የእለት ዜና

ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጠው አዲሱ ብድር ተግባራዊ አልተደረገም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያበድሩትን የብድር መጠን ከፍ እንዲያደርጉ የሚል መመሪያ ቢያወጣም ተግባራዊ እንዳልተደረገ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና የግሉ ዘርፍ አማካሪ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች ከሚያበድሩት ዓመታዊ ብድር አምስት በመቶ የሚሆነውን በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ግለሰቦች እንዲያበድሩ የሚል መመሪያ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ አውጥቶ ካለፈው ከሐምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ቢባልም ተፈፃሚነቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ግለሰቦች ከባንኮች ብድር ሲወስዱ ተንቀሳቃሽ ንብረቶቻቸውን እንደ ማስያዣ መጠቀም እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል። ይህ ማለት ተሸከርካሪዎች፣ ትራክተሮች ወይንም እንደ መጋዘን ያሉ ግንባታዎችን እና የአዝዕርት እህሎችን ጭምር ለማስያዣነት ማቅረብ እንደሚችሉ ተቀምጧል።

ከባንኮች በቀጥታ ብድር ማግኘት የማይችሉ አርሶ አደሮች እና ትንንሽ በሆኑ የግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማለትም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ከሆኑ አበዳሪዎች ብድር እንዲያገኙ ይደረጋል። ለተቋማቱ ደግሞ ባንኮቹ ብድር በመስጠት ለተበዳሪዎቹ ገንዘቡ ተደራሽ እንዲሆን እንዲያደርጉ መመሪያው ላይ ተካቷል።

ባንኮች ብድር ከሚሰጧቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የግብርናው ዘርፍ ቢሆንም ግን የሚሰጠው የብድር አቅርቦት አነስተኛ ነው ያሉት የዘመን ባንክ ፕሬዘዳንት ደረጀ ዘበነ ናቸው። ለዚህ እንደምክንያት የሚነሳው ባንኮች ብድር በሚሰጡበት ወቅት እንደ መያዣ ለሚጠየቁ ሃብቶች የግብርናው ዘርፍ ቋሚ የሆነ ሀብት ማቅረብ ስለማይችል እና የግብርና ምርቶች ሁሌም አደጋ ውስጥ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እንደሆነ ታውቋል።

ይህ ማለት ባንኮች ሲያበድሩ የሚያበድሯቸውን ዘርፎች የአደጋ ተጋላጭነት እንዲሁም የሚያሲዙትን ንብረት ቋሚነት ያጣራሉ። ስለዚህ የግብርና ምርቶች ደግሞ የዓየር ንብረት ለውጥ፣ የገበያ ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ማለት እንዲሁም ሌሎች ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምርታቸው ላይ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል በዘርፉ ያሉ ሰዎች ለማቅረብ የሚችሉት ማስያዣ ቋሚ አለመሆኑ የሚያገኙት የብድር መጠን ዝቅ አድርጎባቸዋል ነው ያሉት ደረጀ። ነገር ግን የግብርናው ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ ይህ አዲስ መመሪያ መውጣቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና የግሉ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ደምስ (ዶ/ር) የመመሪያው መውጣት ጠቀሜታ ላቅ ያለ እንደሆነ ገልጸው የግብርናው ዘርፍ እስከዛሬ ድረስ የሚያገኘው የብድር መጠን ከ 10 በመቶ የማይበልጥ ነበር ብለዋል። ይህንንም የብድር መጠን የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከልማት ባንክ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል። የግል ባንኮች ድርሻ ከአንድ በመቶ ያነሰ ነበር ነው ያሉት።በተቃራኒው ለወጭ እና ገቢ ንግድ አቅራቢዎች ደግሞ 48 በመቶ እንደሚበድሩ ነው ገለጹት።
ነገር ግን ይላሉ ደምስ (ዶ/ር) 80 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ ለሚሸፍነው እና እንደ እኔ እምነት የአገሪቱም 50 በመቶ ኢኮኖሚ ለሚያንቀሳቅሰው የግብርናው ዘርፍ 10 በመቶ የሚሆን ብድር ምንም ማለት አይደለም ነው ያሉት። አሁን የግል ባንኮች የሚሰጡት ብድር አምስት በመቶ መሆኑ ማለትም ከአምስት እጥፍ በላይ እንዲያድግ መደረጉ በጣም ጥሩ የሚባል ለውጥ እንደሆነም ተናረዋል።

ቢሆንም ግን የባንኩ ሴክተር ከግብርናው ሴክተር ባለሙያመዎች ጋር በደምብ ተቀምጦ እየሠራ አይደለም። መሰረታዊ የልማት ሥራ ለሚሰሩት እነዚህ የግብርናው ዘርፍ ባለሙያች የገንዘብ ችግር ሊፈታ ይገባል። ለብድር እንደማስያዣ ለሚነሳው ጥያቄ ደግሞ መሬትን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ የሆኑ ንብረቶች ማለትም እንደ የቁም ከብት ያሉ ንብረቶችን መጠቀም እንደሚቻል በመመሪያው መቀመጡ እንደ ለውጥ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!