የእለት ዜና

የምሽት መዝናኛ ቤቶች መነቃቃት ከኮቪድ 19 ማግስት

Views: 742

አዲስ አበባ ካዛንችስ አካባቢ ከሚገኙ የምሽት ቤቶች ውስጥ በአንዱ ተገኝቻለሁ። በቤቱ ውስጥ ያሉ አገልጋይም ሆነ ተገልጋዮች ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ፤ በእዛች የበሬ ምላስ በምታክልና የተፋፈነች ጠባብ ቤት ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝ ጉዳይ ፈፅሞ የተረሳና ማንም ቁም ነገሬ የሚለው ጉዳይ ላለመሆኑን ምስክር ነው። በቤቷ ውስጥ ያለው ሰው፤ ሁሉም በራሱ ዓለም ገብቶ ይዋዥቃል። ገሚሱ ጥጉን ይዞ በተመስጦ ይጠጣል፣ ገሚሱ መሀል ገብቶ ይደንሳል ሌላው ደግሞ በስካር ወጀብ ተንሳፎ እየተቃቀፈ እየተሳሳመ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያወራል። የፍትወት ስሜቱን ሊያስደስት የሻተም በቤቱ ውስጥ ካሉ ሴቶች ጋር ይስማማል፣ ይጨቃጨቃል።

ራሄል (ስሟ እንዲገለፅ ባለመፈለጓ የተቀየረ) ጠይም፣ ቁመቷ አጠር ያለና ሰውነቷ ሞላ ያለ ወጣት ነች። ከየጥጉ በደብዛዛው ቤት ላይ የሚረጨውም አብረቅራቂ ብርሀን ‹‹ዲም ላይት›› የደስ ደስን ጨምሮላታል። ጡት ማስያዣ አይሉት ቲሸርት በውል የማይለይ ጠቆር ብሎ ነጭ አበቦች ጣል ጣል ያሉበት ጨርቅ ቢጤ ከላይዋ ጣል አድርጋ፤ አጭር ጅንስ ቁምጣ ከስር ለብሳለች። በመጠጥ ቤቱ ከወዲህ ወዲያ ስትንቀሳቀስ በዙሪያዋ ያሉ ወንዶ ከእርሷ ጋር አብረው ወዲህ ወዲያ ዐይናቸው ይከላወሳል። ‹‹ደንበኛ ለመሳብና የተሻለ ቢዝነስ ሠርቶ ለማደር ነው እንደዚህ አይነት ልብስ የማዘወትረው›› ትላለች የልብሷን ማጠር ምክንያት ስትገልፅ።

እኔም ከተቀመጠችበት የምሽት ቤቱ አንደኛው ጥጋት ጠጋ በማለት ወንበር ስቤ ተቀመጥኩኝና ‹‹እንዴት ነሽ?›› በማለት ሰላምታዬን አቀረብኩላት። ‹‹አለሁ ይመስገነው›› አጭር መልሷ ነበር። ትንሽ ኮስተር ብላ ነበርና የመለሰችልኝ ጨዋታዬን ለመቀጠል ፈራሁ። ቢሆንም ግን ከምሽት ቤቱ የተገኘሁበትም ሆነ እርሷን የቀረብኩበትን ዋንኛ ዓላማ በማሰብ ጨዋታዬን በመቀጠል ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄዬን አስከተልኩኝ።

‹‹ይመስገነው ነው፤ ይኸው እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድር! እንደ ድሮው ባይሆንም እየሠራን ነው።›› ስትል መለሰችልኝ። ‹‹የኮሮና ስጋት በቃ እዚህ ቤት አይታሰብማ?›› ቀጣይ የመግባቢያ ጥያቄዬ ነበር።

‹‹እና ምን ይደረግ? ተፈርቶ አይቻል! እንጀራስ በምን ይበላል? ሰዉ ደግሞ አሁን አሁን መስሚያውን እየደፈነ ነው›› አለችኝ ግድ የለሽነት በተሞላበት ስሜት። አክላም ‹‹ምን አዳር ነው ወይስ ጊዜያዊ የፈለከው?›› በማለት በእጇ የያዘችውን ሲጋራ በረጅሙ ምጋ ወደላይ አጎነችው።

