ከጋሞ ምድር – ኤዞ ከተማ የተቀዳ ማስታወሻ

Views: 340

እንግዳቸውን ለይተው ያውቃሉ። በመተላለፊያ መንገዶች ላይ ‹አሻም!…አሹ!› ይላሉ፣ ወንዶቹ ባርኔጣቸውን ከፍ አድርገው ይዘው ከአንገታቸው ዝቅ ሲሉ፣ ሴቶችም የደረቡትን ነጠላ ከራሳቸው እያሸሹ። ሞቅ ያለ አቀባበላቸውና ፈገግታን የተሞላ ገጻቸው፣ የከተማዋን ቀዝቃዛ አየር ያስረሳል፤ ያሞቃል። ቤታቸውን ለእንግዶች ጥለው፣ የጓዳውን ምግብ ሳይሰስቱ አቅርበው፣ እንደ ‹እናት› በስስት እያስተናገዱ ነው የተቀበሉን፣ ያቆዩንም።

ኢትዮጵያዊ ሆኖ ይህን ዓይነት ኹነት የት አካባቢ ሊታይ ይችላል ብሎ መጠየቅ ጨዋነት ነው፣ በአራቱም አቅጣጫ ይህ መልካምነት ይገኛልና። በመንፈስም በአካልም ከመጥበብ ተላቅቆ አሻግሮ ለቃኘ፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ ተስፋን የሚያለመልሙ፣ የሰውነት ከፍታን የሚያስታውሱ፣ ሐሜታውንና የከተማ ንትርኩን፣ ሽሚያና ግብግቡን የሚያስረሱ አካባቢዎች፣ መልክዓ ምድሮች፣ ማኅበረሰቦች፣ ኅብረቶች እና ብዙ ነፍሶች ይገኛሉ።

አሁን የምነግራችሁ ግን፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ 45 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ኤዞ ከተማ የሆነውን ነው። ከመኻል አገር ሸገር አንስቶ፣ አርባምንጭ ከተማ አሳድሮ ማለዳ ኤዞ ከተማ ያዘለቀን ጉዞ ምክንያቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር ነው። በተያያዘም በኤዞ ከተማ እና አልፎ በምትገኘው ብርብር ማርያም ገዳም አካባቢ የሚከፈቱትን የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ለመመረቅ።

በኤዞ ግዙፍ ሆቴል ማግኘት አይቻልም። ለማደሪያ አልጋ የሚፈልጉ እንግዶች ቢኖሩ እንኳ፣ ነዋሪው ከየቤቱ መኝታ ይሰጥ ይሆናል እንጂ ማረፊያ ቤቶች አይገኙም። ምንአልባት ጥቂት ኪሎትሮችን ተመልሶ ወደ ጨንቻ ከተማ ማምራት የግድ ሊል ይችላል። ነገር ግን በቀርከሃ አጥር የተከበቡ የኤዞዎች መኖሪያ ቤቶች በራቸው አልተዘጋም፣ አይዘጋም። ልባቸው በከተማ ካሉ ግዙፍ ሆቴሎች ይልቃል።

‹ግቡ!› ይላሉ። ‹አሹ ሰሬ ኡደታ› የሚል ቃል ከአንደበታቸው ሲወጣ ገጻቸው ንጹህ ፈገግታን ተመልቶ ነው፤ ‹እንኳን ደኅና መጣችሁ› ሲሉ። ከአልጋቸው ለቀው፣ ከቤታቸው ወጥተው፣ ‹ለከተማ ሰው› እንዲመች በአቅማቸው አሰናድተው ማረፊያ ይሰጣሉ።

