በትብብር ለሚተላለፉ የሬዲዮ ዝግጅቶች መመሪያ ሊወጣ ነው

Views: 382

መቀመጫቸውን በውጭ አገራት አድርገው በኢትዮጵያ ባሉ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች በትብብር የሚዘጋጁ የሬዲዮ ዝግጅቶችን አሰራር አቅጣጫ የሚያሳይ መመሪያ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚያወጣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወንድወሰን አንዱዓለም ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

መመሪያው በውስጡ መቀመጫቸውን ውጭ አገር ባደረጉ የመገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በትብብር አገር ውስጥ ባሉ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች መተላፍ ይችላሉ አይችሉም የሚለውን፣ተጠያቂነታቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ፣የኤፍ ኤም ጣቢያዎቹ ከሚያስተላልፉት 18 ሰዓት ውስጥ ምን ያህል ሰዓት ወስደው መስራት እንደሚችሉ እና ከኤፍ ኤም ጣቢያዎቹ ‘ኤዲቶሪያል ፖሊሲ’ አኳያ እንዴት መስራት እንዳለባቸው የሚያመላክት እንደሆነ ነው ወንድወሰን የተናገሩት።

VOA DW እና BBC በአገራችን ባሉ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች የሬዲዮ ፕሮግራሞችን እያስተላለፉ የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ፕሮግራሞች በኢትዮ ኤፍ ኤም እና በአሐዱ ራዲዮ በኩል ይተላለፋሉ፤ ፕሮግራሞቹ መተላለፍ የጀመሩት በቀጥታ ከሬዲዮ ጣቢያዎቹ ጋር ባደረጉት ስምምነት ሲሆን መረጃን ማስተላለፋቸውን በቅንነት ብናየውም የሬዲዮ ጣቢያዎቹ እርማት መስጠት በማይችሉበት አግባብ በተለይ አሁን ካለንበት አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ያልተረጋገጡ፣የወገኑ፣የመረጃ ምንጫቸው ያልታወቁ መረጃዎችን በእነዚህ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ እየተሰራጩ እንደሆነ ወንድወሰን ተናግረው የመመሪያው መውጣት ወቅታዊ ነው ብለዋል።

የብሮድካስት አዋጁ በጣም የቆየ እና አዋጁ በወጣበት ወቅት እንደ አሁን በርካታ የግል የመገናኛ ብዙኃን ያልተስፋፉበት ጊዜ በመሆኑ እና የማስታወቂያ ሚኒስትር የመገናኛ ብዙኃኑን ይቆጣጠር በነበረበት ወቅት ሲሆን በአዋጁ ላይ በግልፅ የተፃፈ ነገር ባለመኖሩ ያልተከለከለ ነገር የተፈቀደ ነው በሚል አንድምታ ዝግጅቶቹ መተላለፍ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ግን እንኳን ተቀርፀው በሚተላለፍ ዝግጅቶች በቀጥታ በሚሰራጩ ዝግጅቶች በሚፈጠሩ ስህተቶች ጣቢያዎቹ ከተጠያቂነት ነፃ እንደማይሆኑ ከጣቢያቹ ጋር መነጋገራቸውን ወንድወሰን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የሬዲዮ ጣቢያች በጣቢያዎቻቸው ላይ ዝግጅቶቻቸውን የሚያቀርቡ የመገናኛ ብዙኃን ‘ኤዲቶሪያል ፖሊሲ’ ላይ ወሳኔ መስጠት ማለትም ይህንን ማቅረብ ትችላላችሁ ይህንን ማቅረብ አትችሉም ብለው መወሰን በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ፕሮግራሞቻቸው እንዲተላለፍ ማድረግ ከሙያ ሥነ ምግባር እንዲሁም ከህግ አንፃር ልክ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

የአሐዱ ራዲዮ ዋና አዘጋጂ ጥበቡ በለጠ ከእነዚህ የራዲዮ ጣቢያዎች ጋር በቀጥታ ተፈራርመው መስራት እንደጀመሩ ተናግረው በብሮድካስት ህጉ መሰረት ግን በሚያስተላልፏቸው ሃሳቦች ይዘት ተጠያቂ የምንሆነው እኛው ስለሆንን እና የእነሱ ተጠያቂነት ከእኛ ቀጥሎ የሚመጣ ስለሆነ አሁን ካለንበት ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ አኳያ ከ BBC ጋር ያለንን የሥራ ውል አቋርጠናል ብለዋል። ከ VOA ጋር አሁንም እየሰራን ብንገኝም ልክ እንደመጀመሪያው ሳይሆን የምሽት የዜና ሀሳባቸው ላይ ቀድመን መነጋገር ጀምረናል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን የሚገኙበት አገር የሚዲያ ነፃነት እና የሚዲያ የእድገት ደረጃ የቆሙለት ዓላማ ከእኛ አገር ጋር አብሮ የማይሄድ ስለሆነ በተለይ ልክ እንደዚህ ባለ አገር ችግር ውስጥ በምትገባበት ወቅት እንደነዚህ ካሉ የመገናኛ ብዙኃን ጋር መስራት እጅግ አስቸጋሪ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። እንደ እኔ የግል አስተያየት እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን ለአገር ውስጥ ጣቢያዎች የሥልጠና እና ሌሎች ሙያዊ እገዛዎች እንዲሰጡ እንጂ የሬዲዮ ዝግጅቶቻቸውን ባያስተላልፉ እመርጣለሁ ብለዋል ጥበቡ።

የግል የመገናኛ ብዙኃን ከእነዚህ አይነት ጣቢያዎች ጋር አብሮ የሚሰሩት ካሉባቸው የገንዘብ አቅም ወስንነት እንደሆነ ጥበቡ ገልጸው መንግሥት ለግል የመገናኛ ብዙሃን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

ከውጭ አገር የሚገቡ የስቱዲዮ እቃወች ላይ የሚጣሉ ቀረጦች እና ለማስታወቂያ ከሚበጀተው 100 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዓመታዊ የመንግስት በጀት ውስጥ የግል የመገናኛ ብዙኃንን ያላካተተ መሆኑ ከእንደነዚህ አይነት የመገናኛ ብዙኃን ጋር እንድንሰራ ያስገድደናል ሲሉም ጥበቡ ሀሳብ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com