ከብልጽግና ውልደት እስከ ጦር መማዘዝ

Views: 273

ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በህይወት እያሉ የያኔው የኢትዮጲያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር አህአዴግ ጥናቱን አጠናቆ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት ተሰማማተው ነበር።ነገር ግን በውል ባልታወቀ ምክንያት ሳይሳካ ለሰባት ዓመታት ዘገየ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ውህድ ፓርቲ የመመስረት እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ።ኢህአዴግን ከመሰረቱት እና የአድራጊ ፈጣሪ ሚናን ከፊት ሆኖ ለ27 ዓመታት ሲዘውር የቆየው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ሕውሃት) ብልጽግና የተባለውን ውህድ ፓርቲ ሳይቀላቀል ቀረ።ከውሕድ ፓርቲነት እራሱን ያገለለው ሕውሃት ተቃዋሚ በመሆን ጉዞውን ጀመረ።ይህ ምናልባትም በውህድ ፓርቲው ብልጽግን እና በተቃዋሚው ሕውሃት መካካል ትልቅ ልዩነት የፈጠረ ክስተት እንደሆነ ይታመናል።

ከምንም በላይ ግን በኮረና ወረርሽን ሳቢያ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መራዘሙ እና በትግራይ ክልላዊ ምርጫ መደረጉ ልዩነቱን ወደ ጡዘት ጎዳና አድርሶቶታል።
ሕገ ወጥ በተባለው ምርጫ ላይ መስከረም 25/2013 የፌደራል መንግስት ሕጋዊ የስልጣን ዕድሜ አልቋል በሚል ሰበብ የትግራይ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት የሚመጣን ማንኛውንም ትእዛዝ አንቀበልም ሲሉ የፌደራሉ መንግስት በበኩሉ በትግራይ ህጋዊ ያልሆነ መንግስት ስለሆነ ያለው የክልሉን በጀት በወረዳዎች በኩል የምንሰጥበትን አሰራር እከተላለሁ በማለት አሳወቀ።

በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ክልል ገዢ ሕውሃት መካካል ጦርነት ውስጥ እስከገቡበት ድረስ ያለፉትን ጉዞ የአዲስ ማለዳዎቹ ኤልያስ ተገኝ እና መርሻ ጥሩነህ እንዲህ ቃኝተውታል።

የኢህአዴግ መክሰምና የብልፅግና ውልደት አተካሮ
ሌላው አሁን ላይ በኹለቱ ሃይሎች መሀከል ወደ አልተፈለገ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ካደረጋቸው ዐበይት ነገሮች አንዱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መክሰምና የብልፅግና ፓርቲ ምስረታ ጉዳይ ይገኝበታል።

ኢሕአዲግን አክስሞ አዲስ ፓርቲ መመስረቱ ለሦስቱ ነባር አውራ ፓርቲዎች ማለትም ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ)፣ ለኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን) እና ሌሎች ከዚህ በፊት አጋር ተብለው አብረው ለሚሰሩ ድርጅቶች ቀላል ቢሆንም ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) ግን ቀላል የነበረ ጉዳይ አልነበረም።

የብልፅግና ፓርቲን በመመስረት ሂደት ላይ ድርጅቶቹ ብዙ ተከራክረዋል ፤ተገማግመዋል አልፎ ተርፎም ልዩነቶቻቸውንና እና አነድነታቸውን አንፀባርቀውበታል።
ለአብነት እንኳን ብንወስድ ልክ የዛሬ ዓመት በነበረው የማክሰምና የመውለድ ሂደት ወቅት የተለያዩ ሀሳቦች በፓርቲዎቹ ተወካዮችና በምሁራን ይነሱ ነበር።አንዳንዶች ኢሕአዴግ ከስሙም እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሆኖ አገሪቱን ለ29 ዓመታት ያህል አስተዳድሯል። ግንባር ሆኖ ይህን ያህል ዘመን ማስተዳደሩ አስደናቂ ነው ብለው ያነሳሉ።

