ተማሪዎች ሰርቪስ እንዲጠቀሙ አስገዳጅ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

Views: 435

በአዲስ አበባ ላይ የሚገኙት ሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የትራፊክ መጨናነቅን ከማስቀረት አንፃር የተማሪዎች መጓጓዧ ሰርቪስን እንዲጠቀሙ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ እንደተዘጋጀ እንደሆነ እንደሆነ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ከፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ረቂቅ መመሪያው እንዲወጣ እየተሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሄርጳ ትምህርት ሲጀመር በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ከመቅረፍ አንፃር ከፍተኛ ሚና አለው ተብሎ ታስቦ የቀረበ የመፍትሄ ሐሳብ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሄርጳ እንደተናገሩት ይህ ሐሳብ መመሪያ ሆኖ ቢፀድቅ እና ሁሉም ተማሪ የተማሪዎችን ሰርቪስ እንዲጠቀሙ ቢደረግ ከመንገድ እና ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ከመቅረፍ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋልም ብለዋል።

አብዛኛቹ በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በቂ ቦታ እንደሌላቸው እና አንድ ህንፃ ተከራይተው የሚሰሩ ብዙ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ይታያል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህ ደግሞ በትምህርት ቤት መግቢያና መውጫ ሰአት ላይ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ስለሌለ መንገዶቹ እንዲዘጋጉ ያደርጋልም ብለዋል።

ይህ የትራፊክ መጨናነቅ በብዛት በግል ትምህርት ቤቶች ላይ እንደሚስተዋል ይታወቃል ለአብነትም በአንድ ትምህርት ኹለት ሺሕ ተማሪዎች ቢኖሩት እያንዳንዳቸው በግል መኪና የሚመጡ ከሆነ ኹለት ሺሕ መኪናዎች በመግቢያና በመውጫ ሰአት ላይ የትራፊክ መጨናነቅ እንዲኖር ደርጋሉ።

ነገር ግን እነዚህን ተማሪዎች 40 ሰው የሚይዘው የተማሪዎች ባስ ብንጠቀም በ50 ባስ ብቻ ተማሪዎቹን ማጓጓዝ እንችላለን በኹለት ሺሕ መኪና እና በ 50 ባስ መካካል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት እንዳለ ይታወቃል ይህ ደግሞ በትራፊክ መጨናነቁ የፓርኪንግ ሁኔታ የነዳጅ ፍጆታን ከመቀነስ አንፃር ያለውን ጥቅም ከፍተኛ ነው።
ለተማሪዎችም አብረው ወደ ቤት ሲሄዱ ከቤት ሲመጡ በባስ ውስጥ ከትምህርት ውጪ እንዲቀራረቡ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

ምናልባት ይሄን ለማስፈፀም ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው የባስ እጥረት ሊሆን ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ ለከተማው ካለው ጥቅም አንፃር ከቀረጥ ነፃ ባሶች የሚገቡበትን ዕድል ለማመቻቸት ቢሞከር ሊስተካከል ይችላልም ብለዋል።

እንደ ሐሳብ የቀረበው የግል ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ቤት አቅርቦት ታስቦ ማቅረብ እንዲችሉ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደግሞ መንግሥት ባሶችን እንዲያስፋፋ ማድረግ ነው ለትምህርት ቤቱ በቅርብ እርቀት የሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ በእግር ቢሄዱ የሚል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ይህ ልምድ በሌሎች ባደጉትም ባላደጉም አገራት ለአብነትም በአሜሪካ በደቡብ አፍሪካ የሚተገበር እንደሆነና በሚተገበርባቸው አገራትም ውጤታማ እንደሆነ እንደሚታወቅ ተናግረዋል።

የመንገድን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር የትራፊክ ፍሰቱ መቀነሱ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት። አክለውም ይህ መመሪያ ቢፀድቅ ከትራፊክ ፍሰት ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ይቀርፋል ሲሉ ተናግረዋል።

ተጠሪነታችን ለትራንስፖር ሚኒስቴር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ይህንን ሐሳብ ይዘን ለትራንስፖርት ሚኒስተር ለማቅረብ እና አስገዳጅ መመሪያ ሆኖ እንዲፀድቅ እየሠራን ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያጋገረቻቸው ትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር ፍቃደስላሴ ደበላ እንዳሉት ይህ ሐሳብ ወደ መመሪያ ቀርቦ ተግባራዊ ቢደረግ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያለውን መጨናነቅ እና አደጋን ከመቀነስ አንፃርም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ለከተማችን ላይ የትራንስፖርት ችግር እንዳለ ይታወቃል ያሉት ኃላፊው ይህ ሐሳብ መመሪያ ቢሆንና ተግባራዊ ቢደረግ የትራንስፖርት ችግሩን ይቀርፋል ብለዋል።
የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ፣የካርቦን ልቀትን ከመቀነስ፣አደጋን ከመቀነስ አንፃርም መኪናዎች አለመብዛታቸው ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com