የእለት ዜና

ቀለም የቆጠሩ ሥራ አጦች

Views: 463

ፉአድ ሚፍታ በተለምዶ ጀሞ ሚካኤል አካባቢ እርሱን ጨምሮ ከአምስት የቤተሰብ አባላቱ ጋር የሚኖር ዕድሜው በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ወጣት ነው።ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት ከአድማስ የኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ሲመረቅ እርሱም ሆነ ጓደኞቹ በተለይም ቤተሰቦቹ የነበራቸው ደስታ ወደር የነበረው አልነበረም።

የእርሱ ደስታ በተማረበት የትምህርት መስክ ሥራ አግኝቶ አንድም ቤተሰቦቹ ለርሱ ብለው የሚያወጡትን ወጪ ማስቀረት እና እራሱን ከቤተሰብ ድጋፍ ማላቀቅ ሲሆን። በሁለተኛነት ደግሞ የትምህርት ደረጃውን በማሳደግ ለተሻለ ደረጃ በመማር የተሻለ ቦታ ላይ መቀመጥን አስቦ ነበር።ሆኖም ከተመረቀበት ማግስት ጀምሮ ሥራ ማግኘት ቀድሞ እንዳሰበው ቀላልና እድሎቹም ብዙ ሆኖ አላገኛቸውም።አራት ኪሎን ብዙ ጊዜ ተመላልሶበታል፤የሥራ ማስተወቂያዎችን ለማንበብ።ስልኩ የሥራ ማስታወቂያ በሚያቀርቡ የማኅበራዊ ገፆች እንደተጨናነቀ ነበር።

ከጋዜጣም ሆነ ከስልክ መተግበሪያ ገፆቹ ላይ የሞከራቸው የሥራ ማስታወቂያዎች ውጤታማ ባለመሆናቸው የተነሳ ወደ ሥራ አፈላላጊ ኤጀንሲዎች ነበር ያመራው ደግሞም ተሳካለት።አጀንሲው ፈተነው ከዛም በአንድ ድርጅት እንዲቀጠር አደረገው።ፉአድ ለድርጅቱ ይሰራል ክፍያውም በኤጀንሲው አማካኝነት ነበር ሲፈፀምለት የነበረው።ሆኖም ከሰባት ወራት የዘለለ እድሜ አልቆየም በድርጅቱ የሰራተኛ ቅነሳ ይደረግ ተብሎ የገፈቱ ቀማሽ ሆነ።ያለፉትን አሥራ አራት ወራት ያለ ሥራ በተስፋ መቁረ ውስጥ ሆኖ ተቀምጧል።

ከሥራ ጋር በተገኛኘ ሲንከባለል የቆየውን የመዋቅር ተዋረዳዊ ተጠሪነት እንዲቆም አድርጎ አሁን ላይ እየሰራ ያለው የመንግሥት ተጠሪ አካል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ይባላል።ኮሚሽኑ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጥቶት ከኹለት አመታት በፊት በሚኒስትሮች ም/ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 435/2011 መሰረት ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ ተቋም ነው።
ኮሚሽኑም ሆነ ባሳለፍነው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) ለፓርላማ አባላት እንዳቀረቡት ሪፖርት ከሆነ በ 2012 ሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተገልጿል።

መንግሥት ባለፈው የበጀት ዓመቱ ልፈጥራቸው ካሰብብኩት በላይ ሥራ ዕድል ፈጥሪያለሁ ያለ ሲሆን።ከታቀዱት ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ከፍ ያለ አፈጻጸም አሳይቼ ወደ ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የተለያዩ የሥራ ዕድሎች ከፍቺያለሁ ብሏል።ከነዚህም 62 በመቶ ማለትም ወደ ኹለት ነጥብ አንድ ሚሊዮኑ ቋሚ፣ 38 በመቶው ወይም አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮኑ ጊዜያዊ ዕድሎች ናቸው ሲል አስታውቋል። በጾታ ድርሻ እንደተቀመጠው መረጃ ከሆነ ከተፈጠረው ዕድል ውስጥ 35 ነጥብ 5 በመቶው ሴቶች፣ 64 ነጥብ 5 ከመቶው ደግሞ ወንዶች እንደሆኑ ተነግሯል።

ከተፈጠሩት ሥራዎች ስርጭት አንፃር 48 በመቶው የሥራ ዕድል በገጠር ለሚገኙ ዜጎች የተፈጠረ ሲሆን 52 ከመቶው ደግሞ በከተማ ለሚገኙ ዜጎች የተፈጠረ ነው ተብሏል። ሆኖም በ2012 ከተፈጠሩት ጠቅላላ የሥራ ዕድሎች መካከል 330,971 ሥራዎች በኮቪድ 19 ተጽዕኖ ምክንያት ከስመዋል ይላል የመንግሥት ያለፈው ዓመት ሪፖርት።

