ትምሕርት ቤቶቻችን ተማሪዎች የሚፈሩበት እንጂ የሚፈሩበት?!

Views: 141

ናፍቆት እና ሰቀቀን የገጠሙ ይመስላል፤ለወራት ተዘግቶ የከረመው ትምህርት ቤት ሊከፈት ነው ።በኮቪድ 19 ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው የነበሩ ሁሉ ወደ ትምርት ቤታውቸው ለመሄድ ቸኩለዋል።በአንጻሩ ወላጅና የትምህርቱ ማኅበረሰብ ይህ የትምህርት ዘመን ምን ይዞባቸው እንደሚመጣ ሲያስቡት ገና የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ አለ።ልጄን ምን ይጠብቀው ይሆን? ኮ ቪድ 19 እንደኛው ጉዳይ ቢሆንም ከዚህ በላይ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ግን ተማሪዎች በይደር ያቆዩት በሔር ተኮር ሽኩቻቸው ነው። በኃይሉ ኢዮስያስ የትምህርት ቤቶች መከፈት ለተማሪዎ እውቀት የሚያፈሩበት ወይስ ለሕይወታቸው የሚፈሩበት ?ይላል

አንዲት አገር በሕልውናዋ እንድትቀጥል ቀጣይነቷን የሚያረጋግጡ ትውልዶች ያስፈልጓታል። በአጭሩ የትውልድ መቀጠል የአገር መቀጠል ዓይነተኛ ሕላዌ ነው ማለት ነው። አንድ ትውልድ የሚባለው እንደ አለማቀፉ ትንታኔ ገለጻ ከሆነ ፳፭ ዓመታት ናቸው። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ስለአገር ግድ የሚሰጠው ሰው አገርን በትውልድ መካከል ያስቀጥላል፤ ያጠናክራትማል። ስለአገር ግድ የማይሰጠው ከሆነ ደግሞ በትውልዱ መካከል አረምን በማብቀል ቀጣይነቱን ይውጠዋል እናም የአገርም ሕልውና እንዲሁ ይፈጸማል፤ ያከትምማል። የሆነው ሆኖ ለአገር ሕልውና አብነት የሆነው የትውልድ መቀጠል አልያም አገርን አጥፊነቱ አሌ የማይባልለት የትውልዱ መቃጠል (መባከን) ልንገለገልበት እንደምንሻው (የተገለጠ በተቃራኒውም ምርዝ ጽንስ የሆነ) ቀዋሚው የልማትም ሲጻረርም የውድመትም መሳሪያ ነው – ትምሕርት።

በእርግጥም ትምሕርት በትውልድ መካከል ድልድይ በመሆን ቀዳሚውን ከአሁኑ እና ከመጪው በታሪክ ያገናኛል። ስለአካባቢና ስለአገር መልክዓ ምድር በማስተማርና በመግለጽ ትውልዱ ከሚኖርበት ስፍራ (ሰፈር) ባሻገር ያሉትን የአገሩን ብሎም የዓለማቱን የመሬት አቀማመጦች፥ የአየር ንብረት . . . ወዘተርፈ በማሳየት ግንዛቤን ይፈጥራል፤ ስለቁሳቁሶች ስለተለያዩ እጽዋት ቅመማና አዘገጃጀትም በተግባርና በንድፈ ሐሳብ በማሳየትም ስለምንኖርባት መሬትና ከምድርም አስመንጥቆ በጠፈር ስላሉ ሌሎች ዓለማት፥ ስለቁሳዊ ይዘቶችና ብሎም ስለመድሐኒቶች አዘገጃጀትና በሽታን እንዴት መፈወስ እንደሚቻል ያሳያል፤ በቀመር (በስሌት) በመረዳት ሕይወትን፥ ዓለምን (ተፈጥሮን) ቀናትን፥ ወራትን፥ ዓመታትን በቁጥሮች ያለዝንፈት ማስላት እንደሚቻል በመኖር መርሕ ያስረዳል፤ በሰዎች መካከል ተግባቦትም እንዲኖር ለድምጽ ከተወከሉት ፊደሎች አንስቶ እስከ ቃላት፥ ሐረጋትና ዓረፍተ ነገሮች ንባብ . . . ወዘተርፈ ድረስ በማሰልጠን የአረዳድ ግድፈትን ያ’ርቃል፥ የሚበጀውን ተሞክሮም ከሌላ ሀገራትና ማሕበረሰብ በውርስም ይሆን በማዛመድ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ በመዶል ሁለንተናዊ የአገር ዕድገትን ለማጠናከር አይተኛም። በትምሕርት ከዚህም በላይ ትሩፋቶች እንዲኖሩ ባይካድም እነዚህ ሁሉ ገጸ በረከቶች የሚሰፈሩበት ስፍራ ትምሕርት ቤት መሆኑን ደግሞ ልቦና ልብ ይሏል።

