የውሎ አበል ክፍያዎች ማሻሻያ መመሪያ ወጣ

Views: 523

የገንዘብ ሚንስቴር እያደገ ከመጣው የገበያ ዋጋ ጋር ለማጣጣም በልማት አጋሮች የሚደረገውን የውሎ አበል ክፍያ ማሻሻያ መመሪያ በጥቅምት ወር 2013 ተግባራዊ አድርጓል።

በሌላ በኩል እስካሁን ሥራ ላይ የቆየውን የሠራተኞች የውሎ አበል ተመን በአሁኑ ወቅት ካለው የገበያ ዋጋ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ እና በመስክ ክትትል እና ግምገማ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላስከተለ የሚንስትሮች ምክር ቤት በሲቪል ሰርቢስ ኮሚሽን ተጠንቶ የቀረበውን አዲስ የመንግሥት ሰራተኞች የውሎ አበል ክፍያ ማሻሻያ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 3/2012 መርምሮ በማጽደቅ ከየካቲት 16 2012 ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል።

ነገር ግን አዲሱ የውሎ አበል ማሻሻያ መመሪያ ከውሎ አበል በስተቀር የአቅም ግንባታ እና ክትትል ግምገማ እንዲሁም የማኅበረሰብ ንቅናቄ ተሳትፎ ሥራዎች ጋር ተያያዢ የሆኑ ሌሎች ወጭዎችን እና የመንግሥት ሰራተኛ ያልሆኑ ሌሎች በልማት አጋሮች ድጋፍ የሚካሄዱ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ክትትል እና ግምገማ ላይ የጎላ ድርሻ ያላቸውን ባለድርሻ አካለት ያካተተ አልነበረም።

በመሆኑም በአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሸን አፈጻጸም የውሎ አበል መመሪያ ያልተካተቱትን እነዚህን ባለድርሻ አካላት በመመሪያው ታሳቢ ያልተደረጉትን ሌሎች ወጪዎች ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም አሁን ካለው የሸቀጦች ዋጋ አንጻር ተቀራራቢ የሆነ በልማት አጋሮች ድጋፍ ለሚከናወኑ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች ለሚደረጉ ክንውኖች የሚያገለግል ውሎ አበል መመሪያ ተዘጋጂቷል።

ይህ መመሪያ “በልማት አጋሮች ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የውሎ አበል እና ሌሎች ተዛማጂ ወጪዎች የአከፋፈል መመሪያ” ተብሎ እንደሚጠራ ለማወቅ ተችሏል። አላማው በልማት አጋሮች ድጋፍ ለሚተገበሩ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እና ከፕሮግራሞቹ ቀረጻ ግምገማ እና ትግበራ ጋር በተያያዘ በሚደረጉ ክንውኖች ወቅት ለሚያጋጥሙ ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችል ወጥ የሆነ የውሎ አበል እና ሌሎች ተዛማጂ ክፍያዎችን ለመዘርጋት የሚያችል ስርዓትን ለመተግበር ነው።

በዚህ መመሪያ እንዲስተካከሉ ተደረጉ ሌሎች ወጭዎች ከውሎ አበል ውጭ ያሉ የትርንስፖርት እና ሌሎች ከሥራው ጋር አግባብነት ያላቸው ወጭዎች ሲሆኑ የውሎ አበል አከፋፈል ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የቀን ውሎ አበል ማሻሻያ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 3/2012 መሰረት ለቁርስ 10 በመቶ ለምሳ እና ለእራት 25 በመቶ እንዲሁም ለመኝታ 40 በመቶ በሚል ተከፋፍሎ የሚሰላ ይሆናል።

የመንግሥት ሰራተኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ በሚደረጉ ክንውኖች ሲሳተፉ በአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ መመሪያ መሰረት የደሞዝ እና የሥራ ድርሻን መሰረት በማድረግ ልዩነት ሳያደርግ በቀን ብር 850 ይከፈላቸዋል በተመሳይ በክልል እና በዞን ዋና ከተሞች ላይ ቢሳተፉ 650 ብር የውሎ አበል ይከፈላቸዋል።በወረዳ ከተሞች ላይ በሚደረጉ ክንውኖች ላይ ቢሳተፉ ደግሞ 450 ብር እነደሚከፈላቸው መመሪያው ያመለክታል።

የመንግሥት ሰራተኞች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በሚኖሩበት ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በሚደረጉ ክንውኖች ተሰታፊ ቢሆን የደምወዝ እና የሥራ ድርሻን መሰረት በማድረግ ልዩነት ሳያደርግ በቀን ብር 125 ይከፈላቸዋል።ይህ የውሎ አበል የአከፋፈል ስርዓት ለሌሎች የማኅበረሰብ አካላት በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ ነው።የውሎ አበሉ የደርሶ መልስ የጉዞ ቀናትን የሚጨምር ነው።

የዱሮው የውሎ አበል አከፋፈል ስርዓት የከተሞችን የኑሮ ውድነት መሰረት ያደረገ እና ከክልል ከተሞች መካከልም ልዩነት የነበረው ሲሆን ለምሳሌ በመቀሌ 650 በባህር ዳር 690 በአሶሳ 500 የነበረ ሲሆን አሁን በሁሉም ክልል እና በዞን ዋና ዋና ከተሞች የሚደረገው ክፍያ 650 ብር ሆኗል።በአዲስ አበባ ደግሞ 750 የነበረው ወደ 850 ከፍ ብሏል።

ነገር ግን ክንውኑን በሚያዘጋጀው ተቋም ወይም መሥሪቤት በኩል ለተሳታፊዎች የተሟላ አገልግሎት ማለትም ቁርስ ምሳ እራት እና የመኝታ አገልግሎት ለተሳትፊዎች የሚቀርብ ከሆነ ተሳታፊዎች የውሎ አበል ክፍያ አይታሰብላቸውም የደርሶ መልስ የጉዞ ቀናት የውሎ አበል ክፍያ ግን የሚሰጣቸው ይሆናል።

መንግሥት በረሃ ብሎ በለያቸው ቦታዎች ክንውኖች ሲደረጉ በአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሸን የውሎ አበል መመሪያ አፈጻጸም መመሪያ የበረሃ አበል ተመን መሰረት በአበሉ ላይ ተጨማሪ ሆኖ ይከፈላል።የትራንስፖርት ወጪዎች ደግሞ የመንገድ ትራንፖርት ባለስልጣን እና የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባወቱት የዋጋ ታሪፍ መሰረት እና የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ፈቃድ በሰጣቸው የትራንፖርስ አገልግሎት ሰጭዎች የትንፖር ዋጋ ታሪፍ ደረሰኝ መሰረት የሚከፈል ይሆናል።

በአየር ትራንስፖርት ለሚደረግ ጉዞ በሚቀርብ የደርሶ መልስ የጉዞ ደረሰኝ እና ለጉዞው ወደ አየር መንገድ የሚያደርስ የመሥሪያቤት የመኪና አገልግሎት ካልቀረበ ለእያንዳንዱ ነጠላ ጉዞ የታክሲ ኮንትራት ወጪ መሸፈኛ ብር (ኹለት መቶ) 200 የሚከፈል ይሆናል።ይህ መመሪያ በሚኒሰተሩ ከጸደቀበት ጥቅምት 2013 ጀምሮ ተግባጋዊ ሆኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com