እኔም ወዲያው ፈገግ በማለት ጋዜጠኛ እንደሆንኩኝና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባልጠፋበትና አሁንም ስጋቱ ባልቀነሰበት ጊዜ የምሽት ጭፈራ ቤቶች መነቃቃት ምን ይመስላል? ሥራቸውንስ በምን አይነት መልኩ እያስኬዱት ይገኛሉ? በሚል ጉዳይ ላይ አንድ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ዳሰሳ እያደረኩኝ እንደሆነ ነገርኳት። አንዳንድ ጥያቄዎችን ልጠይቃት እንደፈለኩኝ በመግለፅም ፍቃደኝነቷን ጠየኩኝ።

‹‹ኦ…. ሰውዬ እኔ እዚህ ለቢዝነስ ነው የመጣሁት! ያንተ ኢንተርቪው ዳቦ አያበላኝ….! ደግሞስ ምን ይሠራልሃል ስለ እኛ ሕይወት ማወቁ›› ብላ መሰላቸት በተሞላበት መንፈስ ከእግር እስከ እራሴ ተመለከተችኝ። እኔም ፈጠን ብዬ ‹‹አይ ስለ እናንተ ሕይወት ሳይሆን በአጠቃላይ በምሽት ቤቱ በኮሮና ወቅትና በአሁን ሰዓት ያለው እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ነው ማወቅ የፈለኩት›› ስል ትህትና በተሞላበት መንፈስ መለስኩላት።

‹‹እኔ ምንም አልናግርም አባቱ! እንደዚህ አይነት ነገር አይመቸኝም። ምን ይሠራልኛል? ባወራው ምንም ትርጉም ስለሌለው ይለፈኝ።›› ብላ እኔን ፊት በመንሳት ከያዘችው ሲጋራ ጋር የተመስጦ ጨዋታዋን ቀጠለች። ከዛም እንደምንም ብዙም ጊዜ እንደማልሰስድባትና ስሟ ጽሑፉ ላይ እንደማይገለፅ በመንገር በተጨማሪም እርሷ የምትሰጠኝ መልሶች ለጽሑፉ ጥሩ ግብአት ሊሆኑ እንደሚችሉ በመለማመጥ መልኩ አስረድቼ እንድትተባበረኝ አግባባኋት።

ይሁንታዋን ሳገኝ ለኔም ለእርሷም ቢራ አዘዝኩኝና ቢራችንን ይዘን ከጠባብዋና በሰዎች ከታጨቀችዋ ቤት በመውጣት በረንዳ ላይ በመቀመጥ ጨዋታችንን ቀጠልን። እንዴት ወደዚህ ሥራ ልትገባ እንደቻለችና ምን ያህል ጊዜ በዚህ ሕይወት እንደቆየች ጠየኳት። እርሷም አጠር አድርጋ አጫወተችኝ።

ተወልዳ ያደገችው ባህርዳር ነው። እስከ ዐስረኛ ክፍል ድረስ በትውልድ አካባቢዋ የተማረች ሲሆን የዐስረኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናን ባለማለፍዋ የተለያዩ ሥራዎችን በአካባቢዋ ለመሥራት ብትሞክርም ሳይሳካለት ቀርቶ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በ20 ዓመቷ ወደ አዲስ አበባ ሥራ ፍለጋ በማለት መጣች።

አዲሳ አበባ ከገባችም በኋላ ለኹለት ዓመታት በአንድ ሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት ትሠራ የነበረ ሲሆን፣ ድሮ በባህር ዳር ሳለች የምታውቃትና በዚሁ በወሲብ ንግድ (ሴተኛ አዳሪነት) ሕይወት ላይ የምትገኝ አንድ ጓደኛዋ ወደዚህ ሥራ ሳታስበው ጎትታ እንዳስገባቻችም ገለፀችልኝ።

ከዛ ጊዜ አንስቶም ለስድስት ተከታታይ ዓመታት የቤት ኪራይዋን የምትከፍልበት፣ የአልባስና የእለት ወጪዋን የምትሸፍንበት፣ ከዛም አልፎ ተርፎ ትንሽዬ ገንዘብ ለቁጠባ ወደ ባንክ የምትወረውርበትና ለቤተሰቦቿም አነስተኛ ድጎማ የምትልክበት ቋሚ ሥራዋ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘለቀ።

ኮሮና ወደ አገራችን ከገባ በኋላ ግን ይሄ ሁሉ እንደቀረ የምታስረዳው ራሄል፣ በኮሮና ወረርሺኝ ሳቢያ እንቅስቃሴዎች በመገታታቸውና መጠጥ ቤቶችና መሰል አገልግሎት መስጫዎች በመዘጋታቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጣ እንደቆየች ትናገራለች።