ለምርጫም ሲወዳደር የቆየው ኢሕአዴግ ሆኖ በግንባር ሆኖ ነው እንጂ ፓርቲ ሆኖ አልነበረም። ስለዚህ ከሽግግር ጊዜ በኋላ ግንባር ሆኖ መቀጠል አልነበረበትም ውህደቱ እንደውም ዘግይቷል የሚል አቋምም ነበራቸው።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው ውህደቱ የኢትዮጵያን የፌደራል ስርዓት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ተሠሚነት ላልነበራቸው አጋር ድርጅቶች እኩል ድምጽ የሚሰጥ ኅብረ ብሔራዊነትን የሚያፀና፣ አካታችነትንና ፍትሃዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሁነኛ አቅጣጫ ነው ብለው ነበር። የፓርቲው ውህደት ሀገራዊ አንድነትን ከህብረ ብሔራዊነት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው ነበር ሊቀ መንበሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰሜኑ አለቃ ሕወሓት ከደርግ ውድቀት ማግስት በኋላ በነበሩት ጥቂት የሽግግር ዓመታት የመበታተን ሳይሆን የመሰባሰብና የአንድነት ፈውስ የሰጠ፤ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል የማዕዘን ድንጋይ የተቀመጠበት፤ አንዣቦ የነበረው ከባድ አደጋ እንደ ጉም በኖ የመጪው ዘመን ተስፋ ጮራ የፈነጠቀበት ወቅት እንደነበር ያነሳሉ።

ያ በኢህአዴግ የተፈጠረው የብሩህ ተስፋ ጮራ በየወቅቱ በሃቀኛ መስመርና ፕሮግራም ተመስርቶ በሚካሄደው የተግባር እንቅስቃሴ እየደመቀና እየሰፋ ባለፉት 27 ዓመታት ተአምራዊ ድሎች ሊመዘገብ ችሏል የሚል አቋም ይዞ ነበር። በነዚህ ዓመታት በዋንኛነት ከሚጠቀሱት ክንዋኔዎች ውስጥ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃል- ኪዳን ሰነድ የሆነው ሕገ-መንግስት ፀድቋል፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተተክሏል። የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ግብርና መር የልማት ስትራቴጂ ተነድፎ በምግብ ራስን በመቻልና ለገበያ የሚሆን ትርፍ ምርት በመላክ ረገድ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ተችሏል በማለት ይከራከራሉ።

የሕውሃት ተቃውሞ ድምጾች
ሕወሓትን ጨምሮ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር የሚመነጩ የድርጅቱ ፅኑ እምነቶችና መመሪያዎች በጠራራ ፀሐይ ተቀምተው ባልተስማማንበት በሌላ ኃይል አስተሳሰብና ፕሮግራም እየተተኩ ይገኛሉ ሲል ልሳኑ በሆነው “ወይን “የህትመት ውጤት ፅፎ መግለጫ አውጥቶ ነበር።

በተለያዩ የሚዲያ አይነቶች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች የሕወሓት ሀላፊዎች ሲመልሱ ብሔር ላይ መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም እያራመደች ያለች አገር ላይ አንድ ፓርቲ ሲፈጠር በክልሎችና በአገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል ምን ዓይነት ግንኙነት ይኑር? ምን ዓይነት የሥልጣንና የሥራ ክፍፍል ይኑር? ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም የሚከተሉ አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? በአገራችን እንዴት ይስተናገዳል? የውክልና፣ የአመራር ስርዓት፣ እኩልነትና ነፃነት፣ የጋራ ተጠያቂነት…ወዘተ እንዴት መሆን በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ መግባባት ሳይፈጠር በአዋጅ የሚፈፀም ውህደት ከቶም የለም እያሉ ይመልሱ ነበር።

በመስከረም 25 /2011 ሐዋሳ ላይ በተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ለብልፅግና ፓርቲ ፅንሰት ከፍተኛ ውይይቶች መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን።በወቅቱ የነበረው ኢህአዴግ ራሱን ሲገመግም ባለፉት ሦስት ዐስርት በሚጠጉ ዓመታት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው የሕዝቦችን የለውጥ ጥማት ሊያረካ የሚችል ሥራ በሚፈለገው ደረጃ አልሰራንም፤ የዴሞክራሲ ባህል አላጎለበትንም፤ ምህዳሩ እየጠበበ መጥቷል እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት ታይተዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር።

ከአስራ አንደኛው የሐዋሳ ጉባኤ በኋላ ኢህአዴግ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እና የሚታገሉበት የጋራ መድረክ ይሆን ዘንድ የጥናት ሥራዎች እንደተጀመሩ በጉባኤው የአቋም መግለጫ በማውጣት ይህን ተከትሎ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ እንደ አንድ ህብረ ብሔራዊና አገራዊ ድርጅት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ህሊናዊ እና ነባራዊ ሁኔታ ላይ መገኘት ችለናል በማለት በአብላጫ ድምፅ ውህደቱን ተቀብሎ አፅድቆ ነበር።

