረጋገጥ መሆኑንም ተናግረዋል። ከጥቃቱ የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸው በመቃጠሉ በሜዳ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው መንግሥት አስፈላጊውን ዕርዳታ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com