ትምሕርት ቤቶች (ሃይማኖታዊ፥ ባሕላዊ አልያም ዘመናዊ/ የቀለም) የሚሰኙቱ በየትኛውም የዓለማት ክፍል ብንሔድ ከሕጻንነት አንስቶ እስከ ብስለት (እውነትም ትምሕርት ወሰንን ቢያሰፋ እንጂ በዘመን መግፋት አይገደብምና) እንዲሁም በእርጅና እድሜ እንኳን እነዚሁ ትምሕርት ቤቶች ትውልድን የሚሰሩ ብቸኛ ተቋማት ሳይሆኑ አይቀሩም ብሎ ለመናገር ያንደረድራሉ፤ ሌሎች ትውልድን ሰሪ ተቋማት ሊኖሩ እንዲችሉ ቢታወቅና የእነዚህን (ሌሎች) ተቋማት ግብራቸውን ማሳነስም ባይሆንም ግን ግን ከነዚህ እዚህ አሁን ከሚጠቀሱቱ (በተለይም ከሕጻንነት ጀምረው ትውልድን ከሚያንጹት ተቋማት) አንጻር ንዑሳን ይመስላሉ። በኹለንተናዊ ዘርፍ ትውልድ ከጨቅላ አዕምሮው አንስቶ የሚሰራበትና የሚታነጽበት የማይሞት ሕላዌ ያለው ታላቆችን የሚፈጥር ትልቅ ተቋም ትምሕርት ቤቶች ናቸውና!!!

ዘመናዊ ትምሕርት ቤቶች በአገራችን ዙሪያ ከመምጣታቸው ቀድሞ የነበሩና አሁንም ያሉ የአብነት ትምሕርት ቤቶች በተለያዩ ስፍራዎች የገኙ ነበር፤ አሁንም ቢመናመኑ እንጂ አልጠፉምና። እነዚህ ትምሕርት ቤቶች ግባቸው ሃይማኖትን አስተምሮ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ትውልድን ፈጥሮ በየአድባራቱ በመሔድ አምላክን ያገለግሉት ዘንድ እንዲያዘጋጃቸው ነውና የአንድ ቤተዕምነት ልሕቀትን ብቻ ስለሚያሳይ መመንመኑ ይገባል የሚሉ አይጠፉም። እነዚህ ትምሕርት ቤቶች በወቅቱ የነበረውን ሕዝብ ደርሰው ከማገልገልና በባሕላዊ ሕክምና፥ ድርሳናትንና ኪነጥበባዊ የሚታዩና የሚዳሰሱ እንዲሁም የማይታዩና የማይዳሰሱ እሴቶችን ለአገሪቷ ከማበርከት አልፈው ዛሬ ዘመናዊ ትምሕርት ቤቶች ለምንላቸው ተቋማት ጽኑዕ መሰረት ነበሩ፤ ዛሬም ቢሆን ናቸው!!!

በነዚህ የአብነት ትምሕርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በተለምዶ “የቆሎ ተማሪዎች” የሚሰኙቱ የትምሕርታቸው አንዱ ፈተና ችግርን፥ ብርድንና ረጅም ጉዞን ተቋቁመው ከአንዱ መምሕር የጠነቀቁትን ትምሕርት አስቀጥለው ራቅ ወዳለው መምሕር ደግሞ በመሔድ ሌላና ተጨማሪ የዕውቀትን እንጀራ ለመብላት ሁሌም ረሐብተኛ (የተራቡ) ነበሩ፤ ዛሬም አሉ አልጠፉም። ታዲያ በዚህ ጊዜ ችግር (ረሐብ) የማይፈታውን ጉባዔ አልፎ አልፎ በሚከሰትበት ጊዜ ጸረ ጉባዔ ሆኖ የሚፈታው ወረርሽኝ (ተላላፊ በሽታ) ነበር፤ ያን ጊዜ ረሐብ ያልመተረው፥ ችግር ያልበገረው ውርጭና ሐሩር ያላጠወለገው፥ የቤተሰቡ እጦትና ናፍቆት ያልሰበረው ተሜ፡ ሊቃውንቱ ተጠበው መላ እስኪያበጁ ይበተናል። ወንበርም አይዘረጋም፤ ጉባዔም ጦሙን ያድራል – ሐዘን ይበረታል።

