ትግራይን መልሶ የማቋቋም ቀጣይ ሥራ

Views: 260

በሕወሓት የቀድሞ አመራር ሥር አባል የነበሩት እና ከአገራዊው ለውጥ በኋላ ወደ አገር ተመልሰው የትግራይ ትብብር ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴት)ን አቋቁመው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ፓርቲ እየመሩ ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር) ሕወሓት ሲመሰረት ለመልካም አላማ ነበር ይላሉ። በዚህ ሂደት ግን ሥልጣን መንበሩን ከተቆናጠጡ በኋላ ብልሹ አሰራሮች ሥር እየሰደዱ በመምጣታቸው ከፓርቲው መለያታቸውን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።

ሕወሓት በተከተለው ብልሹ አሠራር እራሳቸውን ከፓርቲው እንዳገለሉ የሚናገሩት አረጋዊ ሕወሓት በርካት ሕገ ወጥ ሥራዎችን ሲያከናውን ለዓመታት እንደቆየ በፓርቲው ውስጥ ሆነው በቅርበት ከሚያውቁት በመነሳት ያብራራሉ።

የሕወሓት ብልሹ አሠራር ዓመታትን ከዘለቀ በኋላ ዋና አላማውን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ትግራይን መገንጠል እንደነበር አስታውሰዋል። 27 ዓመታትን በመንግስትነት ቆይቶ በሙስና እና በሰብኣዊ መብት ጥሰት ከተጨማለቀ በኃላ በረሃ እያለ ያለመውን እኩይ አላማውም ከማእከላዊ መንግሥት ከተገለለበት በ ላለፉት ኹለት ዓመታት ላማሳካት ደፋ ቀና ሲል መሰንበቱን ያበሳሉ።

በዚህም መታየት የጀመረውን የለውጥ አየር በትግራይ ሕዝብ ደጅ የንፋስ ያክል እንኳን ውል እንዳይል የትግራይን ሕዝብ በአፈና ውስጥ እንዲኖር ፈርዶበታል ከርሟል ይላሉ።

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ባሉ ጁንች ላይ በወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይ ክልል ሕዝብ ነጻ እንደወጣ የሚናገሩት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ፣ የትግራይ ሕዝብ የአፈናና የመከራ ጊዜውን እንደጨረሰ ያምናሉ። የትግራይ ሕዝብ ነጻ መውጣትን ሲገልጹትም “ኢትዮጵያ ዜጎች በሙሉ የአንድነት በሮች ተከፍተዋል” ሲሉ ይገልጹታል።

“የአንድነት በሮች ተከፍተዋል” የሚሉት አረጋዊ የትግራይ ሕዝብ ከአምባገነን አገዛዝ ነጻ በመውጣቱ የተሰማቸው ደስታ ወደር እንደሌለው ይናገራሉ። ታዲያ በዚህ የአንድነት በሮች ተከፍተዋል በተባለለት ጊዜ በትግራይ ክልል በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅ እና እንደሚገባም ብዙዎች ያምናሉ።

ለኹለት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት አመራሮች መካከል የተፈጠረ ልዩነት ቀን በቀን በቃላት ምልልስና መጠላለፍ ቢዘልቅም መጨረሻው የቃላት ልውውጥ አልሆነም። ይልቁንም በፌደራሉ መንግስትና በክልሉ መንግሥት መካከል የተፈጠረው ልዩነት እርስ በእርስ “ሕገ ወጥ ቡድን” በሚል ጥግ የደረሰው የቃላት ጦርነት ወደ ግጭት ወይም ጦርነት በአንድ ሌሊት ተቀየረ። እለቱ ጥቅምት 24/2013 ነበር፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የትግራይ ክልል መንግስት(ሕወሓት) መቀመጫውን መቀሌ ባደረገው የሰሜን እዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ለመላው ዓለም አበሰሩ።

ክስተቱ ለመላው ኢትዮጵያዊያም በእጅጉ አስደንጋጭ ነበር። ክስተቱን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንኳን ያልጠበቅነው እና ይደርጋል ብለን ያላሰብነው የጦርነት ትንኮሳ ጥቃት ተከስቶብናል ነበር ያሉት። በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት ለኢትዮጵያውያን ጥቁር ታሪክ ጥሎ ያለፈ ድርጊት እንደሆነ እስካሁንም እየተነገረለት ነው።
ጥቅምት 24/2013 የተከሰተውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ መጀመሪያ ላይ “ተገደን የገባንበት ጦርነት” ከቀናቶች በኋላ ድግሞ “ሕግ የማስከበርና የሕልውና ዘመቻ” በሚል ስያሜ ከሦስት ሳምንት በላይ የፈጀ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተካሂዷል። ከሦስት ሳምንት በላይ በዘለቀው ሕግ ወጥ የተባለውን እና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈጽሟል የተባለውን የሕወሓት ጁንታ መሪዎች ማስወገድ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በድል መጠናቀቁን የፌደራል መንግሥት ባለፈው ስምንት መጨረሻ ላይ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው በሂደት ላይ እንዳለ ነበር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የትግራይ ክልልን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲስተዳድሩ ሙሉ ነጋን (ዶ/ር) የመረጡት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደርን በተመለከተ በወጣው ደንብ መሰረት ነበር ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) እንደተሾሙ ያስታወቁት።

