የእለት ዜና

የሲሚንቶ ምርት በ 17 ነጥብ 5 በመቶ መጨመሩ ታወቀ

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተመረተ ያለው ሲሚንቶ መጠን ከባለፈው ወራት ጋር ሲነጻጸር ከ 17 በመቶ በላይ መጨመሩን የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ተቋም ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በተቋሙ የሲሚንቶ እና ተዛማጅ የኢንዱስትሪ ልማት ምርምርና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ስመኝ ደጉ እንደተናገሩት በመስከረም ወር ከስድስት መቶ ሺሕ ቶን ሲሚንቶ የተመረተ ሲሆን በጥቅምት ወር ግን ሰባት መቶ ሺሕ ቶን ምርት መመረቱን እና ምርቱ መጨመሩ አገራችን ያለባትን የሲሚንቶ እጥረት ከማስቀረት አንፃር ትልቅ ለውጥ ያመጣል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ምርቱ ሊጨመር የቻለው በመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የምክክር እና የክትትል ሥራ እንደሆነ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀራረብ እቅዶችን በማቀድ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎቹ ከሀምሌ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት መጨረሻ በትንሹ 63 በመቶ የሚሆን ምርቶችን እንዲያመርቱ ከሲሚንቶ እና ተዛማጅ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር እንደተስማሙ እና ከአምራቾቹ ጋር በየወሩ በእቅዳቸው መሰረት እንዲያመርቱ ስምምነት እንደተፈራረሙ ነግረውናል።
የምርት አቅማቸውን ከማሻሻል ረገድ የጥገና ስራዎች የሀገር ውስጥ ግብአት ላይ በተለይም የድንጋይ ከሰል ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ እንዲያገኙ ማድረግን እየሰሩበት እንደሆነ ገልፀዋል።

በአሁኑ ሠዐትም 14 የሚሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ እንዳሉ ጠቁመው ከነዚህ 14 ፋብሪካዎች ውስጥ ክሊንከር የሚያመርቱ 10 ፋብሪካዎች እንዳሉ እና አራት የሚሆኑት ደግሞ ክሊንከሩን እየፈጩ ሲሚንቶ እንደሚሰሩም ለማወቅ ተችሏል።

በጥቅምት ወር ከፍተኛውን የሲሚንቶ ምርት ያመረተው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ሲሆን ያመረተውም 15 ሺህ ቶን እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።በዚህም ዳንጎቴ ሲሚንቶ በወር አመርታለው ብሎ ካቀደው በላይ ማምረት መቻሉን አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ ከእቅድ በታች ወይም ዝቅተኛ ምርት ያመረቱ ኹለት ፋብሪካዎች እንዳሉ እና ምርታቸውም 60ሺሕ ቶን እንደሆነ ታውቀዋል።ይህም የሆነው ያልተሟላ የመሰረተ ልማት በመኖሩ እና በተለይም የመብራት ችግር ስላለ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አስረድተውናል።
በ2012 በጀት አመት ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊየን የሚሆን ሲሚንቶ እንደተመረተ እና በአሁን ሰዐትም ኢትዮጵያ በዓመት 13 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያስፈልጋት ይህም በወር በትንሹ አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ቶን አካባቢ ሲሚንቶ ያስፈልጋታል ብለዋል።
በአቅርቦት እና ፍላጎት መካከል በትንሹ ሦስት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የሚሆን ክፍተት እንዳለ እና ይህንንም ለመሙላት በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወር የተመዘገበው ለውጥ በቂ ባይባልም ጥሩ ጅማሬ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በክረምት ምክንያት ስራ ያቆሙ ፋብሪካዎች እንደነበሩና መንገዱ በክረምት አመቺ ባለሆኑ ምርት ለመቀነሱ ምክንያት እንደሆነ እና በአሁኑ ጊዜም ችግሩ እንደተፈታ ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ ክረምት ወቅትም ከፍተኛ ዝናብ ስለጣለ ደርባ እና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የመሬት መንሸራተት ከፍተኛ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበርና ይህም ችግር ለምርት መቀነሱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
የሲሚንቶ 90 በመቶ ድርሻ የሚወስደው ላይም እስቶን የተባለውን ምርት ለማዘዋወር የሚጠቀሙበት በቤልት እንደሆነና በጎርፍ ምክንያት የደርባ እና ሙገር ሲሚንቶ ማጓጓዣ ቤልት ተበጥሶ እንደነበርና እሱን በጊዜያዊ ሁኔታ ለመጠገን ከአንድ ወር በላይ እንደፈጀም ጠቅሰዋል።
በደርባ ሲሚንቶ ላይ ደግሞ በድልድይ ላይ የሚያልፍ ቤልት እንደተበጠሰ እና ለመጠገን ብዙ ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅሰው በጊዜያዊነት ግን ምርት እንዳይቋረጥ ከፍተኛ ሥራ እንደተሰራ ገልፀዋል።በቀጣይም ሙሉ ጥገና እንዲያገኙ የመሬቱ ሁኔታ ተጠንቶ ሥራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም የዘርፉ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ልማት ተቋሙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በጋራ በመሆን በየቀኑ ምርት እንዳይቆም የክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፀጥታ ሁኔታውንም በተመለከተ እንዲሁ ከክልሎችም ጋር በመሆን የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።በቀጣይ ወርም ደረቅም ከመሆኑ አንፃር የሲሚንቶ ምርት ጭማሪ ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ስመኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!