አሽከርካሪዎችን ለመፈተን ከተዘጋጁት ጥያቄዎች 30 በመቶው ስሕተት ናቸው ተባለ

Views: 123

የትራንስፖርት ሚኒስትር ከዘርፉ አመራሮች ፣ከአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ እና ተሸከርካሪ ምርመራ ተቋማት ባለቤቶች ጋር በተወያየበት መድረክ ላይ እንደተገለፀው ለዕጩ አሽከርካሪዎች ከሚዘጋጁት ሦስት ሺሕ የምዘና ጥያቄዎች መካከል 800 ያህሉ የተሳሳቱ እንደነበሩ ተገልጿል።

የምዘና ፈተናዎች የተለያዩ ክፍተቶች ያሉባቸው ናቸው የተባለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሙሉ በሙሉ የምርጫ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች፤ አራቱም አማራጮች መልስ የማይሆኑበት ወይም አራቱም መልስ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዳለ ተገልጿል።በአማራጮቹ ላይ ሁሉም መልስ ይሆናሉ አሊያም አይሆኑም ተብሎ የተገለፀ ነገር አለመኖሩ ጥያቄዎቹን መልስ አልባ እንዳደረጋቸው ተገልጿል።

አምሳሉ አምባው የአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሲሆኑ እንደ አሽከርካሪ ማሠልጠኛ ማኅበራት ከተመሰረቱ ዐስር አመታትን አስቆጥረዋል።ከ40 በላይ አባል ማኅበራት ባላቸው ተቋማት ውስጥ በሚሰጡት የምዘና ሂደቶች ላይ ችግሮቹን እንዳስተዋሉ ገልጸዋል።ይህንንም ችግር ለከተማም ሆነ ለፌደራል ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች እንዳመለከቱም ለአዲሰ ማለዳ አስታውቀዋል።

በፌደራል ደረጃ የተቋቋሙት መስሪያ ቤቶች እኛን ይከታተላሉ ያሉት አምሳሉ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እና ሌሎች በሥሩ ያሉ መስሪያ ቤቶች ቁጥጥሩን ከሚያደርጉ መስሪያ ቤቶች መሃከል እንደሚገኙበት ገልፀዋል። እንደ ተቋም የንድፈ ሐሳብ እና የተግባር ስልጠና የምንሰጥ ሲሆን በተለይም በንድፈ ሐሳብ ስልጠናው ላይ የካሪኩለም ችግሮች፣ የመፃህፍት ይዘት አቀራረብ መዘበራረቅ እና ሌሎች ከጥያቄዎች ጋር የተገናኙ ክፍተቶች በሥራችን ላይ ክፍተት ፈጥረውብናል ይላሉ ሃላፊው።

እንደእነዚህ ያሉ ችግሮችን እና መመሪያዎችን የተመለከቱ ክፍተቶች ስላሉ እንደ ማኅበር ጥያቄያችንን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረባቸውን አምሳሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል ።

አዲስ ማለዳ ይሄንን ጥያቄ ይዛ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ቁጥጥር እና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን ገ/ሕይወት ሙላቱን አነጋግራለች። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ አሽከርካሪዎች ሲለማመዱም ሆነ መጨረሻ ላይ ለፈተና ሲቀርቡ የሚፈተኗቸው ጥያቄዎች በርካታ እንደሆኑ ገልፀው።ከነዚህ ውስጥ ወደ ስምንት መቶ ገደማ የሚሆኑት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ችግር ያለባቸው መሆናቸውን እነሱም በጥናት ወቅት እነደተረዱት ይገልፃሉ።

ከዚህ በፊት የነበረው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በክልልም ሆነ በፈደራል ትራንስፖርት ባሉ ቢሮዎች እንዲሁም በማሠልጠኛ እና ቴክኒክ ተቋማቱ መካከል የተቀናጀ እና የተናበበ አሰራር አልነበረም ያሉት ዳይሬክተሩ።ከዚህ በኋላ ግን “በማንዋል” ማሻሻያ ተደርጎባቸው የሚሰሩ ስራዎች ይኖራል ይላሉ።

ከኹለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚቋቋም የቴክኒካል ቡድን ይኖራል ያሉት ገ/ሕይወት ቡድኑ የመለማመጃ እና የፈተና ጥያቄዎቹን እንዲከልስና በጥያቄዎቹ ላይ የሚታዩትን ድግግሞሽ፣ አሻሚነት እና ስህተት የሆኑት እንዲስተካከሉ ይደረጋል ብለዋል።በምትኩም የሰልጣኝ አሽከርካሪውን እውቀት፣ ብቃት እና ክህሎትን የሚመዝኑ ጥያቄዎች የሚተኩ ይሆናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ክለሳ እና ግምገማ ከተደረገ በኋላ ‹ሰርኩላሩ› ለሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተላልፎ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች(የአሽከርካሪ ተቋማቱ አሰልጣኞችን ጨምሮ) አስተያየት እንዲሰጡበት ይደረጋል የተባለ ሲሆን በኋላም እንደሚሰራጭ እና በቀጣይም ሰልጣኞች በሞባይል አፕሊኬሽን ጥያቄዎችን የሚያገኙበት አሰራር ጭምር እንደሚኖር ሃላፊው ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በአሽከርካሪዎች ሥልጠና እና ፍቃድ አገልግሎት እንዲሁም የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ እና ብቃት ማረጋገጥ አገልግሎት ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙት 550 የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋማት መካከል 220 ወይም 40 ከመቶው ብቻ የሚሆኑት በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት መስፈርቱን አሟልተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

አምሳሉ በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ ሲሆን ሚኒስቴሩ ያቀረበው እና ስታንዳርድን የሚመለከተው ጉዳይ የሚያተኩረው እንደ ሪፖርት አቀራረብ፣ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ አቴንዳንስ አያያዝ እና ሌሎች ጥቃቅን ነገሮች ላይ እንጂ የትራፊክ አደጋውን ከመላከል አንፃር ያሉ ጉዳዮች ላይ አይደለም የሚያተኩረው በመሆኑም ድጋሜ ክለሳ ሊደረግበት ይገባል የሚል ሐሳብ አላቸው።ስታንዳርዱን ያላሟሉት እነማን ናቸው የሚለው በራሱ ጥቅል ሆኖ ነው የቀረበው ያሉት አምሳሉ ።እኛም ምንም ችግሮች የሉብንም አላልንም ። ከባህሪይ አንስቶ እስከ አደረጃጀት ችግሮች እንዳሉብን የምናውቅ ሲሆን በተቻለ መጠን ክፍተቱን ለማስተካክል የራሳችንን ኃላፊነት እንወስዳለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com