ኬሚካሎችን ለማስወገድ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

Views: 102

በኢትዮጵያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና ተከማችተው የሚገኙ ዲዲቲ፣ ኦርጋኖ ፎስፌት እና ኦርጋኖ ክሎሪን የሚባሉ ኬሚካሎችን ለማስወገድ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ጀነራል ተወካይ ግርማ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

ግርማ እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ኬሚካሎቹ ምን ያህል ናቸው የሚለውን ለማወቅ ሦስት ዓመታት መፍጀቱን አስታውቀው፤ በአሁኑ ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ 383 የሚደርሱ ኬሚካሎች የተከማቹባቸው መጋዘኖች እንዳሉና በእነዚህ መጋዘኖችም 1300 ቶን ዲዲቲና ኦርጋኖ ክሎሪን የተሰኘው ኬሚካል እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ኬሚካሎችን ለማስወገድም በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም (Global environmental facility) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብር በኩል የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱንም አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ያገነችው መረጃ ያመላክታል።

ጨረታውን ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካበቢ መርሀ ግብር ሲሆን ጨረታውን ያሸነፈነፈው ቪዮሊያ ኢንቫይሮሜንታል ሰርቪስ የተባለ በሥራው ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከ 14 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ኬሚካሎች ስታስወግድም ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ነው ሲሉ ግርማ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአገር ደረጃ ለመጨረሻ ጊዜ የፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካሎች ማስወገድ ሥራ የተሰራው ከ 14 ዓመት በፊት በኹለት ዙሮች ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ቶን የሚሆን እንደሆነም አስታውሰዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ማዕከላዊ መጋዘን ተብለው የተሰየሙ ኹለት ትልልቅ መጋዘኖች በአዳማ እና በአዳሚ ቱሉ የሚገኙ ሲሆን፤ በአዳማ ባለው መጋዘን ውስጥ 460ቶን አዳሚቱሉ ባለው መጋዘን 310 ቶን የተቀረው ደግሞ በሌሎች የአገሪቷ ክልሎች ላይ ባሉ መጋዘኖች ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኬሚካሎቹን የማጓጓዝ ሂደት የባዝል ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚባል ስምምነት እንዳለ እና እያንዳንዱ የሚያርፍበት አገር ፍቃድ ማግኘት እንደሚያስፈልግ እና ፍቃድ የማግኘቱ ሂደት ረጅም ጊዜ እንደወሰደ እና በማስወገዱ ላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ኬሚካል በማስወገድ ልምድ ያላቸውን አወዳድሮ መቅጠር ያስፈልጋል ይህም ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ ለማወቅ ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት ኹለቱ ሥራ ተጠናቆ ለማሸግ የሚያስችል የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው ብለዋል።

በቅድሚያም በአዳማ እና አዳሚቱሉ ያሉትን የማዘጋጀት ሥራ ሊሰራ እንደታሰበና ይህንንም ለመሥራት አደገኛ ኬሚካሎች ስለሆኑ ለማጓጓዝ መልሶ ማሸግ (safe guarding) እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ግርማ ለማሸግ የራሱ የሆነ ሥልጠና ስለሚያስፈልገው ሥልጠና መስጠት እንደጀመሩም ነው የተናገሩት።

ኬሚካሎቹን የማስወገድ ሂደት በሦስት ዙር የሚከናወን ሲሆን፤ በአዳማ ያሉትን ኬሚካሎች መልሶ ለማሸግ ቢያንስ 20 ሳምንት ይፈጃል የመጀመሪው ዙር እስከ ሚያዚያ ባለው ጅቡቲ ወደብ ይደርሳል ። ሙሉውን ለማስወገድ ደግሞ ቢያንስ 70 የሚሆኑ ኮንቴነሮችን ይፈጃል ብለዋል።

ምንም እንኳን ኬሚካሉን ማስወገድ ያለበት ያመጣው አካል እንደሆነ ቢታወቅም ነገር ግን እንደ አካባቢ ጥበቃ ዋነኛው ኃላፊነቱ ኬሚካሎቹ በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት አለማድረሱን ማረጋገጥ ነው ስለዚህም አሁን ላይ ላለው ኬሚካሉን የማስወገድ ኃላፊነት ላይ በግንባር ቀደምትነት እየሠራ ነው።

በአጠቃላይ ይህንን ፕሮጀክት ቴክኒካሊ አፍሪካን ኢንስቲቲውት የተባለ እና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገ ፕሮጀክቱን የሚያስተባብር ሲሆን ፣ የጤና ሚኒስቴር እና የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ደግሞ ቴክኒካል ክፍሉን ይመራል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር አጠቃላይ የፕሮጀክቱን የገንዘብ ፍሰት ይመራል ተብሏል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በጤና ሚኒስቴር የሃይጅንና አካባቢ ጤና ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አሽረፈዲን ዩያ እንዳሉት ኬሚካሎቹን የማስወገድ ሥራው ላይ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመሆን ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኬሚካሎቹ ካላቸው የጤና ጉዳት አንፃር የማስወገድ ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ እና ይህንን ለማድረግ ጨረታውን ካሸነፈው ድርጅት በመጡ ሰዎች ቴክኒካዊ ስልጠና ለተመረጡ ሰዎች እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሩ የማስወገድ ሥራው በአገር ውስጥ መሰጠት አለመቻሉ ከባድ እንደሆነና አሁን ኢትዮጵያ የምታስወግደው ኬሚካልም የሚወገደው ስፔን እንደሆነም ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com