ይህ የሰማነው ሳይሆን ያየነው እውነት ነው። ንጹህ አንሶላ አንጥፈው፣ ከልብስ ሳጥኑ ያለውን ጋቢና ብርድ ልብስ ሁሉ አውጥተው፣ ‹ይህን አትንኩ! ያንን አትክፈቱ! አታቆሽሹ! እታጥፉ! ቆልፉ!› ሳይሉ ቤታቸውን ትተዉልን ለቀናት የቆዩ ሰዎችን ዐይተናል። እንዲህ ጭንቅ በበዛበት ዘመን፣ በረሃ ላይ የተገኘች ጠብታ ውሃ ያላትን ዋጋ ያህል ነው፤ ይህ በጎነት።

ኤዞ ከተማ
ጋሞ። ኢትዮጵያ ደጋግሞ ስቅ የሚላት ብትሆን፣ ጋሞን ብትጠራ አይለቃትም ብላችሁ ነው! ጋሞዎች ሰርክ ዜማቸው፣ የምርቃት ቃላቸው ማቀፊያ ኢትዮጵያ ናትና። ኤዞ የጋሞ ፍልቃቂ ናት። በጋሞ ዞን ከሚገኙ አራት ወረዳዎች መካከል አንዷ በሆነችው ቆጎታ ወረዳ፣ እንደ ማእከል ሆና ታገለግላለች። የወረዳው ከተማ እንድትሆን የተወሰነውና መገኛ ወረዳዋም ‹ቆጎታ› የሚለውን ሥያሜ ያገኘው የካቲት 20 ቀን 2011 ላይ ነበር፤ በቅርቡ።

በወረዳው ለሚገኘው ነዋሪ ግብርና ዋና መተዳደሪያ ሲሆን፣ ንግድና እደጥበብም አካባቢው መናኽሪያቸው ነው። ከከተማዋ ብዙም ሳይርቅ ደግሞ አፕል ወይም ፖም በስፋት ይመረታል። የአርባምንጭ መልከኛ ሙዞችም ከመኻል ከተማ ቀድመው ወደ ኤዞና ዙሪያዋ ይደርሳሉ።

መምህር ማዳ አንዳርጌ ተወልደው ያደጉት በዛው ኤዞ ከተማ ነው። ትምህርታቸውን አርባ ምንጭ እንዲሁም ከኤዞ አለፍ ብላ በምትገኝ ጨንቻ በምትባለው ከተማ ተምረዋል። በጥቂቱም ቢሆን ስለኤዞ ከተማ ምሥረታና ቀደም ስላለው ታሪኳ አጫውተውናል።

‹‹ድሮ ገበያ ነበር።›› ሲሉ ጀመሩ። ከገበያዎቹ መካከልም ቦንደላ ጊያ፣ ነጋሳ ጊያ፣ ዶርጎ ጊያ፣ ኦልዶ ጊያ፣ ጋሻጌ ጊያ የሚባሉ አሉ (እነዚህ ሥያሜዎችን በሚመለከት፣ ቅላጼን ተከትሎ የቃላት አጠራር ልዩነት እንደሚኖር ልብ ይሏል!)። ‹ጊያ› የሚለው ቃል ገበያ እንደማለት ነው። ታድያ እነዚህ በኤዞ ከተማ ዙሪያ የነበሩ ገበያዎች ተሰባስበው ሐሙስ ገበያን መሠረቱ። ሐሙስ ገበያ አሁንም ድረስ በኤዞ የደራና የደመቀ ገበያ ሲሆን፣ እሁድ ማለዳ ደግሞ የሸማና ነጠላ ገበያዎች በድምቀት ይታዩባታል።

ወደ ኤዞ ለመግባት አራት በሮች ነበሩ ያሉት መምህር ማዳ፣ በአካባቢው የአጼ ምኒልክ የጦር ሠራዊት እንደነበርም ያወሳሉ። ይህንንም ተከትሎ የንግዱን ጨምሮ በአካባቢው የነበረው እንቅስቃሴ ሊደምቅ ችሏል ሲሉ ከሚያውቁት ታሪክ አካፍለዋል። ታድያ የኤዞ ከተማ ሕዝብ በቀደመው ጊዜ ‹ዳውንቶ› ይባል እንደነበርም አጫውተውናል።