ሆኖም ከውሳኔው በሗላ ከሕወሓት አቅጣጫ የተለያዩ ሀሳቦች ይገለፁ ነበር።ለምሳሌ አምና
በሕዳር ወር አካባቢ የህወሓትና የያኔው ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ ሲናገሩ። የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ተዋህዶ አንድ ወጥ ሃገራዊ ፓርቲ የመሆኑን ጉዳይ ህወሓት ፈጽሞ እንደማይቀበለው፤ የግንባሩ ውህደት ጉዳይን በተመለከተ የህወሓትን አመለካከትንም ሲገልጹ “እንደዚህ ዓይነት ለስልጣን ተብሎ የሚፈጠር ውህደት ህወሓት ፈጽሞ አይቀበለውም” ብለው ነበር።

ጌታቸውም ጨምረውም “ህወሓት እንደ መርህ የሚከተለው ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዴት ይቆዩ የሚል ሳይሆን፤ አንድን ድርጅት፣ ድርጅት የሚያደርገው ሃሳብን ነው ብሎ ነው የሚያምነው።”ሲሉ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረው የነበረ ሲሆን እርሳቸው በወቅቱ እንዳሉት “በየእለቱ እርስ በእርስ እየተናቆሩ የሚውሉት አባል ፓርቲዎችን ይዘን የሃገር ችግርን በመረዳትም ሆነ ችግርን ለመፍታት በምንከተለው መንገድ ጭምር ውሁድ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፤ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቷን ችግር የሚፈታ ሃገራዊ ፓርቲ ይፈጠራል ብሎ ህወሓት አያምንም” ብለው ነበር።

በወቅቱም የህወሓት አቋም ምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁም የሚከተለውን ምላሽ አስቀምጠው ነበር።ከዚህ በፊት በግንባሩ ስብሰባዎች ላይ እንደተወያዩት አባል ፓርቲዎቹን የሚለያዩዋቸውን ጉዳዮች በማጥበብ በሃሳብ ወደ አንድ የሚያመጣችውን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው።ከዚያ ውጪ ካልተዋሃድን ወይም ስያሜ ካልቀየርን በቀጣዩ ምርጫ አናሸንፍም በሚል ርካሽ ስልጣን ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አካሄድን ህወሓት ድሮም አይቀበለውም አሁንም የሚቀበለው አይሆንም ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ህዳር 11 ቀን 2012 ከህወሓት ውጪ በተደረገ የያኔው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ምክር ቤቱ ውህደቱን በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን።ህዳር 21 ውሕደቱን የተቀበሉት ፓርቲዎች ተፈራርመው ብልፅግና ፓርቲ በይፋ የተመሰረተ ሲሆን ህዳር 24 ፓርቲው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ጥያቄ አቅርቦ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታህሳስ 15 /2012 ለብልፅግና ፓርቲ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።

የቀድሞዋ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሒም ሚያዚያ 22/2010 የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እስከለቀቁበት ሰኔ 1/2012እለት ድረስ በሀላፊነት ሲገለግሉ ቆይተዋል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) የሥራ አስፈጻሚ አባልና የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከኃላፊነት የመልቀቃቸውን ውሳኔ መቀሌ በመገኘት ነበር በትግራይ ቴሌቪዥን የተናገሩት። ኬሪያ በወቅቱ ሥልጣናቸውን የለቀቁበት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ አንደማይችል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ ምርጫውን ለማራዘም በወቅቱ የተቀመጠውን አማራጭ የህገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥ የሚለውን ውሳኔ እና ትርጉም ለመሥጠት እየተሄደበት ያለውን መንገድ አለመደገፋቸውን መሆኑን አብራርተው ነበር።

ኬሪያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት “የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በየቀኑ ከሚጥስና አምባገነንነትን ከሚያራምድ ቡድን ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ነው” ብለው አልፈዋል። አፈጉባኤዋ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በስልጣን ላይ ያለው ወገን “ሕገ መንግሥቱን በግላጭ ጥሷል አምባገነናዊ መንግሥት ወደ መመስረት ገብቷል” ሲሉ አጣጥለው ነበር።