እንደ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽኑ ዕቅድ በመላ አገሪቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ፣ እስከ 2017 14 ሚሊዮን ፣ እስከ 2022 ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ አንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል።

የመንግሥት ቁጥራዊ አሃዞች ይህንን ቢያመላክቱም እንደ ፉአድና በእርሱ እድሜ ክልል ከዛም ከፍ ያሉ ዜጎች ግን ዛሬም ሱሪያቸው መንደር ውስጥ በሚቀመጡባቸው ድንጋዮች ጫማቸው ደግሞ ላይ ታች በሚሉባቸው መንገዶች እንዳለቁ ነው።የቤተሰብን እና ሥራ ያላቸውን አብሮ አደግ ጓደኞች እጅ እንደማየት ቀፋፊ ነገር እንደሌለ ፉአድ ይመሰክራል።

ከራሴ ተሞክሮ በመነሳት ዘለቄታዊነት የሌላቸውን ሥራዎች ላይ ተቀጥሬ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረልኝ መመዝገቤ ለሚመለከታቸው ተቋማት ሥራ እንደተፈጠረልኝ ሪፖርት ከማድመቅ ውጪ አሁን ላይ ለሥራ አጥነቴ የፈየደው ነገር የለም ይላል ፉአድ:: ሌሎች ጓደኞቹም ይህንኑ ሐሳብ እንደሚጋሩት አስረግጦ እየተናገረ።ይበልጡኑ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞችና ወረዳዎቸ በመከሰቱ ሳቢያ ተፈጥረዋል የተባሉትም የሥራ ዕድሎች ባላታሰበ መልኩ እንደቀነሱ መንግሥት እራሱ አምኖ ያቀረባቸው ቁጥሮች ይመሰክራሉ።

ለአብነት ያክል በዓመቱ አፈጻጸም ካጋጠሙ ማነቆዎች መካከል ዋነኛውና በዚህ ሰአትም ጭምር የአለማችን ብሎም የሀገራችን ትልቅ ተግዳሮት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አንዱ ነው። ችግሩ አንደ ከተማ በአዲስ አበባ ላይ እንደ አገር ደግሞ በኢትዮጵያ ቀላል የማይባል ለሥራ የተዘጋጁ እጆችን ቀልብሷል።
ኮሮና በኢትዮጵያ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት ሂደት ላይ የሚሸነቁረው ሽንቁር ትልቅ ነበረ ፤ነውም።ሆኖም መንግሥት እንደሚለው ከሆነ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራና የነፍስ ወከፍ ገቢ ላይ እያስከተለ ያለውን ተግዳሮቶች ታሳቢ ያደረገ የአጭር ጊዜ ምላሽና የረጅም ጊዜ የመልሶ ማገገሚያ (Recovery) እቅድ እንዳዘጋጀ አስታውቋል።

በእቅዱ መነሻነትም በወረርሽኙ ለተጎዱ ኢንተርፕራይዞች ማገገሚያ የረዥም ጊዜ የብድር ዋስትና የሚሆን 28 ሚሊዮን ዶላር ሀብት ከለጋሽ ድርጅቶች ማሰባሰብ ተችሏል ተብሏል።በተጨማሪም የሥራ ፈጣሪዎችን ጥረት በመደገፍ በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ውስጥ ለወደቁ 11 ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ በማድረግና በቅርቡም የባንክ ብድር ዋስትና እንዲሰጣቸውና ውድድርን መሰረት ያደረገ የድጋፍ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ እንደነበር በስፋት ተገልጿል።

ተወዳጅ እሸቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሲሆኑ መስሪያቤታቸው በአገር አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ450,000 (አራት መቶ አምሳ ሺ) ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ለ302,887 (ሦሰት መቶ ኹለት ሺ ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት) ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደቻለና። ይህ አፈጻጸም ከሩብ ዓመቱ ዕቅድ አንጻር 67 በመቶ ሲሆን ለዚህ ዓመት ከተያዘው ሦስት ሚሊዮን ዕቅድ አንጻር ደግሞ 10 በመቶ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ውስጥም 72 በመቶው ቋሚ 28 በመቶው ደግሞ ጊዜያዊ እንደሆነ ገልፀው ጊዚያዊ ሲባል ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚቆዩ የሥራ አይነቶች እንደሆነ ያስረዳሉ።በተለይም ከመንገድ ሥራ ጋር የተገናኙ የፕሮጀክት ሥራዎችን እንደ ጥሩ ምሳሌ በመውሰድ።