በጉዞ መካከል
ከኤዞ አልወጣንም። ከኤዞ ሆኖ በዙሪያ ያለው መልክዓ ምድር ቁልጭ ብሎ ይታያል። ደመና ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደላይ እንደሚያርግ ዓይነት፣ በርቀት የተሳሉ ከሚመስሉ ባለአረንጓዴ ምንጣፍ ተራሮች መካከል ያታያል።

ረዘም፣ ጠየም ያሉ፣ ነጠላ የማይለያቸው የኤዞ ከተማ ነዋሪዎች ፈገግታቸው አድሮ አልደበዘዘም። ሕጻናቱም የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ከተከፈተበት አካባቢ እንዲሁም የመጻሕፍትና የፎቶ አውደርዕይ ከቀረበበት ድንኳን አልራቁም። ይልቁንም መርሃ ግብሩን ምክንያት አድርገው ለንባብ የሚሆኑ ቁሳቁሶችና መጻሕፍትን ሸክፈው ከሄዱት መካከል አንዱ ከሆነው ‹ኢትዮጵያን ሪድስ› የሕጻናቱን ትኩረት የሚስቡ የልጆች መጻሕፍትን በማንበብ፣ በማስነበብና ለጨዋታዎች በመጋበዝ ያደረገው እንቅስቃሴ ቀልባቸውን ስቦታል።

ውር ውር ከሚሉት ሕጻናት ባልተናነሰ የሞተር ሳይክሎች ከኤዞ ወደ ጨንቻና አካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ደጋግመው መንገዱን ይመላለሱበታል። በቅጡ ያልተሠራው ጠጠራማ የሆነው መንገድ እግረኛውንም፣ ሞተረኛውንም ለማስተናገድ በቂ ነው። በከተማዋ ፊልምና ሙዚቃ፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ዝማሬዎችን የሚሸጡና በሞባይልና መሰል መጠቀሚያዎች የሚጭኑ ቤቶች ይበዛሉ።

ወደ አንድ ጠጅ ቤት ጎራ አልን። ለጨዋታም፣ ሐሳብ ለመቃረምም። በአርባምንጭ እና ኤዞ ከተማ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ትስስርን አንስተን ካየነው ከታዘብነው በመቀባበል የጨዋታችን ርዕሰ ጉዳይ አደረግነው። ወጣቱ ጠጅ ቀጂ ታድያ ሲሰማን ቆይቶ ኖሮ፣ በጨዋታችን መካከል ገባ። ‹‹እዚህ ነው የተወልድኩትና የኖርኩት፣ እስከ አሁን ግን አርባምንጭን አላውቃትም።›› አለ።

የአርባ ምንጭ መገኛ ከኤዞ ሃምሳ በማይሞላ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነውና፣ ነገሩ ሳይገርመን አልቀረም። የባሰው ግን ቀጥሎ የተናገረው ነው። ‹አዲስ አበባን ግን በደንብ አውቃታለሁ።› አለ። በልጅነቱ ከቤተሰቡ ተነጥሎና ለሥራና ትምህርት ብሎ አዲስ አበባ መቆየቱን ይሄኔ አጫወተን። በዛም ያሰበው እንዳልሆነና ብዙ እንደተንገላታ፣ የልጅነት እድሜው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተራግፈው እንዳለፉ አስታወሰ።

እርሱ ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ የሕይወት ገጠመኝ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ተመልክተናል። ይህ ወጣት ታድያ አሁን ወጣትነቱን በሥራ ይዞታል፤ እየተጠቀመበት ነው። አዲስ አበባ የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው ከንግግሩ ያስታውቃል። ተሻግሮ ሸገርን ከማየቱ በላይ ግን ቅርቡ ያለችውን አርባምንጭን አለማወቁን ደጋግሞ ሲናገር፣ ጉዳዩ እንደሚከነክነው ገብቶናል።

