የእለት ዜና

በሞላሰስ እጥረት ምክንያት አልኮል ፋብሪካዎች ሥራ አቁመዋል

በአዲስ አበባ የሚገኙ የአልኮል ፋብሪካዎች ባጋጠማቸው የሞላሰስ እጥረት ምክንያት ሥራቸውን ለመቀጠል እንቅፋት ስለሆነባቸው ምርት ለማቆም መገደዳቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ልዩ አዲስ የአልኮል መጠጦች ኢንዱስትሪ እና መስከረም አልኮል እና ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲሁም ብሔራዊ የአልኮል እና የአረቄ ፋብሪካ ደግሞ በግማሽ በአልኮል እና በሞላሰስ እጥረት ምክንያት ምርት ለማቆም እየተገደዱ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የብሔራዊ አልኮል እና አረቄ ፋብሪካ የምርትና ቴክኒክ ክፍል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ኮከቤ ቁሜ እንዳሉት በሞላሰስ እና አልኮል እጥረት ምክንያት በሰበታ የሚገኘው ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ ከመጋቢት 2012 ጀምሮ ሥራ እንዳቆመና በመካኒሳ ያለው ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ብቻ ምርት እያመረተ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመስከረም 2013 ላይ 298 ሺሕ አምስት መቶ ሊትር አልኮል ለማምረት ታቅዶ እንደነበርና 230 ሺሕ ሊትር ያህል ብቻ ማምረት እንደታቻለ እና ይህም የምርት መቀነስ በሞላሰስ እጥረት ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ልዩ አዲስ የአልኮል መጠጦች ኢንዱስትሪ ለአልኮል መጠጦች ዋነኛ ግብአት የሆኑትን ሞላሰስ እና ቴክኒካል አልኮል እንደሆኑና በአሁኑ ሰዓትም የኹለቱም እጥረት ስላጋጠመ ሥራቸውን እንዳቆሙ በድርጅቱ ውስጥ የአስተዳደር ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ሰራተኛ ተናግረዋል።

በቀን 100 ቶን ሞላሰስ በወር ሦስት ሺሕ ቶን በአመት ደግሞ ወደ 30ሺሕ ቶን ሞላሰስ ያስፈልገናል ሞላሰስና ቴክኒካል አልኮል የአልኮል ፋብሪካዎች ዋነኛ ግብአቶች ናቸው ያሉት የአስተዳደር ሰራተኛ ከኮቪድ 19 ከተከሰተ ጀምሮ ለስምንት ወራት የኹለቱም እጥረት ስላጋጠመ ሥራ መሥራት ማቆማቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በድርጅቱ ውስጥ ወደ 72 የሚሆኑ ሰራተኞች እንዳሉና በአሁን ሰዓትም ለሰራተኛ ደሞዝ ከተቀማጭ ገንዘብ ላይ እያወጡ እየከፈሉ እንደሆነም አስረድተዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገራቸው የመስከረም አልኮልና ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዮናስ ኃይለማርያም ደግሞ ኮቪድ 19 ከመጣ ጀምሮ በቴክኒካል አልኮል እጥረት ምክንያት ድርጅታቸው በሙሉ አቅሙ ማምረት በሚችለው ልክ እየሰራ እንዳልሆነ እና መንግሥትም በዘርፉ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሊሆኑ ሚገባቸው ተቋማት እያሉ የሳኒታይዘር የማምረት ሂደቱን በዘርፉ ውስጥ ለሌሉ ተቋማት በመሰጠቱ ለሰራተኞቻቸው ከአካውንታቸው እያወጡ ለመክፈል መዳረጋቸውን አክለው ተናግረዋል።

ኮቪድ 19 ሲመጣ ብዙ ድርጅቶች የእጅ ማፅጃ (ሳኒታይዘር) ማምረት በመጀመራቸው ለኛ ይሰጥ የነበረው አልኮል መጠን ቀንሶብናል በዚህም የኛ ሥራ ተበድሏል ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢፌዴሪ ስኳር ኮርፖሬሽን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ጋሻው አይችሉህም እንዳሉት በአገራችን ሰባት የሚሆኑ የስኳር ፋብሪካዎች እንዳሉ እና በክረምት ወራትም ለጥገና ሁሉም ፋብሪካዎች ሥራ እንደሚያቆሙ ተናግረዋል።

ሞላሰስና ቴክኒካል አልኮል የሚገኘው ስኳር ሲመረት ነው ያሉት ኃላፊው በክረምት ለጥገና በቆሙበት ወቅት ስኳር ስላልተመረተ እና በኮቪድ ምክንያት ለብዙ ድርጅቶች ሳኒታይዘር እንዲያመረቱ ስለተሰጠ የሞላሰስና ቴክኒካል አልኮል እጥረት መከሰቱን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በቅርብ ቀናትም ጥገናቸው ተጠናቆ ሦስት ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እየተመለሱ እንደሆነም ተናግረዋል የፋብሪካዎቹ ወደ ሥራ መመለስም የሞላሰስ እጥረትን እንደሚያቃልል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በቀጣይም ጥገናቸውን ቶሎ ጨርሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ሁሉም ፋብሪካዎች ማምረት ሲጀምሩ ችግሩ እንደሚቃለል ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!