ለዚህም እንደማሳያ ያስቀመጡት ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለምርጫ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለ ክፍተትን በመፈለግ “አንዱን አንቀጽ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክፍተት እንዲገኝና አማራጭ እንዲፈለግ” ጥረት ተደርጓል በማለት የምርጫውን መራዘም በይፋ መቃወማቸውን አስታውቀው ነበር።
የምርጫውን መራዘም ሕወሓት በይፋ በመቃወም የአገሪቱ መሪ ከሆነው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በየእለቱ የቃላት ጦርነት መወራወሩን እርስ በእርስ መካሰሱን ቀጠሉበት። በትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ሕወሓትና በፌደራል መንግስቱ መካከል መጠነኛ የነበረው ልዩነት የምርጫ መራዘምን ተከትሎ ልዩነቱ እያየለ መምጣቱ በገልጽ በመታየቱ አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር በኹለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረወን ልዩነት በውይይት አንድፈቱ ጥሪ አስተላልፈው ነበር።

የፌደራል መንግስቱ እና የሕወሓት የቃላት ጦርነት እየተባባሰ በመምጣቱ በአገር ላይ ስጋት መደቀኑን የተገነዘቡ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ልየነቱን ለማጥበብ እና ኹለቱ አካላት ተቀራርበው ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ለማቀራረብ ባሳለፍነው ሰኔ 9/2012 ወደ ትግራይ ክልል በማቅናት ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ አቅንተው ነበር። የአገር ሽማግሌዎቹ በራሳቸው ፈቃድ ለአገር በማሰብ በቀናነት ለማቀራረብ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

የአገር ሽማግሌዎቹ የመቀሌ ጉዞ ዋና አላማ ባለፉት ኹለት ዓመታት በትግራይ ክልል መንግስት እና በፌዴራል መንግስት መካከል እየተፈጠረ ያለው ልዩነት ለማስቀረት እና ለማጥበብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ነበር። በወቅቱ የአገር ሽማግሌዎቹ በኹለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ የሄዱበት መንገድ ውጤታማ አልነበረም።

የትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የፌዴራል መንግሥትን የሚያስተዳድረው የብልፅግና ፓርቲ መካካል ያለው የቃላት ልውውጥ እየበረታ መጣ። የቃላት ልውውጡ እየበረታ በመምጣቱ የትግራይ ክልል የወቅቱ ገዥ ሕወሓት በትግራይ ክልል ስድስተኛውን ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑን ደጋግሞ በማሳወቅ ለምርጫው ዝግጅት ማድረግ ቀጠለ።

ሕወሓት በክልል ደረጃ በሚካሂደው ምርጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ አንዲያስፈጽምለት በደብዳቤ ቢያሳውቅም ምርጫ ቦርድ በክልል ደረጃ የሚደረግ ምርጫ አላካሂድም ህጋዊ አይደለም የሚል መልስ ሰጥቶ ነበር።

በመሆኑም ክልሉ የክልል ምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ምርጫውን እንደሚካሄድ በማሳወቅ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት በማድረግ ላይ እያለ የፌደሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል ምርጫ ህጋዊነት የሌለው እና ቢደረግም እንዳልተደረገ የሚቆጠር ምርጫ ነው ሲል አሳወቀ። የልዩነት ደረጃውን በየእለቱ እያደገ መጣ።
ሕወሓት“ሕዝባችን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው እና የማንም ፈቃድ የማይጠይቅበት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም በክልላችን ምርጫ እንዲደረግ እና ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች እንዲቀጥሉ”ሲል መወሰኑን አስታውቆ ነበር። የክልሉ መንግስት የፌደሬሽን ምክር ቤት እውቅና የለውም ያለውን ምርጫ የምርጫ ቅድመ ሁኔታዎችን በማከናወን ላይ ሳለ አለም አቀፉ ክራይስስ ግሩም ልዩነቱ በድርድር እንዲፈታ አሳስቦ የነበረ ቢሆንም ለውይይት ክፍት ሁኔታዎች አልነበሩም።

ይባስ ብሎ በኹለቱ አካላት መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ በመምጣቱ የትግራይ ክልል መንግስት ክልላዊ ምርጫ በትግራይ ክልል ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ለማስቆም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ እንደ ጦርነት አዋጅ እንደሚቆጥረው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአባላቱ ባስተላለፈው ጥሪ ላይ 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ አስቻኳይ ስብሰባ ነሐሴ 30/2ዐ12 እንደሚካሄድ ከማሳወቅ ውጪ በምን አጀንዳ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ የገለጸው ነገር ባይኖርም፣ የትግራይ ክልል ሥራ አስፈጻሚ በክልሉ በሚካሄድ ምርጫ ላይ የሚሰጥን ውሳኔ እንደማይቀበለው ቀድሞ በመግለጫ አሳውቆ ነበር።