እንዲያ ያለ መልክዓ ምድር፣ እንዲያ ያለ ቀና እና ደግ፣ ታታሪ ሕዝብ ስንመለከት፣ እንደ አገርም ያለንበትን ደረጃ ስንቃኝ፤ እንደ ሕዝብ የምንወቀስበትን አመላችንን ልብ ስንለው፣ ሁሉም የእኛ ሆኖ ግን ምንም የሌለን እንደሆንን ሹክ ይሉናል። እንደ አገር ከሠራነው ይልቅ ያልሠራነው፣ ከሌለን ይልቅ ያለን፣ ካልተሰጠን ይልቅ የታደልነው፣ ከምንመኘው የበለጠ በእጃችን ብዙ ሀብት እንዳለ መራራውን እውነት ያቀምሱናል። የጎደለን አንድ ነገር ብቻ፤ ልብ ማለት!

ኹለቱ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የመጽሐፍት ልገሳን በማድረግ፣ ቤተመጻሕፍትን በማጠናከር፣ ባለሞያዎችን በማሠልጠንና በማማከር እያገለገለ ኃላፊነቱ መሆኑን በተግባር ያሳያል። በዚህም መሠረት በተለያዩ ከተሞች በአንድ ወገን ቤተመጻሕፍት እንደ አዲስ እንዲከፈቱ፣ በሌላ በኩል የነበሩት አቧራቸው ተራግፎ እንዲሠሩ፣ አንዳንዶቹም እንዲጠናከሩ ሲሠራ በቅርበት የተከታተለ ማየት የሚችለው እውነት ነው።
አሁንም በጋሞዎች ምድር፣ በኤዞ ከተማ ኹለት የሕዝብ ቤተመጻሕፍትን ለመደገፍና አለሁ ለማለት ነው የተገኘው። አንደኛው በኤዞ ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ ኹለተኛው በዞኑ ምዕራብ አባያ ወረዳ በምትገኘው ብርብር ማርያም ገዳም አካባቢ የተሠራው ነው።

በኤዞ ከተማ የተገነባው ቤተመጻሕፍት በዶክተር ታደሰ ወልዴ ሥም የተሰየመ ነው። እኚህ ሰው የጋሞ የባህል አባት ወይም በአገሬው አጠራር ‹ሁደጋ› ናቸው። ኑሯቸው በአውሮፓ ቢሆንም፣ ጋሞ እየተመላለሱ መጎብኘታቸውና እንዲህ ላሉ ትውልድን ለሚገነቡ ሥራዎች ቀና ትብብር ማሳየታቸው የተለመደ ነው። እርሳቸው ብዙ ማውራት የማይወዱ ቢሆኑም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ልጆችና አባቶች ምርቃት፣ የቤተመጻሕፍቱ በእርሳቸው ሥም መሰየምም የሚነግረን እውነት መልካም አሳቢነታቸውን ነው።

ታድያ በምረቃት መርሃ ግብሩ ላይ የኤዞ ልጆችና አባቶች ተገኝተዋል። አባቶች ከፊታቸው ልጆችን ይይዛሉ። ያለ ልጆች የሚሆን ነገር የለምና። ‹ልጅ ያቦካው…› የሚል ብሂል በጋሞ ምድር ሰሚ የለውም፣ ኤዞዎች ይህን ብሂል ጭራሹን አያውቁትም። ሕጻናት ንጹህ ነፍስ ያላቸው ናቸውና ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ይመርቃሉ፣ ያስታርቃሉ። እናም በአባቶችና በልጆች ምርቃት ቤተመጻሕፍቱ ተመረቀ።

ድንች፣ ዳጣ፣ ባለጸጉር ድንች፣ ‹ቦኤ› የተባለ የስር ዓይነት ቀረቡ። ቅቤ የጠጣ ቂንጬ እንዲሁም ማር ተከታትለው ቀረቡ። ወቅቱ እንጂ ቢያጎርሱ ደስ ይላቸዋል! ‹ብሉ ጠጡ› ሲሉ በልግስና ነው። ለእንግዶቻቸው ያንን ሁሉ ያለስስት ሲያቀርቡ ታድያ፣ ከምንም በላይ ለአእምሮ ምግብ የሆነውን ጥበብ ለመመገብ መጻሕፍት ወሳኝ ናቸውና፣ ያንን ደግሞ በአደራ ተረከቡ።

ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላን ጨምሮ፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ እንዲሁም ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ንባብን በተመለከተ ሐሳባቸውን ለኤዞ ወጣቶች አካፍለዋል። ንባብ የት እንደሚያደርስ፣ ከመጻሕፍት ጋር ወዳጅነትን መፍጠር ዋጋው ምን ድረስ እንደሆነም፣ የጋሞ ፍሬ የሆኑትን አሰፋ ጫቦን በማውሳት አነሱ።
ደግሞ ከዚህ ተሻገርን። ወደ ኹለተኛው የሕዝብ ቤተ መጻፍሕፍት ምርቃት መሰናዶ። ግን ከዛ ቀድሞ የሆነው እንዲህ ነው፤ ከኤዞ ከተማ ተስተን ወደ ብርብር ማርያም ልንሄድ ባቀድንበት እለት፣ ማልደን ልንነሳ ተቃጥረን ሳለ ዝናብ ሲጥል አደረ። ጠዋት ስንነሳም ጭቃው እንደልብ የሚያንቀሳቀስ ዓይነት አልነበረም። ‹መንገዱ ስለማያስኬድ…› ተባለ፤ ልንቀር። በምዕራብ አባያ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ብርብር ማርያም ገዳም ስር፣ ዳገቱ መጀመሪያ ላይ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች እንግዶቻቸውን ይጠብቃሉ። ያስጨንቃል።

እንደፈራነው አልሆነም፣ ካሰብንበት አልቀረንም። ጭቃው ገር ሆኖ የማለዳዋ ፀሐይ አሸነፈችው፣ ሳይውል ደረቀ። በዐይናችን ፊት ከአንድና ኹለት ሰዓት በፊት ለዕይታ የሚጨንቅ የነበረው መንገድ ወደ ቀደመ መልኩ ተመለሰ። ይሄኔ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ ዳገቱን አልፎ ወደምትገኘው ብርብር ማርያም ገዳም ጉዞ ጀመርን።
ጥንታዊት ገዳም ናት። መልካምና የደስታ ስፍራ፣ ያማረችው ፍሬ በብዙ ድካም እንድትገኝ፣ ብርብር ማርያም ገዳምም ከተራራው አናት ላይ ሰፍራለች። መኪና መውጣት የሚችለውን ያህል ደጋግፎ ካደረሰን በኋላ የተወሰነውን ዳገት በእግር አዘገምነው። ብርብር ማርያም ገዳም በ1522 በአጼ ልብነ ድንግል ነው የተገደመችው። ይህች ጥንታዊት ገዳም እንዲህ በወፍ በረር የማይነገር ብዙ ታሪክ ያላት ናትና፣ ይቆየን።

ወደ ሕዝብ ቤተመጻሕፍቱ እንመለስ። በዚህ ስፍራ የተቋቋመው አዲስ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት በአባ ባህርይ ሥም የተሰየመ ነው። በብዙ መጻሕፍት ማጠናከር ገና የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ሁሉም መጀመሪያ አለውና ይህ ቤተመጻሕፍት መመረቁ ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ነው።

የብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይኵኖአምላክ መዝገቡ በምርቃቱ ወቅት ሲናገሩ፣ ስፍራው በኢትዮጵያ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች ካሉባቸው ቦታዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ጥንታዊነቱ ለንባብ ብቻ ሳይሆን ለመጻፍም ነው፣ ቀደምት ከሚባሉና አንድ ሺሕ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ጸሐፍትና አንባብያን ያሉበት ነው። ነገር ግን ያ የመጻፍና የንባብ ባህላችን በቤተ እምነቶች ብቻ ታጥሮ የቆየ በመሆኑ፣ አብያተ ቤተመጻሕፍት ሳናስፋፋ ለረጅም ጊዜ ቆይተናል።›› በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ።

