ሦስቱ ጸረ ኢትዮጵያ የጥፋት ኃይሎች!

Views: 282

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በሰላም ወጥተው ለመግባት እና የተረጋጋ ህይወት ለመምራት ከስጋት የጸዳ ሰላማዊ አካባቢ ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ሲባል ምንግሥት ለዜጎቹ ዘብ የሚቆም የመከላከያ ሠራዊት ደራጃል፤እንዲሁም በልዩ ልዩ አደረጃጀት ስር የሚዋቀሩ የጸትታ ፈርፎችን በማዋቀር ሰላሙ በለጠ እንዲጠናከር በማድረግ ለዜጎቹ ያለውን ተቆርቋሪነት ያሳያል።
ይሁን እና ብሔር ላይ የተመረኮዙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ጎልቶ የወጣበትን የሦስቱ ልዩ ኃሎች ገጽታ ከተጨባጭ ማብራሪያ ጋር ግዛቸው አበበ በዚህ መልክ አዘጋጅቶታል

ጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ የቤተ-መንግስቱን እድሳትና የፓርክ ግንባታ ሲጀምሩ ይህ ሥራቸው ለመቶና ለኹለት መቶ ዓመታት መታሰቢ እንደሚሆንላቸው አስረግጠው ተናግረው ነበረ። ብዙ መናፈሻወችን፣ ፓርኮችንና የውኃ ትርኢት ማሳያ ቦታወችን በዚህ ‘መታሰቢያን የማቆም’ በሚል መንፈስ መገንባቱን በሰፊው ሲያያዙት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች፣ በቢሊዮን የሚቆጠረውን ገንዘብ ስለሚገኙበት ምንጭ፣ መጠኑና ምንጩ ይፋ ያልተደረገውን ገንዘብ የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት እና የፋይናንስ ሕጎች በሚፈቅዱት አሰራር መሰረት ይፋ ማድግና ማስተዳርን ወዘተ…. የሚመለከቱ ጥያቄወች እየተነሱ ያለ ምላሽ አንዳንዴም ምን አገባችሁ በሚል ዘለፋ ታልፈዋል።

በዚህ ዓይነት አካሄድ ወደ ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት ጠቅላይ ሚ/ሩ ትርምስና አለመረጋጋቶችን፣ ግጭቶችንና በጭፍጨፋ ደረጃ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን አሳልፈው አሁን በምድር ብረት ለበስ ተሸከርካሪወች እና ታንኮች፣ በሰማይ ተዋጊ ጀቶች እና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች የተሳተፉበት ጦርነት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። ይህ በሰማይና በምድር እሳትን የሚተፉ በርካታ የጦርነት ማሽኖች በብዛት ጥቅም ላይ የዋሉበት የኃይል እርምጃ የሕግን የበላይነት ለማረጋገጥና ወንጀለኞችን እንደ ማደን ተደርጎ እንጅ የእርስ በርስ ጦርነት ተብሎ እንዳይጠራ ከፍተኛ የመገናና ብዙሐን ዘመቻ ተካሄዶበታል።

በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው በትግራይ ምድር የሚካሄድ ፍልሚያ የጠቅላይ ሚ/ሩ በብዙ መንገድ ቸልተኛ ሆኖ መቆየት ምን ዓይነት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን የሚያሳይ ፍጻሜ ከመሆኑ በተጨማሪ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት የዚችን አገር ሕልውና እንዲፈታተኑ አድርጎ ያዋቀራቸውን ሦስት ሰይጣናዊ ሰይፎችንና አደገኛነታቸውን ያጋለጠ አጋጣ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።

የክልል ልዩ ኃይሎች
የክልል ልዩ ኃይል የሚባል ታጣቂ ቡድን ለመጀመሪ ጊዜ የተዋቀረው በሶማሌ ክልል እንደሆነ ይታመናል። ይህ ልዩ ኃይል የተዋቀረው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተዋጊ ቡድኖችን ለመቋቋም ተብሎ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ የኢሕአዴግ አጋር ድርጅት የሆነው የእነ አቶ አብዲ ዒሌ የፖለቲካ ቡድን መሳሪያ በመሆን ተቃዋሚወቻውን በመምታት ስም ለሶማሌ ክልል ሕዝብ ሰይጣናዊ ሰይፍ ሆኖ የሚሰራ ኃይል ሆኖ ቀጥሏል። የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ቀስ በቀስ የፖለቲካ ቡድን መሣሪያ ከመሆን የአንድ ግለሰብ፣ የአቶ አብዲ ዒሌ መጠቀሚ ወደ መሆን ደረጃ ወርዶ ለመናገር የሚከብዱ ከፍተኛ ሰቆቃወችን የሚፈጽም ሰይጣናዊ ሰይፍ ወደ መሆን ደረጃም ደርሷል።

