የእለት ዜና

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጸደቀ

Views: 296

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር በትግራይ ክልል ተፈፃሚ ይሆናል ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባሳለፍነው ሀሙስ ጥቅምት 26/2013 በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አደራሽ አካሂዷል።

በመደበኛ ስብሰባውም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመቀበልና ለማጽደቅ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጣ ሰባት አባላት ያሉት ግብረኃይል ተቋቁሟል።

ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆንና ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረኃይል’’ ተብሎ እንደሚጠራም ተገልጿል።
በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ እንደሚደረግ የተገለፀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ እንደአስፈላጊነቱ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸው ተጨማሪ አካባቢዎችን ግብረኃይሉ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪመም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ በየጊዜው ለኅብረተሰቡ የሚሰጥ መሆኑንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com