ሕብረት ኢንሺራንስ ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ አገኘ

Views: 133

ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል በመድን አገልግሎት ዘርፍ የቆየው ሕብረት ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳገኘ አስታወቀ። ይህ ገቢም ከባለፈው በጀት ዓመት ማለትም 2011 ጋር ሲነጻጸር ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ብልጫ እንዳለው ኩባንያው በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔው መድረክ አስታውቋል።

ኢንሹራንሱ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ያገኘው ገቢ ለመጨመሩ በምክንያትነት የተጠቀሰው ዋና ጉዳይ ከፍተኛ ትርፍ እንደሚያስገኝ ተጠንቶ የተገባበት የሪል ስቴት ግንባታ ነው ይላሉ ኢንሹራንሱን ለበርካታ ዓመታት የመሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ መሰረት በዛብህ።

እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የመድን ድርጅቱ በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት አራት ሕንፃዎችን በመገንባት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የኪራይ ገቢ ማግኘቱን እና ቀድሞ ለኪራይ ክፍያ ያወጣ የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ማዳኑን መሰረት በዛብህ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኢንሹራንሱ በዓመት ስድስት ሚሊዮን ብር ያወጣ የነበረውን የቢሮ ኪራይ ክፍያ ባለፈው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ማዳኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ። የኢንቨስትመንት ዘርፍ ገቢው እንዲጨምር ዋናውን ሚና የተጫወተው የቤት ኪራይ ወጪ መቅረቱና ተጨማሪ የኪራይ ገቢ በመገኘቱ መሆኑን መሰረት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።

ሕብረት ኢንሹራንስ ሰኔ 30/2012 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ዘርፍ 551 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው 2011 ዓመት ከተገኘው የአረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ12 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ኢንሹራንሱ በዓመታዊ ሪፖርቱ አመላክቷል። እነዲሁም ሕይወት ነክ ከሆነ መድን ዘርፍ ያገኘው የአረቢን ገቢ 46 ሚሊዮን ሲሆን ይህም ከቀዳሚው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ18 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል። አጠቃላይ ከኹለቱም መድን ዘርፍ 597 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ64 ሚሊዮን ብር ብልጫ በማሳየት የ12 በመቶ እድገት ያሳየ ነው ተብሏል።

ኩባንያው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ካለፉት ኹለት ተከታታይ ዓመታት የተሻለ የካሳ ክፍያ (Loss Ratio) እንዳሳየ የተጠቀሰ ሲሆን። በበጀት ዓመቱ ለካሣ ክፍያ ኹለት መቶ አርባ ሚሊዮን ስድስት መቶ አርባ ኹለት ሺ ብር እንዳወጣ አስታውቋል።

ሕብረት ከግብር በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከ2011 የበጀት ዘመን የ22 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ የተገለፀ ሲሆን ይህም በብር ሲገለፅ 147 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል።

ኩባንያው በባለፈው የበጀት ዓመት ኹለት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን መክፈቱን ያስታወሱት መሰረት በተያዘው የበጀት ዓመት ከሦስት አስከ አራት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት ጠቁመዋል። በተጨማሪም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በኦንላይን ለመስጠት በትኩረት እየሰራ ነው ሲሉ መሰረት አክለዋል።

በሌላ በኩል ኢንሹራንሱ በ2012 የበጀት ዓመት በኮቪድ-19 መከሰት ወደ አረብ አገራት ለሥራ የሚጓዙ የቤት ሰራተኞች ጉዞ በመሰረዛቸው ምክንያት ይሰጥ የነበረውን የህይወት ኢንሹራንስ በመሰረዙ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኩባንያው ይሰጥ የነበረው በቀን የተገደበ የጉዞ ኢንሹራንስ በወረርሽኙ ምክንያት ጉዞዎች በመገደባቸው አገልግሎቱን አስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ እንዳቆመ ተመላክቷል። በዚህም ሳቢያ ከ10 አስክ 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገቢ ኢንሹራንስ ኩባንያው ማጣቱን መሰረት አብራርተዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ሕብረት ኢንሹራንስ በሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በተቀሰቀሰው ኹከት ሻሸመኔ የሚገኘው አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሙሉ በሙሉ እንደወደመ እና አዲስ አበባ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱም እንደ መስታወት መሰበር ያለ አደጋ በማጋጠሙ ከ300 ሺሕ ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com