2010 ለውጥ መጣ መባሉን ተከትሎ አቶ አብዲ ዒሌ ተደመርኩ ብለው ራሳቸውን ከአዲሶቹ መሪወች ጋር ማስማማቱን ትተው ከቀድሞ ጌቶቻው ከሕወሐት አውራወች ጋር የመሞዳሞድ አካሄድ በመከተላቸው ልዩ ኃይሉ ከፍተኛ ሰቆቃወችን ፈጽሞ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን ብቻ ሳይሆን የዘርና የሐይማኖት ልዩነቶችን መሰረት ያረገ ጥቃት እና ውድመት አድርሶ ሰይጣናዊ ሰይፍነቱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያንም ጭምር መሆኑን በገሃድ አሳይቷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ወደ ክልሉ ገብቶ ነገሮችን እስኪቆጣጠር ሰይጣነዊ ሰይፉ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን ላይ ብዙ ጉዳት አድርሷል።

ጥቅምት ወር 2013 የመጨረሻ ቀናት ጀምሮ ደግሞ ሰይጣናዊ ሰይፍነቱትን የማሳየት ተራውን የትግራይ ልዩ ኃይል ተቀብሎታል። የትግራዩ ልዩ ኃይል ሰይጣናዊ ሰይፍነትቱ በዚህ ጊዜ በተግባር ይታይ እንጅ ሰይፉ መሳልና መዘጋጀት ከጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ ተቆጥሯል። በ2010 ዓም የመጨረሻ ወራት ላይ የተከሰተውን የስልጣን ሽግሽግ ተከትሎ የመጣው ጊዜ ደግሞ ሰይጣናዊ ሰይፉን የጥላቻና የጭካኔ ስልቶችን እንዲኖሩት ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራወች የተሰራበት ጊዜ ሆኗል። የጠቅላዩ መንግሥት በዝምታ ተመልክች መሆኑ ደግሞ የሰይፉን ባለቤቶች የልብ ልብ የሰጠና ባሰኛቸው ጊዜ የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ሆኖ እንዲሰማው አድርጓል። ሕወሐቶች የቀድሞ ጓዶቻውን የአሁኖቹን ብልጽግናወችን እንደ ሞኛ ሞኝ ፍጥረታት አድርገው እንዲያዩአቸው ሳደርግም አልቀረም። የአዲስ አበባና የመቀሌ ጨዋታ ለየቅል መሆን አንዳንዶችን ለመኮፈስ ሌሎችን ለስጋት ዳርጎ እንደነበረም ግልጽ ነው።

አዲስ አበባ ላይ መናፈሻወች፣ ፓርኮችና ውኃ የሚረጩ ጌጣጌጦች ሲሰሩ ትግራይ ውስጥ ልዩ ኃይል የሚባለው ክልላዊ ታጣቂ ቡድን የአገር መከላከያ ሊኖረው የሚገባውን ቁመና እንዲይዝ ከፍተኛ ስልጠናወች በጥድፊያ ይሰጡ ነበረ። ይህ የትግራይ ልዩ ሃይል ስልጠና የታንክ፣ የመድፉና የሌሎች ከባድ መሣሪያወችን አጠቃቀምንም ያጣቃለለ ሆኖ ይካሄድ እንደነበረ የክልሉ ፖለቲከኞች በቅርቡ ከሰጧቸው መግለጫወች መረዳት ተችሏል። አሁን ጦርነት በሚካሄድበት ጊዜ ግብግቡ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ጦር እና በትግራይ ክልላከያ ኃይል መካከል እንደሆነ ተደርጎ ነው በትግራይ ሚዲያወች ላይ በመነገርላይ ያለው።

አዲስ አበባ ላይ መናፈሻወች፣ ፓርኮችና ውኃ የሚረጩ ጌጣጌጦች ሥራቸው ተጠናቅቆም ሆነ ገና ሳይገባደዱ በከፍተኛ ሸብረብ እና በፈንጠዝያ ሲመረቁ በትግራይ በተከታታይ የተሰጡ የውጊያ ስልጠናወች የተከታተሉ የልዩ ኃይል አበላትና ኮማንዶ ተብለው የሰለጠኑ ታጣቂወች ከፉከራና ከቀረርቶ ጋር፣ በቁጣና በዛቻ ዲስኩሮች የምረቃ ስነ-ስርዓት ይካሄድ ነበረ።