የሩብ ዓመቱ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ663 ብልጫ እንዳለው የገለፁት አማካሪዋ። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት፣ የሰዉ ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መስፋፋት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ የመዋቅራዊ ችግር አለመፈታት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተመደበ በጀት በቂ አለመሆን እንዲሁም በአብዛኞቹ ክልሎች መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሆን የብድር አቅርቦት በወቅቱ አለማቅረቡ የተገኘው ውጤቱ ከቅዱ ዝቅ እንዲል ያደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ሲሉ የተቋማቸውን የሩብ አመት እንቅስቃሴ ሪፖርት መሰረት አድርገው ገልፀዋል።

ከክልልና ከተሞች አንፃር በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሻለ የሥራ ዕድል ተፈጥሮባቸዋል የተባሉት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርና ኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ ይህም በመቶኛ ሲገለፅ 85 ከመቶ ነው ተብሏል።የአማራ ክልል ላይ መሃከለኛ የተባለ እንቅስቃሴ ሲመዘገብ በተቀሩት ክልሎች ማለትም ቤንሻነጉል ጉሙዝ ፣ ሶማሌ ፣ጋምቤላ፣ ሀረሪና ደቡብ ክልሎች በቅደም ተከተል ከ 57 እስከ 26 በመቶ የሆነ አፈፃፀም ሲያስመዘግቡ እንደ አፋርና ድሬዳዋ ያሉት ክልልና የከተማ አስተዳደር ከ25 በመቶ በታች የሆነ ዝቅተኛ ውጤት ያሰመዘገቡ ናቸው ተብሏል።

እንደ ተወዳጅ አስተያየት ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሚቀርቡ ቁጥሮች ላይ የቁጥር ዝቅ ማለት አንደምታው ሥራ ካለመሥራት ጋር ሊያያዝ የማይገባ ሲሆን በተለይም በክልሎች አካባቢ ሪፖርተን አቀናጅቶ በሰዓቱ ካለመላክና እንዲሁም የዝግጅት ምዕራፍ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ይገልፃሉ።

የግሉ ዘርፍ በሥራ ፈጠራ ዕድል ከማሳተፍና ድጋፍ እንዲያደርግ ከመሥራት አንፃር ሊፈጠሩ ለታቀዱት የሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ የሚያስችል 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማሰባሰብ በዕቅድ ተይዞ ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በተደረገው መግባባት በአጠቃላይ 373.27 ሚሊዮን ዶላር በአገር አቀፍ ደረጃ ተሰብስቧል ያሉት ባለሙያዋ።በተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ለማበራከት የሚያስችሉ የክራውድ ፈንዲንግ /Crowd Funding/ የመንግሥት የብድር ዋስትና ሥርዓት ዝርጋታ የጽንሰ ሐሳብ ሰነዶች መዘጋጀቱን ጨምረው ገልፀዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተገናኘ የግሉን ሴክተር ማሳተፍ የመንግሥትንም ጫና ማቅለል በመሆኑ ኮሚሽኑ በስፋት እየሄደበት ያለ ጉዳይ ነው የሚሉት ተወዳጅ በተለይም አካል ጉዳተኞችንና ከስደት ተመላሾች ለመጠቀም የሚያስችል የሥራ ዕድል ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

አቤኔዘር ሙልጌታ በ20 ዓመቱ እንደ ሰፈሩ አብሮ አደጎች በሱስ ውስጥ አልተዘፈቀም ይልቁንም እንደ ቀልድ በጀመረው የማርሻል አርት ስፖርት እራሱን እያሻሻለ ሦስት የጥቁር ቤልት ዳኖችን ለማግኘት ችሏል።በቀለም ትምህርትም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከኦርቢት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በደረጃ አራት (ዲፕሎማ) ተመርቋል ሆኖም ላለፉት አንድ ኣመት የቀለም ትምህርቱ ሥራ ሊያስገኝለት አልቻለም።ይልቁንም ማርሻል አርቱን በተማረበት ትምህርት ቤት አዳዲስና ከርሱ በታች ቀበቶ ያላቸውን ስፖርተኞች ካለምንም ክፍያ ያሰለጥን ነበር (አእምሮውን ነፃ ለማድረግ)።ሆኖም እሱም የኮሮና ዳፋ ባስከተለው መዘዝ ተዘጋ። ምንም እንኳን ለሥራ ዕድል ያመለከተባቸው መንግሥታዊም ሆነ የግል ተቋማት ተገቢውን የሥራ ዕድል ባይፈጥሩለትም አቤኔዘር ተስፋ እንማይቆርጥ ይናገራል ።እንደ ቢዝነስ ካርድ መሥራትና ባነር ማሳተም ያሉ ሥራዎችን በአንዳንድ ሰዎች መልካምነት አልፎ አልፎ እሰራለሁ ሆኖም ልቤ የሚያርፍበትን መደበኛ ሥራ ግን ዛሬም እየፈለኩ ነው ይላል መንፈሰ ጠንካራው አቤኔዘር።