ተቋማቸውም በአካባቢው ቤተመጻሕፍቱን ያቋቋመበት ዓላማ፣ ከረጅም ጊዜ በፊት የነበረውን የበለጸገ የንባብና የጽሑፍ ባህልና ሀብት ለማደስና በስፋት በአገር ደረጃ እንዲተገበር ለማድረግ ነው አሉ። ከአካባቢው የንባብና የጽሑፍ ታሪክና ባህል በመነሳት፣ ‹እንደ አዲስ ቤተመጻሕፍት አቋቋምን ሳይሆን፣ የኖረውን አስቀጠልን ነው› ሲሉ አጽንዖት ሰጡ። ለቀደሙት ክብርን ሰጥተው የዛሬን ትውልድ ድረሻ አያይዘው ሲጠቁሙም ነው።

በዚህ ክዋኔ ዶክተር ታደሰ ወልዴ ተገኝተዋል። እርሳቸውም አሁን የተሻለ ሕይወትን ለመምራት፣ ከዓለም የሚያገናኝ እውቀት ለመሸመት፣ ከምድሩ አልፎ የሕዋውን ለመቃኘት እውቀት አስፈላጊ ነው በማለት አነሱ። ‹‹እውቀትን የጨበጠ ሕዝብ ተሸንፎ አያውቅም፣ አይታለልም፣ አይረታም፣ ትክክል ያልሆነውን ልክ አይደለም ብሎ ይሞግታል። ስለዚህ የእውቀት ባለቤት እንድንሆን መጻሕፍት ዋነኞቹ ናቸው።›› ሲሉም መልዕክታቸውን አድምቀው አስተላለፉ። ሁሉም ታድያ በመልዕክታቸው ከመጻሕፍት የሚገኘውን ቁምነገርና እውቀት፣ ጥበብና ሥልጣኔ ከማሳታቸው ጎን ለጎን፣ አደራውን ለአካባቢው ሰው ሰጥተዋል።

መርቀው ከማይሰለቹ አባቶች ምርቃት፣ መልካም ምኞትና የምሳ ግብዣ በኋላ አካባቢውን ለቀን፣ የመጣንበትን ጉዳይ ጨርሰናልና ደግሞ ለመምጣት ያብቃን ብለን፣ ኤዞን ለመጨረሻ ጊዜ ሰላምታ ሰጥተን እኩለ ቀን ላይ ወጣን። ቁልቁል ወረድን።

ጨንቻን አልፎ ወደ አርባ ምንጭ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ እጽዋት የተከበበ ነው። የአርባ ምንጭ የፍራፍሬ ማሳዎች ከሩቅ ይታያሉ። ምድሩ ሁሉ አረንጓዴ ምንጣፍ የለበሰ ይመስላል፣ እልፍ ሲሉ ደግሞ የአርባ ምንጭ ሐይቆች። ጫሞ እና አባያ ሐይቆች በመካከላቸው ‹የእግዜር ድልድይ› ተብላ የምትጠራ ቀጭን መሬት አኑረዋል። ሥማቸው ይለያይ እንጂ አልተለያዩም፣ ድልድይን ሠርተዋል። ውሃ ውሃ ነው፣ ሐይቅም ሐይቅ። ሰውም ያው ሰው ነው። ኢትዮጵያዊም እንደዛው።
የተፈጥሮን ድንቅ ውበት እየቃኘን ቁልቁለቱን ጨረስን፤ ወደ አርባ ምንጭ፤ ከዛ ወደ ሸገር፤ አዲስ አበባ። ወደ ቀደመ ነገራችን ተመለስን፣ ሩጫ፣ ጫጫታ፣ ወከባ…። ሰላም ለአገራችን!

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com