በዚህም መሠረት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በክልሉ በሕጋዊነት ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የክልሉን መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ መዋቅሮች የሚመሩ ኃላፊዎችን መልምለው እንደሚሾሙ አመላክተው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ሐሳብ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አረጋዊ በርሔ(ዶ/ር) የሚመራው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አንዱ ነው። ፓርቲው መንግሥት ያቀረበለትን ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ተባብሮ የማሥተዳደር ሥራ ሙሉ በሙሉ እንደተቀበለው የፓርቲው ሊቀመንበር አረጋዊ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

አረጋዊ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ መቀበላቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተጀመረውን ጊዜያዊ አስተዳደር ማዋቀር ሥራ በጋራ እየከወኑ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። የአወቃቀር ሥራውም ሕዝቡ የመረጠውን ምርጫ መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት የሕዝቡን ፍላጎት ያደረገ አደረጃጀት ሥራ በክልሉ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አረጋዊ በቅድሚያ የዲሞክራሲ ሥርዓት አሥተዳደሩን ሊጎለብቱ የሚችሉ ተቋማትን መኖራቸው ወሳኝ እንደሆነ ያምናሉ። ጊዜያው አስተዳደሩን ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ የተጠናከረ መሆን እንዲችል የፍትሕ ተቋማት፣ የሕግና የጸጥታ ተቋማት በተጠናከረ መንገድ መደራጀት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በአዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን ለማስተዳደር እየተሰራ ያለው ሥራ የጥገና ለውጥ የሚመስል ዝንባሌ እንዳለው የሚገልጹት ደግሞ የሰላምና ደህንነት ባለሙያው ኤልያብ ጥላሁን ናቸው። ኤልያብ እንደሚሉት ከሆነ በትግራይ ክልል አየተካሔደ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታ አካባቢውን ጠንቅቆ የሚውቅ አደራጅ ያስፈልጋል ይላሉ።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የተፈጠረውን የአወቃቀር ሥርዓት ለመጠገን እና ሰላም ለመፍጠር መሰረታዊ ተቋሞችን መፍጠር ቀዳሚ ሥራ መሆን እንደሚገባው ያምናሉ። ተቋሞችን ለማዋቀር በቅድሚያ የሕዝቡን ሰላምና ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ መሆናቸውን መታየት እንዳለበት አመላክተዋል።
የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ለሦስት ሳምንት በዘለቀው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ እያለ የክልሉን የወደፊት እጣ ፋንታ ወስኖ ነበር። በዚህም መሰረት ነበር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ ላይ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው። ይህንንም ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የሕግ ማስከበር ዘመቻው መጠናቀቁ ሳይገለጽ አስታውቆ ነበር። በወቅቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል በክልሉ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በመፈጸሙ ሕገ መንግሥቱን ማስከበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጾ ነበር።

በወቅቱ ሕወሓት በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ድርጊት አረጋዊ(ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነ ሕገ መንግስቱን በመናድ የፈለገውን አንባምገነናዊ አስተዳደር መመለስ ነበር ይላሉ። ታዲያ በዚህ አሰቃቂ ድርጊት በክልሉ በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ተከስተዋል። ሕወሓት በፌደራል መንግስቱ ጋር ግጭት ላይ በነበረበት ጊዜ በትግራይ ክልል የሚገኙ በርካታ መሰረተ ልማቶችን እንዳወደመ ተነግሯል።

በዚህም በትግራይ ክልል አፋጣኝ ሥራ የሚፈልጉ በርካታ የቤት ሥራዎች መኖራቸው ግለጽ ነው። በክልል በፍጥነት መሠራት አለባቸው ተብለው ከሚታሰቡ የቤት ሥራዎች ውስጥ በቅድሚያ የህዝቡን ሥነ ልቦና በመገንባትና የውስጥ ሰላሙን አስተማማኝ ማድረግ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አረጋዊና ኤሊያብ ጠቁመዋል።