የዚህችን ወጣት ሕይወት ያለምክንያት አይደለም ያነሳነው። እንደ ራሄል ሁሉ በተለያዩ የምሽት መዝናኛ ቤቶች ውስጥ በመሥራት ኑሯቸውን የሚገፉ፣ ቤተሰቦቻቸውን የሚደጉሙና እልፎ ተርፎም ትንሽም ብትሆን ለቀጣይ ሕይወታቸው ጥሪትን የሚያስቀምጡ ጥቂቶች አይደሉም።

በአንድ የምሽት መዝናኛ ቤት በዚሁ ሥራ ብቻ ሳይሆን በአስተናጋጅነት፣ በባር-ቴንደር (የመጠጥ ቀጂነት) እንዲሁም በአልጋ ክፍል ኃላፊነትና በፅዳት ሠራተኝነት የሚሠሩ ብዙ ሠራተኞች አሉ። ታዲያ እኚህ ሠራተኞች በኮቪድ 19 ሳቢያ እንቅስቃሴዎች በተገቱበትና የመጠጥ ቤቶችም ሆነ ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተዘጉበት ወቅት ከፍተኛ ለሆነ ችግርና እንግልት ተዳርገው የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥለው የነበሩ ክልከላዎችና ግዴታዎች በተወሰነ መልኩ በመነሳታቸው በትንሹም ቢሆን ከችግራቸው ተንፈስ እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ምሽት ቤቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት
የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ አገራት ከባድ ሥጋት ላይ ወድቀው ሰንብተዋል። የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችንም ወስደዋል። አሁንም ድረስ በአንዳንድ አገሮች ውሳኔዎቹ እየተወሰዱ ይገኛሉ።

በአገራችን ኢትዮጵያም በአምልኮ ስፍራዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ ፍርድ ቤቶች በከፊል ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላትም ቀድሞ ይጭኑት ከነበረው የሰው ቁጥር ቀንሰው እንዲጭኑ ተገደዋል። በተጨማሪም የምሽት መዝናኛ ቤቶችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት እንዲዘጉ ተወስኖ መዝጊያቸውን ከርችመው ሰንብተዋል። በቅርቡ እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ መልካቸው እስኪመለሱ ድረስ።

ዘላለም አበራ መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው ‹‹ባክ ያርድ›› ባርና ሬስቶራንት ውስጥ በማናጀርንት ይሠራል። በኮሮና ሳቢያ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከትሎም በሬስቶራንቱ ጥንቃቄ የተሞላበት አገልግሎት መስጠት እንደቀጠሉና በባሩም ጥቂት ደንበኛ የነበሩ ሰዎች ይመጡ እንደነበር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ያስታውሳል።

ይህም ከፍተኛ የሚባል የኢኮኖሚ ክስረት እንዳስከተለባቸው የሚገልፀው ዘላለም፣ አሁን ግን ገደቡ በመነሳቱ ምክንያት በደንብ እየሠሩና ተጠቃሚም በገፍ እየመጣ እንደሚገኝ ገልፆ አንዳንድ ጊዜ እቤቱ ከአፍ እስከ ደፉ ጢም ብሎ ሊሞላም እንደሚችል ይናገራል።

‹‹በኮቪድ ወቅት ሙሉ ለሙሉ የባህል ቤታችንን ዘግተን ነበረ።›› የሚለው ደግሞ ሲ.ኤም.ሲ በተለምዶው ወሰን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የ‹‹ሀ ግዕዝ›› የባህል ምሽት ቤትና የፍሬ ባርና ሬስቶራንት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ስዩም አባተ ነው። እንደ ስዩም ገለፃ ከሕግ አኳያም ሆነ የደንበኞቻቸውንና የሠራተኞቻቸውን ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃር የባህል ቤቱ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ሬስቶራንቱ ሥራ አለማቋረጡን ያስረዳል።

‹‹ያም ቢሆን ግን›› ይላል ስዩም ‹‹ያም ቢሆን ግን ሥራው እጅግ በጣም የሞተ ነበር። አንደኛ ሰው ለራሱ ይፈራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወንበር ስናስጠቅም የነበረው በአንድ ጠረጴዛ ላይ አንድ ሰው ስለነበረ ገቢያችን በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳበት ሰዓት ነበር።›› በማለት በኮሮና ምክንያት ደርሶባቸው የነበረውን ኪሳራ ይገልፃል። አሁን ግን እንደ ቀድሞው ጊዜ ባይሆንም በአንፃራዊነት የተሻለ ሥራን እየሠሩ እንደሚገኙም ጨምሮ ያስረዳል።

