የእለት ዜና

ሕይወት እና ጓደኝነት

‹ጓደኝነት
ሕሊና ቢወረስ በክፉ ትዝታ፤
ልቦና እየሻረው በጣፋጭ ትውስታ፤
በአብሮነት ጎዳና ገስግሶ ሚያነግሠው፤
መሆኑ ብቻ ነው ጓደኛ ጓደ’ኛ ሰው፤
ጊዜ እያፈለቀ የመቻቻል ወኔ፤
ለመልካም ተግባርህ ለደካማው ጎኔ፤
በጥሩ ቀን ሞገድ፤ አግባብቶን አላምዶ፤
ላያለያየን ነው፤ ያገናኘን ፈቅዶ።
አንዴ ጥፋተኝነት አንዴም ደግሞ ደግነት
ኩርፊያም ፍቅር ያለበት ደስ ይላል ጓደኝነት።
ይህ የስንኝ ቋጠሮ ‹ጓደኛነት› በሚል ርዕስ ድምጻውያን በጋራ ካቀነቀኑት ሙዚቃ ላይ በጥቂቱ የተወሰደ ነው።

እድሜያቸው በሀምሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ቢሆንም፤ በሩቁ ለሚያያቸውና ቀርቦ ለማያውቃቸው ሰው፤ ተክለ ሰውነታቸውና ለሁሉም የሚያሳዩት የተግባቢነት ባህሪያቸው ወጣት እንጂ ወደ ጎልማሳው እድሜ የገቡ አያስመስላቸውም። የሚያያቸው ኹሉ እድሜያቸውን ከሠላሳ አምስት እስከ አርባ፣ ግፋ ቢልም ከአርባ አምስት እንደማይዘል ይገምታል። እነርሱ ግን ከሠላሳ ሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀ የጓደኝነት ትውውቅ አላቸውና ስለእድሜያቸው አንዱ ለአንዱ ምስክር ናቸው።

ሰለሞን ዘውድነህ እና ሄኖክ ውብነህ ይባላሉ። ትውውቃቸው የጀመረው ገና በአፍላነት እድሜያቸው በ1979 አካባቢ ሲሆን ይህም በቦሌ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በነበሩበት ወቅት ነው። በአንድ የጋራ ጓደኛቸው አማካኝነት እንደተዋወቁና ቀስ በቀስ እየተላመዱና ልብ ለልብ እየተግባቡ ሲመጡ፤ አስደሳች የሆነ የጓደኝነት ሕይወትን በወጣትነታቸው እንዳሳለፉ የሚናገሩት እኚህ ጓደኛሞች፣ በጉልምስና እድሜያቸውም ምንም እንኳን የኑሮ ውጣ ውረድ ጥቂት ቢያራርቃቸውም የቀድሞውን የጓደኝነት ፍቅራቸውን በማስታወስ አሁንም እየተደዋወሉና እየተገናኙ የጋራ ጊዜን እንደሚያሳልፉም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አጫውተውናል።

ጓደኝነት ስሜት ነው፤ በሕይወት የተለያዩ አጋጣሚዎች ተዋውቀን በሂደት ስለተላመድነው ሰው የማሰብ፣ የመጨነቅና እንደራስ አድርጎ በማየት የመውደድ ስሜት። ብዙኀኑ የእምነት አስተምሮዎች ሆነ ማኅበራዊ ተቋማት ስለ ጓደኝነት አስፈላጊነትና የሕይወት በረከቶች አጥብቀው የሚያስተምሩ ሲሆን፤ ከስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ እውነተኛ ጓደኛን ማግኘት እንደሆነም ይስማማሉ።

‹‹ጓደኛ በኹለት አካላት የምትኖር አንዲት ነፍስ ናት።›› ይላል ግሪካዊው ባለቅኔና ፈላስፋ አርስቶትል የጓደኝነትን ጥልቀትና ምስጢርነት ሲገልፅ።
በአዲስ አባባ ዩንቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ (sociology) ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ክቡር እንግዳወርቅ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ጓደኝነት ሲያስረዱ፣ ‹‹ጓደኝነት ኹለት ወይንም ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ የሕይወት አጋጣሚዎች ተገናኝተው የሚፈጥሩት፤ ለረዥም ጊዜም የሚዘልቅ ግንኙነት ነው›› ሲሉ ይገልፃሉ። ያም ግንኙነት መዋደድ፣ መተሳሰብና እርስ በእርስ የሚደረግ እንክብካቤ ሲኖረው ጓደኝነት ተፈጠረ ማለት እንደሚቻልም ያስረዳሉ።

ሌላ ባለታሪኮችን እናንሳ፤ ነዋል አቡበከር እና ዓለምፀሐይ እንደሻው ጓደኛሞች ናቸው። ዓለም ባንክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ሜሪት አካዳሚ የስምተኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅት በ2004 ትውውቃቸው እንደጀመረ ይናገራሉ። በጊዜውም ኹለቱም ለትምህርት ቤቱ አዲስ ተማሪ ስለነበሩ፤ የአዲስ ተማሪ ወጉ ነውና የፍርሀት፣ የብቸኝነትና የድብርት ስሜት ተሰምቷቸው በነበረበት ወቅት እንደተዋወቁ ያስታውሳሉ።