የሕዝቡን ሰላም ከማረጋገጥ አንጻር በክልሉ አሁን ላይ በሥራ ላይ የሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደር በታችኛው የአወቃቀር ደረጃ ላይ ያሉ የሕወሓት ሥርዓት አራማጆችን በሕዝቡ እገዛና ፍላጎት መፈተሽ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ አረጋዊ ተናግረዋል። አረጋዊ አክለውም በኹሉም ቦታዎቹ ሕዝብ የመረጣቸው አዲስ አወቃቀር ማደራጀት ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ወሳኝ ሥራ መሆን አለበት ባይ ናቸው።

የሰላምና ደህንነት ባለሙያው ኤልያብ በበኩላቸው በክልሉ በሥራ ላይ ያለው ጊዜያዊ አሥተዳደር በቀዳሚነት የደህንነትና የተቋማት መሻሻያዎችን( sector and security reform) በሕዝቡ ድጋፍና ፍላጎት ማደራጀት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ሌላው በክልሉ ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ በሕዝቡ ትብብር የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ግጭቶች እነዲፈጠሩና መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ ያደረገውን የሕወሓት አመራሮችና ግብረ አባሮችን ለሕግ ማቅረብ መሆኑን አረጋዊ ይስማማሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኅዳር 10/2013 ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይ የሕወሓት ቡድን ከዚህ የባሰ ጥፋት ከማድረሱ በፊት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርብ፣ የከተማው ሕዝብ እንዳይጎዳ ሕግ ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ስምምነት መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በበኩሉ ሰሞኑን ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል። በውይይቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ(ዶ/ር) በሕወሓት የተዘረፈውን ንብረት መልሶ እነዲተካና ሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት እነዲያገኝ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ በሽሬ እንዳሥላሴ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር በተደረገ ውይይይ ሕዝቡ ያመነበት አስተዳደር መቋቋሙን ተናግረዋል።
በዚህም በከተማው ጊዜያዊ ከንቲባን ጨምሮ የምክር ቤት አባላት መመረጣቸውን አስታውቀዋል። እንዲሁም በከተማው አምስቱም ቀበሌዎች የሕዝብ መማክርት ጉባዔ አባላት መመረጣቸውን ገልጸዋል።

በሕዝብ የተመረጠው ጊዜያዊ አስተዳደርም የህወሃት ጁንታ አጥፍቷቸው የሄዱትን የመንግሥት መዋቅሮች ይዘረጋሉ ብለዋል። የወረዳውን በጀት በመጠቀምም የተዘረፈው የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት እንደሚሟላ ጊዚያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሌሎች አካባቢዎችም በሕዝብ የሚመረጥ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚያደራጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።
በሕዝብ የተመረጡ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎችን መርጦ ለማዋቀር በሚሠራው ሥራ ላይ የውስጥ እንቅፋቶች እንዳይገጥሙ በጥንቃቄ ከመሥራት ባለፈ ጊዜ የሚጠይቁ ሥራዎች መኖራቸውን ኤልያብ አመላክተዋል። በመሆኑም በመሀል ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ የማኅበረሰቡን የልብ ትርታ በሚገባ መዳመጥ እነደሚገባም ባለሙያው ጠቁመዋል።

በጊዜያዊ አሥተዳደር ማዋቀር ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳን ከሕዝቡ የሚመጡ ምክረ ሀሳቦችን መሰረት ያደረገ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅበት ባለሙያው አመላክተዋል።

የህግ የበላይነት የማስከበር ስራችን ከህግና ከህጋዊነት እንዲሁም ከአንድነታችንና ከቀጣይ ጤናማ የአገረ-መንግስት ግንባታችን አንፃር ሰፋ አድርገንና ሰከን ብለን ነው የምናየውእና የምንተገብረው። ምክንያቱም ነፃነት ሁሉም ሊቀዳጀው የሚገባ ትልቅ የሰው ልጅ ስጦታ ነውና።በየትኛው ሁኔታና የአገራችን ክፍል ያሉና ሊፈጠሩ የሚችሉ ትናንሽ ጁንታዎና ቅሪቶችም ከህግ በላይ መሆን እንደማይችሉ መገንዘብ ግድ ይላቸዋል።

ህግ የማስከበር ስራችን ፍፁም የማይሸራረፍና በምልአት የሚፈፀም ከመሆንም ሌላ አማራጭ የለዉም በማለት የትግራይ ብልጽግና ከፍተኛ አመራር የሆኑት ነብዩ ስሑል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com