እነሆ ዛሬም ሰለጠነ በሚባለው ዓለም ላይ የምትገኝ ኢትዮጵያ ከሰብአዊና አዕምሮአዊ ስልጣኔዋ ይልቅ በዓለም ላይ የከፋው ወረርሽኝ ሰልጥኖባት “ነገ ተምረው አገርን ይገነባሉ፥ ተተኪም ትውልድ ናቸው!!!” ስትል በትምሕርት ገበታ ላይ አቅርባ በዕውቀት ጉባዔ ላይ ሸክፋ ይዛ የነበር ልጆቿን (ቅድሚያ ደሕንነታቸው ያሳስባታልና) ከበተነቻቸው ወራት እንደዘበት ነጎዱ። እውነት ነው ይህ ወረርሽኝ መከሰቱ እና ተማሪዎች ወደ የቤተሰቦቻቸው መላካቸው (ትምሕርት ቤቶች ተማሪዎች የሚፈሩባቸው እንጂ የሚፈሩባቸው ስላይደሉ) በአንድ ጎኑ ባርኮት ነበር – ሰይጣን የተሳፈራቸው ፖለቲከኞች የሚጋልቧቸው ተማሪዎች በዘር ዛር፥ በሃይማኖት ጥላቻና የአስተሳሰብ ልዩነት ባላቸው ምስኪኖች ላይ ጃስ በተባሉ ቁጥር (በኦሪት እንደነበረው ሁሉ) ከከፍታ (ፎቅ) ላይ በመገፍተር፥ በድንጋይ ወግሮ በመግደል፥ በዱላ ቀጥቅጦ በመጣል እንዲሁም በስለት (ካራ) የተማሪ ደንብ ልብስ የለበሱ ልጆች ተጨማሪ የሰው ዕርድን እንዳይፈጽሙም ሆነ እንዳይፈጸምባቸው ተከላክሏልና ይሕ ወረርሽኝ መጥቶ ትምሕርት መዘጋቱ አንዱ በረከት ነው። አንዳንዴ መሰል ግጭትንና ቅስፈትን ያቆማል ተብሎ የተሾመው አካል “ራሱን በዳተኝነት አሹቆና” እሱው ራሱ ችግርም አስቸጋሪም ሲሆን እንግዳው መቅሰፍት ደግሞ የቀደመውን ያሽቀነጥርልሐል።

ተጨማሪው በረከት ሊሆን የሚችለው ተማሪዎች በየቤታቸው ሳሉ ትምሕርትን በኢንተርኔት የማዳረስ ዝንባሌ (ምንም እንኳ በኢንተርኔት ትምሕርት መሰጠት እንደጀመረ በተነሳው ቀውስ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም) በተለይም በግል ትምሕርት ቤቶች በስፋት እየተዳረሰ ነበር፤ ይሕም ከማውራትና “ላደርግ ነው! ልሰራ ነው!” እያሉ ቀድሞ ለፍፎ በግብር ግን የዜሮ ብዜት ለተገለጠበት መንግሥት፡ በዋናነትም ለአዲስ አበባ አስተዳደር የነዚህ የግል ትምሕርት ቤቶች የጭንቅ ምርጫ የአስተዳደሩን እና የትምሕርት ቢሮውን ተግባር ምንምነቱን ያሳየበት እንደሆነ እሙን ነው – ምክንያቱም ባሳለፍነው 2012 እያንዳንዱ የመንግሥት መምሕር አነስተኛ tablet pc እንደሚሰጠውና በዛም ትምሕርቱን ሊሰጥ የሚቻልበትን አግባብ አመቻችቶ እንደጨረሰ ደግሞ ደጋግም ነግሮን ነበርና!!! ቢያንስ ቢያንስ ይሕ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ እንኳ (ብዙዎችን ያስገደለውና የኢንተርኔት ጊዜያዊ መቋረጥ ምክንያት የሆነው ነውጥ ባይፈጠር) መንግሥት ትምሕርትን ለማዘመንና በመጠኑስ በከተማ ያሉትን ተማሪዎችን ለመድረስ እንዳወራው ሙከራን ያደርግ ነበርን? መልሱን ለነሱ።

