ከ“ጦርነቱ” ጀርባ

Views: 341

ሴኩቱሬ ጌታቸው መብረቃዊ ባሉት የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ የጥቅምት 24 ጥቃትን ተከትሎ የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕወሓት እንዲደመሰስ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ዐሥራ አምስት ቀናት ያለፉት ይህ ዘመቻ፥ አብዛኛው በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ከተሞችን በመቆጣጠር ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በመሸጋገር መቀሌን በሁሉም አቅጣጫ በ50 ሬዲየስ ዙሪያ መከበቡን የመከላከያ ሚኒስትሩ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) በአገር ውስጥ ለሚገኙ የውጪ አገራት ወታደራዊ አታሺዎች እና ዲፕሎማቶች ከቀናት በፊት አስታውቀዋል።

በዚህ ሳምንት የኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ደግሞ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑትና የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሓኖም (ዶ/ር) “ጁንታውን” ከአገራቸው አስበልጠው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዓለማቀፍ ጫና እንዲበረታ እንዲሁም ሕወሓት ድጋፍ እንዲያገኝ ላይ ታች ሲዋትቱ እንደነበር በማያሻማ ሁኔታ ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎም በአገር ውስጥ የሚገኙም ሆኑ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን የጀነራሉን መግለጫ በስፋት አስተጋብተዋል። አንዳንዶች የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴድሮስ የኮሮና ወረርሺኝን በተመለከተ ባሳዩት ቸልተኛነት እንዲሁም ለቻይና ከለላ ሰጥተዋል በሚል ከሥልጣን ለማባረር ያደረጉትን ሙከራ በመቃወም የድጋፍ ዘመቻ ማድረጋቸው አሁን ላይ ጸጽቷቸዋል፤ “የእናት ጡት ነካሽ” ሲሉ የተቃውሞ ዘመቻ የከፈቱባቸውም አሉ።

ቴድሮስ ለሕወሓት ያሳዩትን ድጋፍ በተመከለተ ሌሎች “ድመት መንኩሳ፣ አመሏን አትረሳ” ሲሉም ተሳልቀዋል። ልክ እንደ ሌሎች የሕወሓት ባለሥልጣናት በአስቸኳይ የእስር ማዘዣ ይውጣባቸው ከማለት ባሻገር፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማሳዊ ጫና በማድረግ ከያዙት ሥልጣን እንዲለቁ ለተባበሩት መንግሥታት አቤት ማለት አለበት ሲሉ ማሳሰቢያ መሰል ምክር የለገሱም አልታጡም።

ዘመቻው ፋታ የነሳቸው ቴድሮስ ኀሙስ አመሻሽ ላይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል። በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሁኔታ ልባዊ ሐዘን የተሰማቸው መሆኑን የገለጹት ቴድሮስ፥ ሁሉም ወገኖች ለሰላም፣ ለሰዎች ደህንነት እና ለጤና እና ለሰብኣዊ እርዳታ ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። ብዙዎች የሚከሷቸውን ለአንደኛው ወገን ታደላለህ የሚለውን “እውነት አይደለም” ሲሉ በማስተባበል ውግንናቸውም ከሰላም ጋር ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ባልተለመደ መልኩ ከሦስት ቀናት በፊት ፊታቸው ገርጥቶ፣ በፍርሃት ተውጠው እና ጓንት ሳያጠልቁ የሰጡት መግለጫ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ከሚደርስባቸው ድብደባና ግርፊያ ባሻገር ሞት ስለሚጠብቃቸው እጃቸውን እንደማይሰጡም አስታውቀዋል። አንዳንዶች ደብረፂዮን በእስረኞች ላይ ይደርስ የነበረውን ኢሰብኣዊ አያያዝ ምስክርነት ሰጥዋል ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ያ ያሳዩዋቸው የነበሩት ወኔ፣ አይበገሬነት እና ትምክህት ተንነው በፍርሃት መተካታቸው ሐዘኔታቸውንም እንዲገልጹ አስገድዷቸዋል።

ሌላው ሕወሓት በዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ከመንግሥት ጎላ ብሎ የታየበትን ሁኔታ ለመቀልበስ በሚመስል መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቶች በተለያዩ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን በመቅረብ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተንቀሳቀሱበት ሳምንት ሆኖ አልፏል። ለአብነት በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናሲሴ ጫሌ ጅራ ከሲቢሲ ሬዲዮ፣ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ሻውል በፍራንስ 24፣ በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳድር ሂሩት ዘመነ በዩሮ ኒውስ፣ ሬድዋን ሁሴን በሲኤንኤን እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትሩ ቀንዓ ያደታ በአልጀዚራ ላይ በመቅረብ ማብራሪያና የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል። በተጨማሪም የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፖምፒዮ እና በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቴቦር ናዥ የኢትዮጵያን መንግሥት እርምጃ ከሞላ ጎደል እውቅና የሚሰጥና የሕወሓት ተንኳሽ ጥቃት የሚያወግዝ መግለጫ መስጠታቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ጉልበት ሰጥቷል።

ይህም በተለይ ቴድሮስ አድሓኖምን (ምንም እንኳን በድብቅ ነው ቢባልም)፣ አሉላ ሰለሞን፣ የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጸዳላ ለማ በዋሽንግተን ፓስት እንዲሁም ማርቲን ፕላውት፣ ትሮቮል፣ ኸርማን ኮህን እና አሌክስ ድዋል ሕወሓትን ተጠቂ አድርጎ በመንግሥት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ ላይ ውሃ አፍስሶበታል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ሐሳባቸውን ያሰፈሩ በርካቶች ናቸው።

እጅግ አስገራሚና አነጋጋሪ በመሆን ከተነሱት ሰሞነኛ ጉዳዮች መካከል የሕወሓት ባለሥልጣና ቤተሰቦቻቸውን ወደ አሜሪካ ለማሾለክ ያደረጉት ያልተሳካ ሙከራ መጋለጡ ይገኝበታል። በተለይ የሕወሓት ሊቀመንበር ባለቤት አስካለ ገብረኪዳን እና የኹለት ዓመት ወንድ ልጃቸውን ለማስመለጥ የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱን እንዲሁም ያደረጓቸው የኢሜል መልዕክት ልውውጦች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ሾልከው ወጥተዋል። “የፈረደበት የድሃ ልጅ በጦርነት ውስጥ ይቆላል፤ እነሱ ግን ቤተሰቦቻቸውን ለተንደላቀቀ ኑሮ ወደ ውጪ አገራት ይልካሉ” ሲሉ ምሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን በአደባባይ ነውራቸው መጋለጡ ለወጣቱ የማንቂያ ደውል መሆን አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።

የሆነው ሆኖ ጦርነቱ እንደሚባለው በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ወይንስ የተራዘመ ጊዜ ይወስዳል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ዛሬም እርግጠኛ ምላሽ ያገኘ አይመስልም።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com