ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምዝገባ መስፈርት እየመረመረ ነው

Views: 151

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የነባር እና አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት እድሳት እና ምዝገባ ለማከናወን ፓርቲዎች ያቀረቡትን የአባላት ፊርማ እና ሰነድ እየመረመረ መሆኑን አስታወቀ።

ቦርዱ በአዲሱ የምርጫ ምዝገባ አዋጅ መሰረት ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው የተገኙ 76 ነባር የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖለቲካ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ሰነድ ምርመራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አማካሪዋ እንደገለጹት የነባር የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ መተዳደሪያ ደንብ ሰነድ ምርመራ በሶስት ነገሮች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው አንደኛው የፓርቲዎች የአባላት ፊርማ ማጣራት ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዳቸውን ማረጋገጥና የፓርቲ መተዳደሪያ ደንባቸው በአዲሱ የምርጫ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት መስተካከል አለመስተካከሉን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ሰነዳቸውን ለምርመራ ያቀረቡ 76 ፓርቲዎች በአዲሱ የምርጫ ምዝገባ መስፈርት አማልተው ከተገኙ እንዳሟሉ የሚገልጽ እድሳት እንደሚደረግላቸውም ተመላክቷል።
የአዲስ ተመዝጋቢ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምዝገባ ምርመራ በአዲሱ አዋጅ መሰረት ያቀረቡት የአባላት ፊርማ ትክክለኛነት እና ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዳቸውን በማረጋገጥ የውሳኔ ሀሳብ እንደሚሰጥ የቦርዱ ኮሚኒኬሽን አማካሪ ጠቁመዋል።

በአዲሱ የምርጫ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የሚመዘገቡ አዲስ ፓርቲዎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ እናት ፓርቲ፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲ፣ አፋር አብዮታዊ ፓርቲ እና የሲማሌ አርበኞች ፓርቲ መሆናቸወን ሶሊያና ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) በቀድሞው እንቅስቃሴው የምዝገባ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበ ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል።

ምርጫ ቦርድ የነባር እና አዲስ ተመዝጋቢ ፓርቲዎችን አዲስ የምርጫ ምዝገባ አዋጅ መስፈርት ለመመዘን በመላው አገሪቱ በሚገኙት 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹ የጠቅላላ ፓርቲዎችን የአባላት ፊርማ እውነተኛነት ለማረጋጋጥ ባለሙያዎች በወረዳ እና በቀበሌ ተሰማርተው ያገኙትን ሪፖርት ለምርጫ ቦርድ አጠናቀው ማቅረባቸውን ሶሊያና ተናግረዋል።

ቦርዱ በመላው አገሪቱ ባለሙያዎችን አሰማርቶ ባደረገው የአባላት ፊርማ ማረጋገጥ ሥራ በ 11ዱም ክልሎች በአማካኝ ከኹለት ሺሕ 900 አስከ ሦስት ሺሕ የአባላት ፊርማዎችን ማረጋገጣቸውን የጠቆሙት ሶሊያና የሁሉም ፓርቲዎች የአባላት ፊርማ ማጣራቱን ጠቁመዋል።

የፓርቲዎቹ አባላት ፊርማ ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች መኖራቸውን ሶሊያና ሲያነሱ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ አባላቶች መገኘታቸው፣ የወረዳ እና የቀበሌ ሥሞች ፓርቲዎቹ ካቀረቡት ሰነድ ጋር ትክክል አለመሆን፣ የአባላት የቤት ቁጥር አዲስ በሚል ተሞልቶ የተጠቀሰው ቦታ ኗሪ መሆን አለመሆን አለመጠቀስ እና በአባልነት የተጠቀሱ ሰዎች ሙሉ በሙሉ አለመገኘት ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ነው ሶሊያና ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት።

ቦርዱ በመላው አገሪቱ ከሚገኙት 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የቀረበለትን ሪፖርት መርምሮ ከፍተኛ ችግር የሆኑትን በመለየት የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው መስፈርቱን የላሟሉት የሚለውን እንደሚወስን ሶሊያና አብራርተዋል። የምርመራ ውጤቱን በአንድ ሳምንት ውስጥ ቦርዱ እንደሚሳውቅም አክለው ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት በሰራተኞች በተራ የመግባት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ፊርማ ባስመዘገቡበት በመላው የአገሪቱ ክፍል በወረዳ እና በቀበሌ የአባላት ፊርማ ትክክልኛነት ለማረጋገጥ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስገቧቸውን የአባል ይሰረዝልኝ ጥያቄ እና የጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ለመመርመር የወሰደው ጊዜ የነባር ፖለቲካ ፓርቲዎች እና አዲስ ተመዝጋቢ ፓለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ የምርጫ ቦርድ የምዝገባ መስፈርት እንዲዘገይ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን አማካሪዋ አስታውሰዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com