አዲስ አበባ ላይ መናፈሻወች፣ ፓርኮችና ውኃ የሚረጩ ጌጣጌጦች ሲጎበኙና ፊልም ተሰርቶላው የጠቅላይ ሚ/ሩን ገጽታ መሳመሪያ የሚሆን ፕሮፓጋንዳ ሲሰራባቸው ትግራይ ውስጥ፣ በትንንሽም ሆነ በትልልቅ ከተሞች፣ በስቴዲዮሞችና በአደባባዮች ወታደራዊ ትርኢቶች ይኮመኮሙ ነበረ።

አዲስ አበባ ላይ መናፈሻወች፣ ፓርኮችና ውኃ የሚረጩ ጌጣጌጦች በጠቅላይ ሚ/ሩ እና በእንግዶቻቸው እየተጎበኙ ፎቶወች በፌስቡክ ላይ እንደ ጎድ እየተለቀቁ ስለ ምድራዊ ገነት ብዙ ወሬ በመንግሥትና በብልጽግና ሚዲያወች በሰፊው ሲወራ ትግራይ ውስጥ ግን አደገኛ ጉብኝቶች ይካሄዱ ነበረ። በነዚህ ጉብኝቶች ሰይጣናዊ ሰይፉን ደም የማጉረፍ ሥራውን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራወችና ምክክሮች ተካሂደዋል።

አሁን ቀስ በቀስ በመውጣት ላይ ያሉ መረጃወች ግልጽ እንደሚደርጉት፣ ከፌደራላዊ ሥልጣን ገለል የተደረጉት የሕወሐት ፖለቲከኞች እና ጡረታ የወጡ የጦር መኮነኖች የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ ኃላፊወች ጋር ቋሚ ግንኙነቶችን ያደርጉ እንደነበረ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰሜን ዕዝ የተለያዩ ክፍሎች በመሄድ ዱለታወችን ማካሄዳቸውን እያፈተለኩ ከሚወጡ ወሬወች መረዳት ይቻላል። የሰሜን ዕዝ አካል የሆነው የ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አባላት የነበሩ እና ከጥቅምት 24 የለሊት ሴራ አምልጠው አፋር የገቡ ወደ 11 የሚሆኑ ወታደሮች ለአማራ መገናኛ ብዙሐን ያሳወቁት ፍጻሜ የሚያረጋግጠው ይህን ሃቅ ነው።

ዕድኞቹ ወታሮች የክፍል ጦሩ አዛዥ የነበረው እና የኮሎኔልነት ማዕረግ የነበረው ግለሰብ ከጌታው ረዳ ጋር በቅርበት ይሰራ እንደነበረ፣ ጥቃቱ ሊፈጸም በጣም ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውት በነበረበት ጊዜ እንኳ አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ ጦር ክምፑ ጎራ ብሎ እንደነበረ፣ ጥቃቱ በተፈጸመበት ምሽት ከእነ ጌታቸው ረዳ ጋር ሲመሳጠሩ የነበሩት የክፍለ ጦሩ አዛዥና ሌሎች አመራሮች የለሊቱን ኦፕሬሽን መምራታቸው፣ የክፍል ጦሩ አባላት የነበሩና ከእነሱ ጋር ለመተባበር የተስማሙ ወታደሮችና አካባቢውን የከበቡ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት የክፍለ ጦሩን ወታደሮች ማጥቃታቸውን አጋልጠዋል።

