የተቋረጠው የሥነ ልሳን ሕክምና ትምህርት ውዝግብ አስነስቷል

Views: 238

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ፍላጎት የትምህረት ክፍል ይሰጥ የነበረው የሥነ ልሳን ሕክምና ወይንም ‘የስፒች ቴራፒ’ ትምህርት በመምህራን እጥረት ምክንያት ለሦስት ዓመታት ያህል አዲስ ተማሪ ሳይቀበል የቆየ መሆኑ ውዝግብ አስነስቷል።

የሥነ ልሳን ሕክምና ትምህርት ለሦስት ዓመታት የሚሰጥ የትምህርት መርሃግብር ሲሆን የትምህርት ክፍሉ በ2008 እና በ2009 የትምሀርት ዘመን ተማሪዎች ተቀብሎ የኹለቱንም ዓመት ተማሪዎች በአንድ ላይ በ2011 አስመርቋል። ይሁን እንጂ በ2008 ገብተው በ2010 መመረቅ የሚገባቸው ተማሪዎች ሳይመረቁ መዘግየታቸውን አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ለማወቅ ተችሏል።

የትምህርት ክፍሉ በበኩሉ እንደተባለው ለሦስት ዓመታት ሳይሆን ለአንድ ዓመት ብቻ የተቋረጠ እንደሆነ እና ይህም ደግሞ ከመምህራን ዕጥረት የተነሳ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። አያይዞም በ2013 የትምህርት ዘመን እንደገና እንደሚጀመር የትምሀርት ክፍሉ ኃላፊ እና መምህር የሆኑት ዓለማየሁ ተክለማርያም (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በትምህርት ክፍሉ ያጋጠመውን የመምህራን እጥረት ለመፍታት ከውጭ አገር በመጡ በጎ ፈቃደኛ መምህራን በመታገዝ ተማሪዎችን ማስመረቃቸውን አስታውቀው በያዝነው የ 2013 የትመህርት ዘመን ግን ሙሉ በሙሉ መምህራን በመቅጠር ችግሩን ፈተናል በትምህርት ዓመቱ ኹለተኛው ወሰነ ትምህርት ደግሞ የኹለተኛ ዲግሪ መርሃግብር ለመጀመርም ከዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውሳኔ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።

የስነ ልሳን ሕክምና ወይንም ‘ስፒች ቴራፒ’ በተለያዩ አደጋዎች የመናገር ክህሎታቸውን ላጡ አዋቂ ሰዎች እና ለህፃናት ልጆች ደግሞ በአእምሮ እድገት ውስንነት እንዲሁም ከላንቃ ክፍተት እና ከከንፈር መሰንጠቅ ችግር ጋር እና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ሲወለዱ ጀምሮ ለሚፈጠር የንግግር ክህሎት ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ሕክምና ነው።

በኢትዮጵያ የሥነ ልሳን ሕክምና በዋነኛነት በመንግሥት ደረጃ የሚሰጠው በየካቲት 12 ሆስፒታል ብቻ ሲሆን አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የግል የሥነ ልሳን ሕክምና መስጫ ተቋም ይሰጥ የነበረው የሥነ ልሳን ሕክምና ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሕክምናው መሰጠት እንዳቆመ በየካቲት 12 ሆስፒታል የሥነ ልሳን ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ቢንያም ገብረዓብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በየካቲት 12 ሆስፒታ አንድ ሺሕ 50 ያህል የተመዘገቡ ታካሚዋች እንዳሉም ገልፀው በሆስፒታሉ ያለነው የሕክምና ባለሞያዎች ግን ኹለት ብቻ ነን ብለዋል።

በ 2011 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከልዩ ፍላጎት የትምህረት ክፍል ተመርቀው ከወጡ የሕክምናው ባለሞያዎች መካከል ኹለቱ በየካቲት 12 ሆስፒታል ፣ኹለቱ በጅማ ሆስፒታል፣ ኹለቱ በመቀሌ ሆስፒታል እና አንዱ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት እንደሚሰሩ ቢንያም ተናግረው ቀሪዎቹ ግን ከተመረቁበት ሙያ ጋር ያልተያያዘ ሥራ እየሰሩ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ከስድስት እና ከሰባት ዓመታት በፊት ምንም አይነት የሥነ ልሳን ሕክምና ባለሙያ እንዳልነበረ እና የመጀመሪያዎቹ ባለሙያዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልከው እንደተማሩ ያስታውሳሉ። በአሁኑ ሰዓት ግንባር ቀደም በዘርፉ ሕክምና እየሰጡ የሚገኙት ብርሃኔ አበራ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ትምህርቱን በአሜሪካ አገር እንደተከታተሉ ተናግረዋል።

ብርሃኔ አክለውም ሕክምናው ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ እና በመርፌ ወይንም በመድሃኒት ታግዞ የሚሰጥ ሕክምና ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ የለውም ብለዋል። በተለይ ደግሞ ከላንቃ ክፍተት እና ከከንፈር መሰንጠቅ ችግር ጋር ለሚወለዱ ሕፃናት የካቲት 12 ሆስፒታልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሆስፒታሎች ከሚያደርጉት የቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ ልጆች የንግግር ክህሎት ችግር ስለሚጋጥማቸው ሕክምናው ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ ሕፃናቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት ከበለጠ አፍ የመፍቻ ዕድሜያቸው ስለሚያልፍ ሕክምናውን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል ሲሉ ሙያዊ አስተያተቸውን ሰጥተዋል ብርሃኔ።ከችግሩ ስፋት እና ክብደት አኳያ ደግሞ በቂ ባለሙያ አለመኖሩንም አክለው አሁን በአገራችን ላለው 110ሚሊየን ለሚገመት የሕዝብ ቁጥር 16 የሥነ ልሳን ሕክምና ባለሙያ ብቻ በቂ እንዳልሆነም አንስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com