የምሽት ቤቶች – ሠራተኞቻቸውን ከመደገፍ አኳያ
ታሪኩ አሰፋ መስቀል ፍላወር አካባቢ ከሚገኙ የምሽት መዝናኛ ቤቶች ውስጥ አንዱ በሆነው ‹‹ቪላ ቨርዲ›› ውስጥ በባር-ማንነት ይሠራል። በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እንቅስቃሴዎች በመታገዳቸውና የሚሠራበትም ባር በመዘጋቱ እርሱ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡም ጭምር ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና አድርሶባቸው እንደነበር ይገልፃል።

‹‹የቤት ኪራይ ለመክፈል፣ የቤተሰብ የአስቤዛ ወጪን ለመሸፈንና ለመሳሰሉት ጉዳዮች የምከፍለው እስካጣ ድረስ በጣም ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። በዛ ላይ ሦስት ልጆች አሉኝ። እነሱን ይዞ ስድስት ወርን ያለገቢ መኖር በጣም ከባድ ነበር። የቤተሰብ ወጪን ለመሸፈንም ትንሽ የባንክ አካውንቴ ውስጥ ያጠራቀምኳት ገንዘብ ስለነበረችኝ ያቺ ስጠቀም ቆየሁ። እርሷ ስታልቅ ደግሞ ቤተሰብ እጅ ላይ ነው የወደቅኩት።›› በማለት በጊዜው ደርሶበት የነበረውን ከፍተኛ ችግር ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል።

በመግቢያችን ያነሳናት ራሄልም የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱና ትሠራበት የነበረው የምሽት ቤት በመዘጋቱ ሳቢያ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጣ እንደነበር ትገልፃለች።
‹‹የምሽት ቤታችን እንደተዘጋ ለአንድ ኹለት ወር ባንክ ውስጥ የቆጠብኩትና ለአንዳንድ ሰዎችም ያበደርኩት ገንዘብ ስለነበር እርሱን እየተጠቀምኩኝ ቆየሁ። ከኹለት ወራት በኋላ ግን የቤት ኪራይ የምከፍለው ቀርቶ የምበላው እስካጣ ድረስ ተቸግሬ ነበር። ነገር ግን በዚህ ሥራ የማውቃቸው ሰዎች ጋርም ሆነ ጓደኞቼ ጋር እየደወልኩና ገንዘብ እየተበደርኩ እዚህ ደረስኩ።›› በማለት ወቅቱን በከባድ ፈተና ውስጥ ሆና እንዳሳለፈችው ትናገራለች።

‹‹ምንም የባህል ቤቱ ጠባብ ቢሆንም ከዘፋኞች ጨምሮ ወደ ኻያ የሚጠጉ ሰዎችን እናስተዳድራለን›› የሚለው ደግሞ ስዩም ነው። ስዩም አክሎም ‹‹እውነት ለመናገር የባህል ሙዚቃ ተጨዋቾቹንና ባንዱን ምንም አልደገፍንም። ግን ሠራተኞቻችን ከሥራ ገበታቸው ሳናፈናቅል፤ ተወያይተን የደሞዝ ጉዳይ ላይ አስተያየት አድርገናል። ዘፋኞቹን ግን ምንም አላገዝናቸውም ነበርና ተበተኑብን። አሁን ደግሞ ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት እየተመለሱ ሲሄዱ ተመልሰው ስለመጡ ተቀብለናቸው በጥሩ ሁኔታ እየሠራን እንገኛለን።›› በማለት ሠራተኞቻቸውን ሙሉ ደሞዝ ባይከፍሉም እንኳን በተቻለ አቅም በተወሰነ መልኩ እየደጎሙ አብረው ቆይው ዛሬ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ የመመለስ አቅጣጫን ይዘው እየሠሩ እንደሚገኙ ያስረዳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትና የምሽት ቤቶች መነቃቃት
ምንም እንኳን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአገራችን እየጨመረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተወሰዱ እርምጃዎች ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በመድረሱ እና ወረርሺኙ ከኛ ጋር ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ከመሆኑ አንጻር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥለው የነበሩ ክልከላዎችና ግዴታዎች በተወሰነ መልኩ እንዲነሱ ተደርገዋል።