ይህ እኩለ ለሊት ሲቃረብ በ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ላይ የተካሄደው የክፍል ጦሩ አባላት ተኝተው በነበሩበት ሰዓት መሆኑን፣ ጥቃቱ በእሩምታ ተኩስና በእጅ ቦምብ የታገዘ እንደነበረ ያመለጡት ወታደሮች ተናግረዋል። ድንገተኛ ጥቃት የተሰነዘረባቸው የክፍል ጦሩ ወታደሮች መሣሪያ አንስተው ራሳቸውን ለመከላከል ያደረጉት ሙከራ መሣሪወች የሚመቀጡበትን ቦታ አሰቀድመው በከበቡት ሴረኞች ተኩስ ሳይሳካ ቀርቷል። ከ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አባላት ስንቶቹ ተገድለው፣ ስንቶቹ ተማርከው፣ ስንቶቹ ደግሞ ከሃዲወች ሆነው በጓዶቻቸው ላይ የጥይት እና የቦምብ ጥቃቱን በማድረስ እንደተሳተፉ ታሪክ የሚነግረን ጉዳይ ይሆናል።
የሰሜን ዕዝ አካል በሆነው በ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ላይ የተሸረበው ሴራና የተካሄደው ጥቃት በተመሳሳይ ትግራይ ውስጥ በሚገኙ የሰሜን ዕዝ ሌሎች ክፍሎች ላይም በተመሳሳይ ሰዓት ተካሂዷል። ሴራው የሰሜን ዕዝን ቀላልና ከባድ የጦር መሣሪያወች ለመዝረፍ ብቻ ሳይሆን ከሕወሐት ጋር ተባባሪ አንሆንም ያሉ ወደ 30 ሽሕ የሚጠጉት የዕዙን አባላት በተለያዩ መንገዶች ከሥራ ውጭ ለማድረግም ጭምር ታቅዶ የተካሄደ መሆኑ የህወሐት አባላት ድምጺ ወያኔና ትግራይ ቴሌቪዥን ላይ በግልጽ ተናግረዋል።

የቀድሞው መምህርና ወደ በረሀ ገብቶ የድምጺ ወያነ ጋዜጠኛ የነበረው አቶ ሴኩ ቱሬ ከህወሐት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆኑት የሰሜን ዕዝ አባላት በጤናቸው ከትግራይ ከወጡ የሕወሐት ጠላት መሆናቸው አይቀርም በሚል እሳቤ ‘መብረቃዊ’ እርምጃ እንደተወሰደባቸው በግልጽ ተናግሯል። ይህ ግለሰብ በወታደሮቹ ላይ የተወሰደውን እርምጃ በግልጽ ለመናገር ሲቸገርና ሲንተባተብ የታየ ሲሆን ቆየት ብሎ የተወሰደውን እርምጃ ‘ዲሞብላይዝድ’ እና ‘ዲስቴብላይዝድ’ ሲል ጠርቷታል። ይህ በ30ሽሕ የዕዙ አባላት የሆኑ ወገኖቻችን ላይ የተካሄደው ከሥራ ውጭ የማድረግ አድርምጃ ምን ምን ያካተተ እንደነበረ በቅርብ ይፋ ይወጣል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።

የዕዙ ወታደሮች ባልታጠቁበት እና በተኙበት ሰዓት በእሩምታ ተኩስና በቦምብ የተቀነባበረ ቀጥቃት የተካሄደባቸው መሆኑ መጋለጥ መጀመሩን ተከትሎ በአሳፋሪ ሥራቸው የተደናገጡ የመሰሉት የትግራይ ባለሥልጣናት ከሕወሐት ጋር ተባባሪ አንሆንም ያሉ የሰሜን ዕዝ ወታደሮች በአንድ ካምፕ ውስጥ እንደ ምርኮኛ ተቀምጠው፣ በየቀኑ ደሮ ወጥና ጥብስ እየተቀለቡ፣ የቧንቧ ውሃ ሳይሆ የታሸገ ውኃ ብቻ እየጠጡ በምቾት ውስጥ ያሉ የሚያስመስል ዜና ሰርቶ አሰራጭቷል። ያም ሆነ ይህ የትግራይ ልዩ ኃይል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውን ምን ኣይነት ሰይጣናዊ ሰይፍ መሆኑን በሰፊው አሳይቷል።

አሁንም ልዩ ኃይሎች አጠያያቂ አቋም ይዘውና አጠያያቂ ተግባራትን እየፈጸሙ በየክልሉ ይንቀሳቀሳሉ። ዘርንና ጎሳን መሰረት አድርገው በየክልሉ የተመሰረቱት፣ ቀጣይ ምልመላወችንም ዘርንና ጎሳን መሰረት አድርገው በመጠናከር ላይ ያሉት ልዩ ኃይሎች ችግሮች ሲከሰቱ ወይም ክልሉን የሚመራው ቡድን ወይም ግለሰብ ሲያኮርፍ ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ በበቂ ሁኔታ ትምህርት ተገኝቶ ይሆን? ከዚህ በኋላስ በየክልሉ የተቋቋሙት ልዩ ኃይል የሚባሉት ቡድኖችና በነዚያ ክልሎች የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት ክፍሎች አብረውና ተስማምተው የሚኖሩት እንዴት ይሆን? ለመሆኑ ዘርንና ጎሳን መሰረት አድርገው የተቋቋሙትና በዘርና ጎሳ በተዋቀረ የፖለቲካ ቡድን የሚመሩት የክልሎች ልዩ ኃይሎችና ኢትዮጵያዊነትን እንግቦ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የመቆም ዓላማ ያለው መከላከያ ኃይል በጥርጣ ከመተያየት ነጻ ሊሆኑ ይችላሉን?

