ንቅናቄና ‹አነቃናቂዎቹ›

Views: 223

ዜጎችና የሲቪክ ማኅበራት በሚኖሩበት አገር ለውጥን ማምጣት ሲሹ ከሚያደርጓቸው ተግባራት አንዱ ንቅናቄ ነው። ይህም ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ለመቀስቀስ፣ ውሎ የሚያድር ተጽእኖ ለማሳደርና ጫና ለማድረግ የሚረዳ ነው። ታድያ በዚህ ውስጥ የመንግሥት ተሳትፎና አጋዥነት ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው።

በአገራችን እንዲሁም በዓለማቀፍ ደረጃ የተለያዩ ንቅናቄዎችን በተለያየ ጊዜ ተመልክተናል፤ አሁንም አሉ። በቅርቡ የነበረው የ16 ቀን ንቅናቄ ወይም አክቲቪዝምም ለዚህ ተጠቃሽ ነው። የሴቶችን ጥቃት እናስቁም በሚል የወንዶችን አጋርነት የሚያጠይቀው የነጭ ሪቫን ቀን ባሳለፍናቸው ኹለት የተጠጉ ሳምንታት ሲታሰብ መቆየቱንም ልብ ይሏል።

ከአራትና አምስት ዓመት በፊት ይህን ንቅናቄ አስመልክቶ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ በሥራ አጋጣሚ ለመታደም እድሉን አገኘሁ። አዳራሹ የአገር ባህል ልብስ በለበሱና ልጇን እንደዳረች እናት እንግዶች ለማስተናገድ ሽር ጉድ የሚሉ ሴቶች በብዛት ይታዩበት ነበር። ከጣት ቁጥር የማይዘሉ ወንዶች ከብዙ ሴት ታዳሚዎች መካከል አሉበት። አሁን የማልጠቅሰው አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ክፍል ነው ያንን መሰናዶም ያዘጋጀው።

በመድረኩ አሳዛኝ ታሪኮች ተነግረዋል፤ ያንን ተከትሎ ያለቀሰና የተቆጣ አለ። ሻማ/ጧፍ ማብራትና ‹የሴቶችን ጥቃት እቃወማለሁ› ብሎ ቃል መግባት ሌላው የመሰናዶው አካል ነው። ሆነ። ዝግጅቱ አለቀ፤ እንግዶች ተሸኙ፤ አበቃ።

በቀጣዩ ዓመትም አጋጣሚ ሆኖ ያው ተቋም ባዘጋጀው መድረክ ላይ ታደምኩ። ጊዜ ወደኋላ የተመለሰ ይመስል ካለፈው ዓመት ጋር ተመሳሳይ ኹነት ተደረገ። አጋፋሪዋ የቢሮው ኃላፊም ባለፈው ዓመት ላይ የነበሩት ሴት ናቸው። መድረኩ በየዓመቱ የመሰባሰቢያና የመገናኛ ፌስቲል እንጂ በፍጹም ለውጥ ለማምጣት ታስቦ የተደረገ አይመስልም። ከዛ በቀጠለው ዓመት ያው ኹነት ተሠልሶ ስመለከት ግን ለመድኩት መሰለኝ፤ ተውኩት።

ሰው በዓል ጠብቆ ቢያከብር ለማስታወስ፣ ዝክር ቢዘክር ለበረከት፣ ደግሶ ቢያበላ በገንዘብ ለማይገዛ የሕሊና እርካታ ነው። ለሌላውም እንዲህ ውጤት ይኖረዋል። እንዲህ ወቅትን ጠብቆ የሚኖር ንቅናቄ ግን ትርፉ ምን እንደሆነ ግራ ያጋባል። ችግሩ ከንቅናቄው እንዳልሆነ እሙን ነው። ለአጭር ጊዜ የሚደረጉ ንቅናቄዎች አሉና፣ ለምን ለአጭር ጊዜ ሆነ ለማለት አይደለም።

ሆኖም ግን ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ጠንከር ያለ አሻራ ማሳረፊያ ሰሞን ማድረግም ይቻላል። ሆኖም በእነዚህ በተለይም ሴቶችን በሚመለከት ባሉ ንቅናቄዎች ‹ነቅናቂ› ሆነው የተሰየሙት ላይ ብዙ ማስተካከያ ሳያስፈልግ አይቀርም። እንደ አፍሪካውያን የአገር መሪዎች ለበርካታ ዓመታትም ተመሳሳይ ሰዎች፣ ተመሳሳይ ሥራን ያለለውጥ እየሠሩ መመልከትም ደስ አይልም።

በጀቱም፣ አቅምና ጉልበቱም ያለባቸውና ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ‹ንቅናቄያችን ምን አፈራ?› የሚለውን በሚገባ መቃኘትና መጠየቅ አለባቸው። ትልቅ ሐሳብና ሥራ ተሸክመው ካልሠሩት፣ ግዙፍ ግብ ይዘው ከግባቸው ለመድረስ በዓመት እንኳ ሩብ እርምጃ ካልተራመዱ፣ ንቅናቄያቸው በጉልበትም በገንዘብም ወጪ ወጥቶበት ምንም ትርፍ ካላስገኘ፣ ‹‹ነቅናቂዎች ሆይ ንቅናቄውን ልብ በሉ›› ልንል ሳይገባ አይቀርም።

ትክክለኛና እውነተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአንድ የንቅናቄ ሐሳብ መነሻነት ዓለም የተቀየሩ መልኮች አሏት። ቀላልና ተራ ነገር እንዳይደለ በዚህ እናውቃለን። ‹ነቅናቂ እኛ ነን!› የሚሉ ግን፣ እርምጃቸውን ልብ እንዲሉ አደራ ማለት፣ ማስታወስና ማሳሰብ ያሻል።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com