በኢንተርኔት ለመዳረስ ታስቦ የግል ትምሕርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው መስጠት ጀምረውት የነበረው ትምሕርት ብዙዎቹን ትምሕርት ቤቶች የራሳቸውን ድረ – ገጽ (website) እንዲመሰርቱና የመስመር ላይ (online) ትምሕርትን መስጠት በመጀመር የት/ ቤታቸውን አስተዳደሮች፥ የት/ ክፍሎች፥ መምሕራን፥ ተማሪውችንና የተማሪዎችን ቤተሰቦች ያነቃና የዘመናዊውን ዘመን የትምሕርት አሰጣጥን ተሞክሮ ያቃመሰ ጅምር ነበርና ይኸውም አንድ የዚሁ ወረርሽኝ ትሩፋት ይመስላል።
መንግሥት በቅርቡ እንደተናገረው ከሆነ በየሀገሪቷ የሚገኙ ተማሪዎች እንደያሉበት አካባቢና የበሽታው ስርጭት መጠን ትምሕርት ቤቶችን ከፍተው ተማሪዎቻቸውን ሊጠሩ እንዲችሉ እቅድ እንዳለው አሳውቋል። በአዲስ አበባችንም የሚገኙ ትምሕርት ቤቶች በጥቅምት 30 ቀን እንደሚከፈቱና ትምሕርትም መሰጠት እንደሚጀመር ነው ያሳወቀን። ይሕንንም ሲያከናውን ብዙ ውይይትንና መፍትሔ አዘል ሐሳቦችን አሰባስቦ ይበልጥ በማጠናከር የተሻሉትን በባለሙያዎች ምክር ታግዞና አንጥሮ በመውሰድ እንዳደረገው ቢታመንም አሁንም ቢሆን ልጆቻቸውን ወደ ትምሕርት ቤት ለሚልኩ ወላጆች ስጋታቸውን የሚከላ ነገር መፍጠርና የተማሪዎቹን ደሕንነትም የሚያረጋግጥ በግብር የሚገለጥ ነገርን ማየት ይሻሉ፤ ይሕ እንዲሆን ምን ይቅደም?!

ትምሕርት ቤቶች ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው ተማሪዎች ለኹለንተናዊ እድገት የሚዘጋጁበትና ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ታላቅ ግብን የጸነሰ ተቋም ነው፤ በመሆኑም ይህ ስፍራ ተማሪዎች የሚፈሩበት እንጂ የሚፈሩበት ማለትም (ለፍሬ የሚበቁበት ስፍራ እንጂ በፍርሐት የሚርዱበት) ቦታ ሊሆኑ እንዳይገባ የምንስተው ሐቅ አይመስልም። ይሕንን ማረጋገጥ ደግሞ ሀገሪቷን ይመራል የሚሰኘው የመንግሥት አካልና በተለያዩ ደረጃና ዘርፎች ያሉት ጀሌዎቹ ተቀዳሚ ተግባር ቢሆንም ከነዚህ አካላት ባልተናነሰም የወጡበት ማኅበረሰብም ሆነ የእያንዳንዱ ቤተሰብ እና ግለሰብ እንዲሁም የራሳቸው የተማሪዎቹም ሐላፊነት ሊሆን ይገባል። ልጆችን አፈራም አላፈራም ስለተማሪዎች ግድ የማይኖረው ሰው ስለቤተሰቡ፥ ስለማኅበረሰቡና ስለአገሩ ሕልው እና ግድ አይሰጠውም ማለት ነው። ስለአገሩ ግድ የማይሰጠው ሰው ደግሞ ስለራሱ መኖር ግድ የለውም፤ አገር ስትኖር ነውና የሰው ልጅ በሰላምና በጤና ሊኖር የሚችለው ተብሎ ይተረጎምበታልና።

በዚህ ጊዜ ልንዘጋጅበት የሚገባን ነገር ትምሕርት ሲከፈትና ተማሪዎች ከወራት መራራቅ በኋላ ወደናፈቁት ግቢዎቻቸው፥ የትምሕርት ገበታቸውና ጓደኞቻቸው ጋር ሲቀላቀሉ ሊያደርጉት በሚገባቸው ጥንቃቄና የኛም ከነሱ ጋር በመግባባትና በመተማመን የተመሰረተ ቁጥጥርን መተግበር ነው።