በኦሮምያ ያለው ልዩ ኃይል፣ መጤ የተባሉ ሰወች ከግለሰብ ጀምሮ በከተማና በወረዳ የሚኖሩ በጅምላ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ቤት ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም በቦታው ደርሶ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና ቤት ንበረታቸውን ከአጥቂወች የመጠበቅ ሥራወችን ለመሥራት ዳተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። የአርቲስት ሃጫሉን መገደል ተከትሎ ይህን መሰለ ንጹሐንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በብዙ ከተሞችና ወረዳወች፣ ለስምንት እና ለዐስር ሰዓታት በአንዳንድ ቦታወችም ለኹለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄዱ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ችግሮች በተከሰቱባቸው ቦታወች በመገኘት መከላከል ሳይችል ቀርቷል።

ይህን መሰል የልዩ ኃይሎች ልግመኛነት በቤኒሻንጉልና በደቡብ ክልል በዜጎች ላይ ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው ወቅቶች የታዩ ሲሆን ክልሎቹን የሚመሩት ዘርና ጎሳን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ቡድኖችም ልዩ ኃይሎቹን ለማሰማራትና ዜጎችን ከአጥቂወች ለመከላከል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች የየክልሎቹ ታጣቂወችም ጭምር እጆቻውን የነከሩባቸው እንደሆኑ የሚያሳብቁ ወሬወች በተደጋጋሚ ተሰምተዋል።

በሰኔ 2011 በአማራ ክልል ከተፈጸመወ ግድያ ጋር በተያያዘም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አፍራሽም ገንቢም ሚና እንደነበረው፣ ልዩ ኃይሉ ክፍፍል ውስጥ እንዲገባ መደረጉ እና በዚያ ደም አፋሳሽ ምሽት ልዩ ኃይሉ እንደ መሪወቹ ዝንባሌና ፍላጎት ተከፍሎ ዒላማ የተደረጉ መሪወችን ለመከላከልና ለማጥቃት ከዚህ አለፍ ብሎም እርስ በርሱ የተኩስ ልውውጥ ውስጥ መዘፈቁ፣ በዚህም የሞትና የመቁሰል ጽዋን መጎንጨቱ ታሪክ መዝግቦት ያለፈ ነገር ግ ያልተቋጨ የሚመስል ፍጻሜ ነው።

የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ፌደራል ፖሊስንና አግአዚ ኮማንዶን ማዕከላዊ ሥልጣኑን ከስጋት ነጸ ለማድረግ፣ የሚያምጽበትን ቡድንም ሆነ ግለሰብን ለማፈንና ለመደምስ ሲጠቀምባቸው የነበሩ መሣሪያወች ናቸው። የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት አባልና ኣጋር ብሎ ያዋቀራቸውን፣ ክልሎችን አፍኖ ለመግዛትና ለመዝረፍ የሚጠቀምባቸውን አሻንጉሊት ቡድኖች ለመጠበቅ፣ አመጽ ሲነሳም በእንጭጩ ለመቅጨት በየክልሎቹ የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን መጠቀሚያ ማድረጉ ከማንም የተሰወረ አይደለም። አዎ! በየክልሉ የሚገኘውና ልዩ ኃይል የሚባለው ታጣቂ ቡድን ለኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና አደገኛ ከሆኑት ሦስት ሰይጣናዊ ሰይፎች አንዱ ነው።
ሌሎቹን በሌላ ጊዜ እንመለስባቸዋለን። አሁን ሊነሳ የሚገባው ዋና ጥያቄ “የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ሰይጣናዊ ሰይፍ ይሆኑ ዘንድ የተዋቀሩት የክልል ልዩ ኃይሎች ለዲሞክራሲ፣ ለእውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲሁም ለዜጎች በፈለጉበት ቦታ በእኩልነትናት በሰላም ሰርተው ለመኖር አስፈላጊ ናቸውን?” የሚል ነው።
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com
—-ይቀጥላል—-

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com