<<በአፋር ጨው ማምረቻ ይዞታችንን እየተቀማን ነው>>

Views: 150

በአፋር ክልል ጨው ማምረቻ ይዞታውን እና ግብርም ይከፍልበት የነበረውን ቦታ በክልሉ ማዕድን ቢሮ አልተጠቀማችሁበትም በሚል ምክንያት እንደተቀማ የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅ እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በኮርፖሬሽኑ እቅድ መምሪያ ኃላፊ እና የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ይድነቃቸው ተፈራ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ከተቋቋመ ወደ 18 ዓመት ገደማ እንደሆነው የሚነገርለት የጨው ማምረቻው በመንግሥት የሚተዳደር ሲሆን፤ 10 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሆን ቦታ ተሰጥቶት አንደነበርም ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ይድነቃቸው እንደሚናገሩት ኮሚሽኑ በመጀመሪያ የተሰጠውን የማምረቻ ስፍራ ‹‹የማንጠቀምበትን ቦታ ለክልሉ ሰጥተን ወደ ሦስት ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ይዘን እየሰራን ነበር›› ያሉት ኃላፊው አሁን ግን 600ሺሕ ካሬ የሚሆነውን አልሰራችሁበት በሚል ለወጣቶች ለማስተላለፍ በሚል ግብር የምንከፍልበትን ካርታ የያዝንበትን ቦታ ተወስዶብናል ሲሉ አስታውቀዋል።

ሕጋዊ የሆነ ቦታችን ነው ሲሉ የተናገሩት ይድነቃቸው መቀነስ እንኳን ቢኖርበት የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅ እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ጋር ተነጋግሮ የኛ ካርታ ተስተካክሎ መሆን ሲገባው ነገር ግን አሁን ከይዞታችን ላይ ተመርተናል እያሉ ጨው የሚመረትበት ‹‹ፖንድ›› የሚባል ቦታ የተመረተ ጨው የሚቀመጥበት ‹‹አዎድ›› የሚባል ቦታ እንዳለና እርሱን ካርታ አሰርተው ካርታ ይዘው የሚመጡ ሰዎች መኖራቸውን እና ይህም በካርታ ላይ ድራቢ ካርታ መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹ወጣቶችን ስንጠይቃቸው የክልሉን ማዕድን ቢሮ ነው የፈቀደልን ይላሉ የክልሉን ማዕድን ቢሮ ስንጠይቅ ደግሞ እኛ አልሰጠንም ይላሉ ነገር ግን በፖሊስ መጥተው እኛን ሲያስቆሙንም ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በድርጅታችን ውስጥ የሚመረተው ጨው ወጣቶች (በባህላዊ መንገድ)ከሚያመርቱት ይለያል የሚሉት ይድነቃቸው። እኛ የማይጠቅሙ በጨው ውስጥ ያሉትን ባዕድ ነገሮች ሁሉ አጣርተን አውጥተን አዮዲን ያለው ጨው ነው የምናመርተው ብለዋል። እንደ ኃላፊው ገለፃ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገራችን ያለው የገበያ ውስንነት አለ በሚል ምክንያት ምርት እንድንቀንስም እየተደረጉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

አንድ አምራች ድርጅት ያመረተውን ምርት በነፃ ገበያ ስርዓት ነው መሸጥ ያለበት የሚሉት ይድነቃቸው ይህ ሁኔታ ግን በዚያ አካባቢ ላይ አይተገበርም አወዳድረን መሸጥ ሲገባን ነገር ግን ለአንድ ድርጅት (የጨው አምራቾች ግሩፕ ) ለሚባል ብቻ እንድናቀርብ እየተደረግን ነው ይህ ሁኔታ ደግሞ ከነፃ ገበያ ጋር ይጣረሳል ብለዋል።
የኮርፖሬሽኑ የማምረት አቅም በወር 75ሺህ ኩንታል ሆኖ እያለ ነገር ግን በወር 25ሺህ ኩንታል ለ 12 ዓመታት ሲሸጥ እንደነበረ እና ከአራት ወር በፊት ግን በአገራችን ያለው ገበያ ውስንነት ስላለው ለጥቃቅን አምራቾች የሚበቃ ገበያ ስለሌለ በሚል ምክንያት ወደ 5ሺሕ ኩንታል ብቻ እንዲወርድ መደረጉንም አዲስ ማለዳ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ የፋብሪካው ሕልውና ላይ ችግር ይፈጥራል አምስት ሺሕ ኩንታል ብቻ ሸጠን ለሰራተኛ ከፍለን ሌሎች ወጪዎችን አውጥተን መቀጠል ይከብደናል እንደውም እንደ ድርጅት ለመፍረስ ተፈርዶብናል ሲሉም ይድነቃቸው ተናግረዋል።

ብዙ ፋብሪካዎች ከጨው እጥረት ጋር በተያያዘ እየተዘጉ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ የሚናገሩት ይድነቃቸው ፤ የገበያ ስነስርዓቱ ስላልተስተካከለ እኛ ብዙ ጨው አምርተን የሚገዛን በማጣታችን ይበላሽብናል ፋብሪካዎች ደግሞ ጨው አጣን ብለው መንግሥትን ከውጪ አገር እናስመጣ የዚህ አገር ጨው ውድ ነው እያሉ ይጠይቃሉ አንዳንዶችም በጨው እጥረት የተዘጉ አሉ ብለዋል።

የገበያ ስረዓቱ ላይ ባለው ችግር ምክንያት ተመሳሳይ ጨው ከውጪ አገር ገብቶ እየተሸጠ ይገኛል በዚህም አገራችን ያለ አግባቡ የውጪ ምንዛሬ ታወጣለች ብለዋል።
አቤቱታችንን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርበናል የተወካች ምክር ቤት ለማእድን ሚኒስቴር እና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቅርቧል የሚሰጠንን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ፍሬህይወት ፍቃዱ እንዳሉት በጨው አምራቾቹና በክልሉ መንግሥት መካከል ያለመግባባቶች እንዳሉና እያጣሩ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል ።

ለተጨማሪ ማብራሪያ አዲስ ማለዳ የክልሉ ማዕድን ቢሮና የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ለማግኘት አልተቻልም፤ መረጃውን ስናገኝ እንደምናቀረብ ከወዲሁ እናሳውቃለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com