የእለት ዜና

የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 89 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2013 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ89 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ለአዲስ ማለደ አስታወቀ።
ኢንተርፕራይዙ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ብር 96 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 83 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የኢንተርፕራይዙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ሮቤል አያሌው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች ማለትም ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ ክፍያ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ ሥድስት ነጥብ ሥድስት ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአጠቃላይ 90 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት በአዲስ-አዳማ እና በድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ መንገዶች ኹለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የትራፊክ ፍሰቶችን ለማስተናገድ ታቅዶ ኹለት ሚሊዮን ያኽል ለማከናወን መቻሉን አስታውቋል።ይኽም የኢተርፕራይዙ ክንውን የዕቅዱን 85 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2012 በጀት ዓመት ከ381 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው። ኢንተርፕራይዙ ገቢውን የሰበሰበው ከአዲስ አበባ- አዳማ እና ከድሬድዋ- ደወሌ የፍጥነት መንገድ የአገልግሎት ክፍያ እና ከማስታወቂያና ሌሎች አገልግሎቶች መሆኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጾ ነበር። በበጀት ዓመቱ ከአዲስ- አዳማ እና ከድሬድዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች በድምሩ ከ8 ሚሊዮን በላይ የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ የሚታወስ ነው።

በሩብ ዓመቱ የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃግብሮችን በማዘጋጀት፣ በማስተማር እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን ኢንተርፕራይዙ የጠቆመ ሲሆን። አደጋ በሚያጋጥም ጊዜም በአደጋ መቆጣጠሪያ እና የጉዳት መቀነሻ መለኪያዎች መሰረት በብቃት በመፈጸም፣ የአደጋ ምላሽ ሰጪነት እና ውጤታማነት በማሳደግ፣ በደረሰ አደጋ የተዘጉ የመንገድ ክፍሎችን በፍጥነት ክፍት በማድረግ የትራፊክ ፍሰት እንዲቀጥል ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ኢንተርፕራይዙ የጥገና አቅምን በማሳደግ የሦስት ነጥብ 77 ኪሎ ሜትር የመንገድ አካፋይ ብረት (Gardrail) እንዲሁም 337 ሜትር ርዝመት ያለው የአጥር ጥገና በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ ማከናወኑን አስታውቋል። የተካሄደው ጥገናም በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በመንገድ ንብረቶቹ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመጠገን የመንገዱ ምቾት እና ደህንነት እንዳይጓደል ተሰርቷል ነው ያለው ባለስልጣኑ።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የተለያ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት ሮቤል በዋናው መስሪያ ቤት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ እያከናወነ ሲሆን ይህም ግንባታው 97 ከመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልፀዋል።

የ24 ሰዓት የክፍያ መንገድ አገልግሎቱ በወቅታዊው የኮሮና ወረርሽን ስጋት ሳይስተጓጎል የሰራተኞች እና የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነትን ባስጠበቀ ሁኔታ ማስቀጠል መቻሉ፣ የተቋማዊ ሃብት መረጃ አስተዳደር መተግበሪያ (ERP Software) በተሻለ ሁኔታ መተግበሩ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የተደረገ ቅድመ ዝግጅት እና ግብዓት በወቅቱ በማቅረብ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉ የሩብ ዓመቱ ጠንካራ ጎን እንደነበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል በድሬደዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ የተሽከርካሪዎች የክብደት ቁጥጥር ሥራ ውጤታማ አለመሆኑ እና ከክብደት በላይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በመንገዱ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ትኩረት የሚሻ ጉዳዮች መሆናቸውን ሮቤል ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com