አገረ ሰላም የት ነው?

Views: 624

አንድ ወር ሊሞላው በቀናቶች ልዩነት የተጠናቀቀው እና በፌደራል መንግሥት በኩል የተካሔደው የሕግን የማስከበር እንቅስቃሴ በርካታ አዳዲስ ጉዳዮችን ሲያሰማን እና ሲያሳየን ሰነባብቷል። ከተፈጠረው የሰሚን ጆሮ ጭው ከሚያደርገው በሰሜን ዕዝ ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት እስከ ማይካድራ ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ድረስ ምን አይነት ጉድ ነው እየተከናወነ ያለው የሚል ጉዳይ እንድናነሳ እና እንድንነጋገርም አድርጎን ቆይቷል።

በዚህ ሕግ የማስከበር ዙሪያ ከሑመራ እስከ ዳንሻ፤ ከሽሬ እስከ አዲ ነብርዒድ፣ ገመሐሎ፤ ከቅድስት ከተማዋ አክሱም እስከ ታሪካዊቷ አድዋ ድረስ ያልተዳሰሰበት እና የባሩድ ሽታ ያልሰነፈጠበት አካባቢ መስማት ከአስቸጋሪ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ልብ ይሏል።

የሆነው ሆኖ ታዲያ የፌደራል መንግሥት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የሕግ ማስከበሩን እርምጃ በተቀናጀ እና ንፁሐን በማይጎዱበት መንገድ እንዲያከናውነው ሆኗል። ይህም ታዲያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት በሕግ ማስከበሩ እርምጃ ወቅት ንጹሐን እንዳይጎዱ በሚል ጥንቃቄ በመደረጉ የእርምጃው ጊዜ ሊረዝም መቻሉን ያወሳሉ። ‹‹ላለመግደል ነው የምንታገሰው›› የሚል ንግግራቸው ከጠቅላይ ሚንስትሩ እና ከአማካሪያቸው ማሞ ምህረቱም ዘንድ የሚነገሩ ቃላቶች ሆነውም ሰንብተዋል።

ይህ በሕወሓት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የተለያዩ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩበት እና በርካታ ውይይቶችም እንዲደረጉበት በመደበኛም ሆነ በኢመደበኛ አካሔድ በሮችን ከፍተው ነበር። በመገናኛ ብዙኃንም ረገድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሲቀሩ የወጭ አገራት እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ኹነቱን ከአንድ ወገን በመዘገብም ትዝብትን እና ለአንድ ቡድን ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ድብቅ አጀንዳ ያሳዩበት አጋጣሚም ነበር።

በሞት ሽረት ተጋድሎ ታዲያ በሳምንታት ውስጥ መጨረሻው ምዕራፍ ተባለለት የትግራይን መናገሻ መቐለን የመያዝ እና ከሕወሓት ቁጥጥር ሥር ነጻ የማውጣት ተልዕኮም በሦስተኛው ምዕራፍ የተካተተው ዋነኛው እና ትልቁ ነው። ታዲያ በዚህ ውስጥ መቐለን በእርግጥም ነጻ ከማውጣት ባለፈ በዋናነት አጥፊ ተብለው በሕግ እየተፈለጉ ያሉ የሕወሓት አባላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሐሳብን የሰነቀ እና ከፍተኛ ቆራጥነትም የተስተዋለበት እና ሰፊ ተጋድሎም ተደረገበት እንቅስቃሴ ነበር።

ምንም እንኳን ንጹሐንን ታሳቢ ያደረገ እና የአገርን ሀብት ከግምት ውስጥ የከተተ በሰለጠነ አካሔድ የተተገበረው እርምጃ መቐለን እና ነዋሪዎቿን ከጥፋት ቢታደግም ተፈላጊዎችን ግን እንደታሰበው በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሳይቻል ቀርቷል።

እንደለፋ እና እንደደከመ ሰው ሁኔታው ልብን የሚያዝል ሐሞትን የሚያፈስ ቢሆንም ወታደርነት በራሱ ጽናትን ከትጥቁ እንደ አንዱ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሙያ ነው እና በዚህ የሚፈቱ አልሆኑም። በመሆኑም መቐለ ወይም ሞት ሲል የነበሩት የሕወሓት አመራሮችም መናገሻቸውን ትተው (ምናልባትም ድጋሚ የማየት እድል ሳይገጥማቸው ግብዓተ መሬታቸው ሊፈጸም ይችላል) በቅርብ ርቀት ግን ደግሞ በሰንሰለታማ ተራሮች ወደ ተከበበችው አካባቢ ‹‹አገረ ሰላም›› ተብላ ወደ ምትታወቀው ስፍራ ማፈግፈጋቸውን እና መከማቸታቸው ይፋ ተደርጓል።

ይህ ታዲያ ሕወሓት ከትግል ዘመኑ በኋላ አስቦትም ሆነ ዞር ብሎ ተመልክቶት የማያውቀው ስፍራ ነው የሚሉ እና ስፍራውን በእርግጠኝነት የሚያውቁ ነባር ሕወሓት ታጋይ ሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ፍሰሀ በርሔ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይናገራሉ።