በመዲናዋ ውስጥ በስፋት የሚታየውን የሥራ አጥ ቁጥር ከመቀነስ አንፃር ሚና እንዲጫወት ሃላፊነት የተሰጠው ቢሮ የአዲስ አበባ የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ነው።ቢሮው ይፋዊ በሆነው የማኅበራዊ ትስስር ገፁ እንዳስነበበው ሪፖርት ከሆነ በ2013 አንደኛ ሩብ ዓመት የበጀት ዓመቱን ዕቅድ 15 በመቶ ወይምለ42,000 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ 36,128 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ እንዲሁም 11,540 ለሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ እድሎች እንደፈጠረ ያሳወቀ ሲሆን በሦስት ወራት ውስጥ በአጠቃላይ 47,668 የሥራ እድል ለከተማው ነዋሪዎች ተፈጥሮላቸዋል ብሏል።

ቢሮው ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን በመረጃ ገፁ ያስታወቀ ሲሆን።በቀረበው ሪፖርት ላይ ተሳታፊዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችም እንዳነሱ ገልፆ።የመስሪያ ቦታ ግንባታ እና የሚሰራባቸው ዘርፎች ተናባቢ አለመሆናቸው፣የሰራተኛ የአቅም ግንባታ ሥልጠና አለመኖር፣የከተማው የተዘዋዋሪ ፈንድ ቀጣይ እጣፈንታ፣ዘላቂ የሥራ እድል መፍጠር ላይ ትኩረት ቢሰጥ የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመለከታቸው አካላት አንስተውለት እንደነበር ተገልጿል።
የመስሪያ ቦታ ግንባታ እና የዘርፍ ተዛማችነት በተመለከተ በቀጣይ በሚደረጉ አዳዲስ ግንባታዎች ተስተካክለው እንደሚሰሩ፣የሰራተኛ የአቅም ግንባታ በተመለከተ ክፍተትን መሰረት ያደረገ ከሥራው ጎን ለጎን እየተሰጠ እንደሚሄድ፣የተዘዋዋሪ ፈንድ በሚመለከት በተረጋጋ ሁኔታ ጊዜ ወስዶ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ በከተማ ደረጃ እንደማይለቀቅ እንዲሁም ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የግል ድርጅቶች ላይ አቅም በመፍጠር ከመንግሥት ተቋም ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ እንደሚደረግ የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ይመር ከበደ ምላሽ እንደሰጡ የቀረበው ፅሁፍ ያሳያል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮው በ2013 ከ280,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅጂያለሁ ያለ ሲሆን ከሥራ እድሎቹም 80 በመቶ ቋሚና 20 በመቶው ጊዜያዊ እንደሚሆኑ አስታውቆ ነበር።

ሆኖም የከተማ ፍልሰቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየጎረፈ በሚመጣባት አዲስ አበባ፤ ከተለያዩ የክልል ከተሞች ጭምር የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለሥራ ፍለጋ በሚከትሙባት ከተማ፤ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በሕገ ወጥ መልኩ ሄደው እየተመለሱባት በምትገኘው መዲና ያለው የሥራ ፍላጎትና አቅርቦት የባርኔጣና ጫማ ርቀት ያለው ይመስላል እንደ ብዙሃን አስተያየት ሰጪዎች።

እንደ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መሰረታዊ የቅጥር ስታቲስቲክስ ከሆነ አገር አቀፍ የሥራ አጥነት ምጣኔ በ2013 40 በመቶ የደረሰ ሲሆን በየዓመቱ በአማካይ ወደ ሥራ የሚገቡ ሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ደግሞ ኹለት ሚሊዮን ነው።የሥራ አጥ የከተማ ወጣት ምጣኔ (ከ15-29 ዕድሜ) ከኹለት ዓመት በፊት ባለው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ 25 ከመቶ ነው።

እንደ ተወዳጅ ሐሳብ ከሆነ በተለይም የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽኑ ተፈጠረ የተባለውንም ሆነ ይፈጠራል የሚባለውን የሥራ እድል በተጫባጭ መረጃ የተመሰረተ መሆኑን በስሩ ባሉት ዲፓርትመንቶች የሚከታተል መሆኑን ገልፀው።ከመረጃ ትንተና አንስቶ እስከ ገንዘብ ስርጭት ያሉ ጉዳዮች በኮሚሽኑ በአንክሮ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው ይላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com