ታዲያ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ሰፊው የማኅበረሰብ ክፍል የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ሲቀጥሉ ቀድሞ በነበረው ሁኔታ ሳይሆን አሁንም ትልቅ የኅብረተሰብ ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 መከላከልን ታሳቢ ባደረገና ኅብረተሰቡን በማያጋልጥ መልኩ ማከናወን እንደሚጠበቅበባቸው የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለያዩ ጊዜያት ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።

ካሳለፈውነው ዓመት 2012 ክረምት የቡሄ በዓል ወዲህ ኮሮና የሚያደርሰው ተፅእኖ እያነሰ መምጣቱንና የሰዉም ፍራቻ እየቀነሰ በመሄዱ የምሽት ቤት ሥራቸውን እንደ ጀመሩ የሚገልፀው ዘላለም ነው። እንዲህም ይላል ‹‹መንግሥት በድጎማ ሊቀጥል አልቻለም። መጠጥ ቤቶች ብቻ ሳይሆን ከመጠጥ ቤቱ ጋር በተጓዳኝ የሚሠሩ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ‹‹ጀብሉ›› ወይንም ሱቅ በደረቴዎችና መሰል አካላት አሉ። እነሱም ከእኛ ሥራ ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለዚህ ሁሉንም ደግፎ መንግሥት መያዝ አልቻለም።

በተለያዩ የምሽት ቤቶችም ሆነ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራቸውን መቀጠላቸውን ፖሊስ እያየም ዝም እያለ መጣ፣ ተጠቃሚው ደግሞ ፍራቻው እየቀነሰ ሄደ፣ የመጠጥ ቤት ባለቤቶችም ይሄን እያዩ አንዳንድ ለጥንቃቄ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ሥራውን ጀምረውታል። በአሁኑ ሰዓት ወደኛ ቤትም ከኮሮና በፊት እንደነበረው ባይሆንም ሰዎች እየመጡ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜም ለውጥ አለ።›› ሲል ያስረዳል። ያም ሆኖ ግን የመጠጥ ቤት ሥራ ከኮሮና ባህሪ ጋር እንደማይሄድ ሳይደብቅ ነገር ግን በአጠቃላይ በሁሉም ቦታዎች ላይ ወረርሽኙ እየተረሳና የምሽት መዝናኛ ቤቶችም ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ይገልፃል።
‹‹የባህል ቤቱን ሥራ የጀመርነው የዘመን መለወጫ እለት ነው። ያው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ቡሄ አለቀ፤ ከዛም የዘመን መለወጫ መጣ። እኛም ከአዲስ ዓመት ጀምሮ እየሠራን ነው ያለነው። ነገር ግን የደንበኞቻችን ቁጥር ድሮ የነበረውና አሁን ያለው በጣም ይለያያል።›› የሚለው ደግሞ ስዩም ነው።

ስዩም የተጠቃሚዎች ቁጥር የመቀነሱንም ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ይላል ‹‹አንደኛ ነገር ኮቪድ 19 ያመጣው ተፅእኖ ነው። ኹለተኛ ደግሞ አገራዊ ጉዳይ አለመረጋጋቱም አለ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ድሮ ለሊት እንሠራ ነበር። አሁን ላይ እስከ አራትና አምስት ሰዓት ብቻ ነው የምንሠራው። ያውም ወጣቱ ነው የሚመጣው። ትልቅ ሰዎች አሁን ላይ አናገኛቸውም።

በፊት ደንበኞቻችን ሚስትና ልጆቻቸውን ይዘው እስከ ስድስትና እና ሰባት ሰዓት ድረስ በቤታችን ይቆዩ ነበረ። አሁን ላይ ግን ያ የለም። ከወቅቱም የፖለቲካ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሥራችን እጅግ በጣም የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ነው ያለው።›› በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ ያለውን የባህል ቤታቸውን የሥራ ሁኔታ ያስረዳል።

የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ምን ይመስላሉ?
የኮሮና ወረርሽኝ ከሌሎች በሽታዎች የሚለይበት አንደኛው ምክንያት የስርጭት ፍጥነቱ ከፍተኛ መሆኑና መድኃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘለት ወረርሺኝ መሆኑ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በወረርሺኙ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪና ግንኙነት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሁሉ የሚያጠቃ በሽታ በመሆኑ ነው። የአንድ በቫይረሱ የተያዘ ግለሰብ አለመጠንቀቅ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ሁሉ በወረርሽኙ እንዲያዙ የማድረግ እድልን ያሰፋዋል።