አገረ ሰላም ከትግራይ መናገሻ መቐለ ወደ አቢ አዲ መንገድ ሰንሰለታማ አካባቢ ተከትላ ከትማ ምትገኝ ስፍራ ለመሆኗ ይነገርላታል። በ50ዎቹ ኪሎ ሜትሮች ከመቐለ ርቃ የምትገኘው አገረ ሰላም እንዴት በሕወሓት በኩል ተመራጭ ሆነች የሚለው ጥያቄም ይነሳል።

ስፍራውን እንደ እጃቸው መዳፍ ያህል የሚያውቁት ኮሎኔሉ ታዲያ ምላሻቸውን ሲሰጡ፤ ስፍራው በተራራዎች ከመከበቡ ባለፈ ውስጡ ጠንካራ ምሽጎች እና ዋሻዎች ለጥቃት አመቺ ያልሆኑ መደበቂያዎች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ለሕወሓት ማፈግፈጊያ እና መከማቻ ግንባር ቀደም ተመራጭ መሆኑን ይናገራሉ።

በአካባቢው አረንጓዴ ስፍራ እና ልምላሜ ከመታየቱ ባለፈ ለመኖር እና ለጥቂት ጊዜ ሕወሓት ተቀምጦ አቅሙን ሊያደራጅ የሚችልበትም ስፍራ ይሆናል የሚሉ መረጃዎችንም ኮሎኔሉ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሕወሓት ካለው ጸባይ እና አቅም አንጻር አንድ ቦታ ሰፍሮ የመቆየት እና ይዞታውንም አስከብሮ ማስቀጠል አቅምም ሆነ ወኔ ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ያለበትን አገረ ሰላም ተራራማ አካባቢዎች በመጠቀም ወደ ሌላ ስፍራዎች ሊዘዋወር እና አድራሻውን ሊያጠፉ ስለሚችል መንግሥት ፋታ እና የትንፋሽ መሰብሰቢያ ጊዜ ሊሰጣቸው አይገባም ሲሉም ይናገራሉ።

አገረ ሰላም ካለው የተያያዙ ተራራማ መልክዓ ምድር የተነሳ ለወታደራዊ ስልት ጠቀሜታው ላቅ ያለ መሆኑንም የውትድርና አዋቂዎችም ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በእርግጥም መንግሥት እያካሔደ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ በተለይም ደግሞ ተፈላጊዎችን የመያዝ ሥራውን ሂደት ፈታኝ ሊያደርገው እንደሚችልም ይጠበቃል።
ዶጋ ተምቤን፣ አቢ አዲ፣ ማይጨው እነዚህን አካባቢዎች የከበበው ሰንሰለታማው ተራራ በአገረ ሰላም ተሸሽገው ለሚገኙት የሕወሓት አባላት አድራሻቸውን ቀይረው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች እንዲሸሹ ሊያግዛቸው እንደሚችልም አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በርካታ የትግራይን አካባቢዎች መንግሥት በቁጥጥር ሥር ከማዋሉ ጋር ተዳምሮ ሕወሓት ሽሽቱ ከጓሮ እንደማያልፍ የሚያሳብቅ ሁኔታ ቢፈጠርም አገረ ሰላምን መምረጡ ግን በቂ መሸሸጊያ ለጊዜውም ቢሆን አገኛለሁ በሚል በትግል ጊዜውም ቢሆን የሚጠቀምበት ስፍራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በፌደራል መንግሥት በኩል ያለው የከበባ ሁኔታ በወታደራዊ ቴክኒክ በተለያዩ ክፍሎች ቢከፈልም እና ፌደራሉም ኃይል በየትኛው ደረጃም ቢሆን በአስቸኳይ የሚያጠናቅቅበት እና ተፈላጊ ናቸው ያላቸውን ሰዎችም በቁጥጥር ሥር የሚያውልበት መንገድ ሊፈጥን እንደሚገባ ይነገራል።

ከዚህ ቀደም በካርታ ላይ እንኳን ስሟ ተሰምቶም የማትታወቀው በደቡባዊት መቐለ የምትገኘው አገረ ሰላም የበርካቶች ዐይን እንዲያርፍባት እና ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም ዐቀፍ ድረስ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ በአንክሮ የሚከታተሉ ሁሉ ጆሯቸውን እና ትኩረታቸውን የሰጧት አነስተኛ ግን ደግሞ ሥሟ የገዘፈ ስፍራ ሆናለች።

ይኸው ጉዳይ ታዲያ እንዲያው አገረ ሰላም ምን ብትሆን ነው? የሚለው ጥያቄን ቢያስነሳም ከላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው በትላልቅ ተራሮች የተሸፈነው እና በጉያቸው አቅፈው የያዙት ዋሻ በርካቶችን ሊሸሽግ እና በየትኛውም መንገድ ከሚሰነዘረው ጥቃት እና የመሣሪያ አረር ሊታደግ ምቹ መሆኑ እንደሆነ ይነገራል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com