መንግሥት በስሩ ለሚያስተዳድራቸው ተማሪዎች የሚያድለውን የጭምብል ብዛትና ዓይነት ቀድሞ ማድረስ ይኖርበታል። በወጪ ረገድ ለዚህ ግብዓት መግዣ የሚውል ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ምደባ (budget) የሚጠይቅ እንደሚሆንና መንግሥትም በዚህ ትንሽ ሊቸገር ይችላል። ሆኖም ይሕንን ወጪ ተገን አድርገው ንዋዩን ለመቦጥቦጥ የሚያሰፈስፉትን የገንዘብ አንበጦችን ለመቆጣጠር ተፈጻሚነቱ የሚያስተማምን ስርዓትን ሊያበጅ ጥሰትም ሲገኝ አፋጣኝ የፍትሕ እርምጃ ሊ’ሰጥበት የሚያስችል ውቅር ቀድሞ ማበጀት ይገባዋል።

የግል ትምሕርት ቤቶችና መላው የትምሕርት ቤቱ ማኅበረሰብም ተመሳሳይ የጥንቃቄ ትኩረትን መውሰድ ይገባዋል። ብዙዎቹ የግል ትምሕርት ቤቶች በትምሕርት አሰጣጣቸው ረገድ ከመንግሥት ትምሕርት ቤቶች አንጻር የተሻሉ መሆናቸውን የተማሪዎቻቸው ወላጆችና ሌሎችም እማኝነታቸውን ቢገልጹም የክፍሎቻቸው የማስተናገድ ብቃት ግን የመንግሥትን ያሕል ሰፊና አዝናኝ ሊሆን እንደማይችል በከተማይቱ ባሉ በደምሳሳው በሁሉም የግል ትምሕርት ቤቶች በመገኘት ማጣራት ይቻላል።

በሽታው እየከፋና በቁጥር ረገድ እየጨመረና እየገነነ በመጣበት ጊዜ ትምሕርት ቤትን መክፈቱ አደጋ እንደሚኖረው ከግምት ያለፈ እርግጠኛነት መናገር ይቻላል፤ አደጋውን ለማጥፋት ባይቻልም ግን ለመቀነስ ግን እንደሚቻል እንዲሁ። በመሆኑም የተማሪዎችን ቁጥር አመጣጥኖ ትምሕርት ቤቶቹ ከግቢያቸውና ከክፍሎቻቸው ሕንጻ (physical setup) አንጻር ለተማሪዎቻቸው እና ለመምሕራኑ የሚስማማ እና ደሕንነታቸውን ቅድሚያን የሚሰጥ፥ ከተፈቀደው የፈረቃ ትምሕርት ጋርም የሚጣጣም የትምሕርት ስራን እንዲያካሒዱ መንግሥት ከቁጥጥር ያለፈ እገዛን ሊያደርግላቸው ግድ ይላል – እነሱም አገር ተረካቢ ትውልድን ለመስራት የራሳቸውን ታላቅ ሐላፊነት እየተወጡ በመሆኑ!!!

በመጨረሻም፦ ተማሪዎቻችን ከረዘሙ ወራት ቆይታ በኋላ ወደትምሕርት ገበታቸው የሚመለሱበት ሰኞ ጥቅምት 30 ቀን እንደአንድ ስጋትና ጉጉት የተቀላቀለበት የሁላችንም የትኩረት ዐይኖቻችንንና ጆሮዎቻችንን ወደ ትምሕርት ቤቶቻችን የምንወነጭፍበት የጸሎት/ የዱአ ዕለት መሆኑ አይታበልም። እናም ይሕች ቀን እስክትደርስም የበሽታው ስርጭት እንዲቀንስ እያንዳንዳችን ስርጭቱን ለመቀነስ የየራሳችንን ጥንቃቄ እየወሰድን ወደፈጣሪ ካንጋጠጥን ዕለቷን የምንጠብቃት ስጋት በተሳገበት ጉጉት መሆኑ ቀርቶ በናፍቆት ብቻ ይሆናል።

ማን ያውቃል ነገ ምን መፍትሔን ይዞ እንደሚነጋ?! እንደሚነጋ እናውቃለን፤ አብረን እንደምንነጋም ተስፋ እናደርጋለን፤ መፍትሔ ሊኖር እንዲችል ደግሞ እያንዳንዳችን እንሰራለን፤ ለመፍትሔ የሚሆነው ስራችንም ለራሳችን የሚገባውን ተገቢ ጥንቃቄ በመውሰድ ይጀምራል።
በጤና ያቆየን።
አበቃሁ።
በኃይሉ ኢዮስያስ

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com