ታዲያ የወረርሺኙን መስፋፋት ከሚያባብሱና ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአንድ ተሰብስበው ከሚገኙበት ስፍራዎች ውስጥ አንዱ የምሽት የመዝናኛ ቤት ነው። አዲስ ማለዳም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ተከትሎ ሥራቸውን የጀመሩት የምሽት የመዝናኛ ቤቶች የወረርሺኙን ሥርጭት ለመቀነስ ምን አይነት ጥንቃቄዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ ጠይቃለች።

የኮሮናን ወረርሺኝ ሥርጭት ለመግታት በባርና ሬስቶራንቶች ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል የሚለው የ‹‹ባክ ያርድ›› ማናጀር ዘላለም አበራ፣ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን እንዲህ ይዘረዝራል። ‹‹አንደኛ የመጠጥ እቃዎቹን እንቀቅላቸዋለን ሼከር፣ ሎሚ መጭመቂያ፣ ብርጭቆና የመሳሰሉት እቃዎች ታጥበው ይቀቀላሉ። ሠራተኞች በየሰዓቱ በሚገባ እጃቸውን ይታጠባሉ፣ ማስክ የማድረግም ግዴታ አለባቸው፣ በየጠረጴዛውም አንዳንድ ሳኒታይዘር እንዲቀመጥ ተደርጓል በተጨማሪም በር ጋር ጥበቃው የሙቀት መለኪያ እንዲይዝ ተደርጓል።›› በማለት ያስረዳል።

የባር-ማንነት ሥራዉን ዳግመኛ ከጀመረ አንድ ወር ከ15 ቀኑ እንዳስቆጠረና የምሽት ቤቱ ግን ቀደም ብሎ እንደጀመረ የሚገልፀው ታሪኩ ደግሞ፣ በሚሠራበት ባር ውስጥ ያለውን የጥንቃቄ ሁኔታ ሲገልፀ እንዲህ ይላል። ‹‹ሰዉ ወደ ምሽት ቤቶች ዳግመኛ በብዛት መምጣት ጀምሯል። ሥራ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ወደ ባራችን የሚመጣው ሰው ቁጥር ወቅቱን ጠብቆ አንዳንዴ ከፍ ይላል አንዳንዴ ዝቅ ይላል። በኮቪድ ምክንያት እጅግ ተቀዛቅዞ የነበረውም ገበያ አሁን አንፃራዊ ለውጥ እየታየበት ነው።

ነገር ግን እኔ አሁን እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው፣ ምንም የምጠነቀቀው ጥንቃቄ እንደሌለ ነው። ምክንያቱም የሚመጣውም እንግዳ በባዶ ነው የሚመጣው ስለዚህ በተቻለ መጠን ቶሎ ቶሎ እጄን ለመታጠብና ሳኒታይዘር ለመጠቀም እሞክራለሁ እንጂ ማስክና መሰል ቁሳቁሶችን አልጠቀምም። አሁን ምንም ጥንቃቄ የለም። የባሰ ነገር ነው ያለው።›› ሲል ይገልፃል።

የ‹‹ሀ ግዕዝ›› የባህል ምሽት ቤትና የፍሬ ባርና ሬስቶራንት ባለቤትና ማናጀር ስዩም አባተ ደግሞ እንዲህ ይላል፤ ‹‹እኛ አሁንም ቢሆን ሰው እራሱን ጠብቆ እንዲያስተናገድ ነው የምንለው። ምክንያቱም አንደኛ ነገር የኛ ጥንቃቄ ለደንበኛም መልካም ነው ደንበኛ እራሱ ጥንቃቄህን ሲያይ ነገ ተመልሶ ይመጣልሃል። እራሱን የሚጠብቅ ለሰው ሕይወት ሀላፊነት የሚሰማው ደንበኛም አለ።

ቢሆንም ግን አንዳንድ ሰዉ ትንሽ ከጠጣና ሞቅ ካለው በኋላ አንተ እንደምትለው አይሄድልህም። ድብልቅልቁ ይወጣና አንተም መቆጣጠር ይከብድሃል። በዚህ መካከል እንደፈለገ ትልና አንተም የራስክን ጠብቀህ ዝም ትላለህ። እና የኮሮና ጉዳይ በተለይ ለሊት ላይ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። እርቀቱን እንዲጠብቅ የጥንቃቄ መርሆዎችን እንዲከተል ማድረግ ለሊት ላይ አትችልም። እሱ እሱ ነገር ትንሽ ማነቆ ነው።›› በማለት የጥንቃቄው ነገር ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ያስረዳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com