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በ27/12/2012 ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባዔ ለማካሄድ በሚያስብበት ወቅት አጀንዳውን ለአባላቱ መግለጽ እንደሚጠበቅበት አስረድቶ፣ በተደጋጋሚ ስለአጀንዳው መጠየቁን ገልጿል። ሆኖም ግን አጀንዳውን ሳያውቁ ቀድሞ ሳይገለጽላቸው እንደማይሳተፉ በማሳወቅ ሳይገኙ ቀሩ።

እንዲህ አንዲህ እያለ የልዩነት ደረጃው እያደገ በሀሳብ ልዩነት ላይ የተመሰረተው ወደ ተግባር መቀየር ተጀመረ። ሕወሓት በፌደራሉ መንግስት ሕገ ወጥ ነው የተባለውን ምርጫ ጳጉሜ 4/2012 በይፋ በማካሄድ ማሽነፉን አበሰረ። ማሽነፉን ተከትሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትግራይ ክልል መንግስት ሆኖ እንደሚቆይ በይፋ አወጀ።ከመስከረም 25/2012 በኃላም የፌደራል መንግስት ህጋዊ እውቅና እንደሌላ በመግለጽ ለፌደራል መንግስት ተገዢ እንደማይሆን አስታወቀ።

በዚህ መካከል የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ክልል ሕገ ወጥ የተባለውን ምርጫ በማካሄዱ ሕገ ወጥ ቡድን እንደሆነ በማወጅ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን በጀት በወረዳዎችና በክፍለ ከተሞች ደረጃ እንደሚሰራጭ አስታወቀ። ውሳኔው ሕወሓትን ያስደነገጠ ነበር። ሆኖም በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል የነበረው ልዩነት እንዱ ሌላውን ሕገ ወጥ ቡድን በሚል ክስ ሲካሰሱ ቀናቶች ተቆጠሩ። ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ ከሳምንታት በፊት ሕወሓት በተደጋጋሚ በተለይም የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጀት ለክለሉ መዋቅር እንደማይሰጡ ከወሰነበት ቀን ጀምሮ ሕወሓት የፌደራል መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት አንዳወጀ እንቆጥረዋለን በማለት ከውይይት ይልቅ ወደ ጦርነት የሚመሩ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲያወጣ ነበር።

ሕወሓት ጳጉሜ 4/2012 ባካሄደው ክልላዊ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል(ዶ/ር) ያሳለፍነው ሰኞ ጥቅምት23/2013 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፌደራል መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ ተደጋጋሚ በደል መፈጸሙን በመግለጽ አሁን ላይ ያለን የመጨረሻ አማራጭ እንደ ህዝብ መዋጋት መሆኑን በይፋ ተናግረው ነበር። ደብረ ጽዮን በመግለጫቸው ከመንገዳችን የሚደናቅፈንን ሀይል ውጊያ እንገጠማለን በማለት የተፈራውን ጦርነት ለመቀስቀስ ጉትጎታ አድርገዋል። “የምንገጥመው ውጊያ የህዝብ ውጊያ ነው የሚሆነው። ድሉ የኛ ነው፣ ድሮም የኛ ነበር አሁንም አሽናፊዎች እኛ ነን።” ሲሉም የጦርነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ነበር። ፕሬዝደንቱ አክለውም “የፈለገው መሳሪያ አያሸንፈንም፣ እንደ ትግራይ ተዘጋጅተናል እንገጠማለን።” ሲሉ የጦርነት ነጋሪቱን ጎስመዋል።

ይህ በሆነ በማግስቱ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2013 ለሊት በትግራይ ክልል መቀመጫ መቀሌ ላይ ያልታሰበ እና መላ ኢትዮጵያንን ያስደነገጠ ድርጊት ተፈጽሞ ማደሩን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ጥቅምት 25/2013 በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው አረዱ

በማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተሰማው ዜና “ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል።” የሚል ነበር። በመግለጫው “ሕውሃት እንደ ባዕድ እና እንደ ወራሪ አገር ሠራዊት ቆጥሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝለፍ ተነሥቷል። በዳንሻ በኩልም ጦርነት ከፍቷል” ብለው የጦርነት ትንኮሳውን አበሰሩ።

ሕወሓት ያልተፈለገ ጦርነት መጀመሩን ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ መከላከያ በአካባቢው ህግ የማስከበር ሥራ እንዲሰራ ትእዛዝ መሰጠቱን ገልጸው ነበር። በዕለቱ ማለትም ጥቅምት 25/2013 በነበረው የመከላከል ሥራ ውጤታማ እንደነበር በዕለቱ ምሽት ላይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com