ቀስ በቀስም ትውውቃቸው መላመድን ሲያመጣ፤ በጣም የሚዋደዱና ሁሉንም ምስጢራቸውን ሳይደባበቁ የሚካፈሉ የልብ ጓደኛሞች ለመሆን በቅተዋል። ይህም ጓደኝነታቸው እስከ ዩንቨርሲቲ ድረስ ዘለቀ። የአንድ ዓይነት ትምህርት ክፍል ተማሪ በመሆን በአንድ የማደሪያ ዶርም እያደሩ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። ጓደኝነታቸውም የቀድሞው መሰረቱ ሳይናድ እስከ አሁን ድረስ መዝለቁን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

ተማሪ ሳሉ የመኖሪያ አካባቢያቸው አንድ አካባቢ በመሆኑ ጠዋት ጠዋት እየተጠራሩና አንድ ላይ ወደ ትመህርት ቤት እየሄዱ፤ በኹለቱም ውስጥ የሚያግባባና የሚያቀራርብ ብዙ ነገር እንዳለ በመረዳታቸው እየተደጋገፉና እየተመካከሩም እስከ አሁን ድረስ መዝለቃቸውን ኹለቱም ይናገራሉ።
በተለይም ዓለምፀሐይ የትውውቃቸው ወቅት ከክፍለ አገር የመጣችበትና ከብዙ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ጋር ለመቀራረብ የምትቸገርበት ወቅት እንደነበር በማስታወስ፣ በጊዜው ብዙም ጓደኛ ካልነበራት ነዋል ጋር መተዋወቋ ከሰዎች ጋር በነበራት ግንኙነትና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ መልካም የሚባል ለውጥን እንዳመጣላት ትናገራለች።

እንዲህም ስትልም ስለ ጓደኛዋ ትገልፃለች። ‹‹ነዊን የመሰለ ሰው እንደ ጓደኛ እራሱ መውሰድ ይከብደኛል። ከእህቶቼ በላይ የምትረዳኝ የሕይወቴ አንድ አካል ናት። የጓደኝነት ጣዓሙን እራሱ በእርሷ ነው ያወቅኩት። ብዙ ነገሮቼን አካፍላታለሁ፤ እርሷም በተመሳሳይ የተለያዩ ጉዳዮቿን ታዋየኛለች። አብዛኛው ነገር ደግሞ ያግባባናል። ያም ሁኔታ ነው እስከዛሬ ድረስ በጓደኝነት እንድንቆይ ያደረገን ብዬ አስባለሁ።›› ስትል ትገልፃለች
አክላም ‹‹ጓዋደኛ ማለት በመጥፎውም ሆነ በጥሩ ጊዜ አብሮ የሚሆን ነው። እኔ አሁን ለምሳሌ ከእርሷ በኋላ ብዙ ጓደኞችን ተዋውቄያለሁ። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ አብረውኝ የቆዩ የሉም። ምክንያቱም ጊዜያዊ ጓደኝነት ነበር። የእርሷን አይነት ጓደኛ ደግሞ ስታገኝ እስከመጨረሻ ትሄዳለህ። ከእርሷ ብዙ ነገሮችን አትርፊያለሁ። ማወቅ ስላለብኝ ነገሮች ሁሉ ከሰዎች ሁሉ በልጣ አሳውቃኛለች። የመስጠትን ትርጉም እና ከራሳችን በላይ ለሰው መኖር እንዳለብኝ ጥሩውን ነገር አስተምራኛለች።›› ስትል ስለ ጓደኝነታቸው ታስረዳለች።

ነዋልም በበኩሏ ጓደኝነት የሰው ልጅ ከተሰጠው የእርስ በርስ ግንኙነቶች ውስጥ በጣም ውቡ ግንኙነት ነው ትላለች። ‹‹ሀዘን፣ ደስታ፣ ሕልም፣ ሐሳብ፣ ተስፋን ሁሉ የምናጋራው፤ የዓለምን ሸክም በግማሽ የሚያቀል አጋር ነው ጓደኛ ማለት።›› ስትል ትገልጸዋለች።

ጓደኝነት ጥቅሙ የማይለካ ነው የምትለው ነዋል፣ አንድ ሰው ጓደኛ ሲኖረው የሚመካበት እና የሚወደው ሰው እንዳለው ማሰቡ በራሱ ትልቅ የራስ መተማመንን ይሰጠዋል ባይ ናት። ብዙ ማንነትና ብዙ መዋደድ ትልቅ የሕይወት ጣዕም እንዳለውና አመለካከትን እንደሚያዳብርም በመግለፅ፣ ድካምና ጥንካሬን ሁሉ በትክክል ማወቅ የሚቻለው ከጓደኛ ነው ስትልም ታስረዳለች።

‹‹ይህን ሁሉ ደግሞ ከዓለምፂ ጋር ባለን የጓደኝነት ቅርርብ ውስጥ አግኝቼዋለሁ። ጉድለቴን በመሙላት ያላየኹትን እንዳይ በእጅጉን ረድታኛለች። ስለዚህ በእጅጉን ከእርሷ ጋር ባለኝ ግንኙነት ተጠቅሜያለሁ፤ በጣምም ደስተኛ ነኝ።›› ነዋል ያለችው ነው።

አንድ ሰው አንድም ሆነ ከዛ በላይ የሆኑ ጓደኞችን በመያዙ የሚያገኛቸው ብዙ ጥቅሞች እንዳሉ የሚያስረዱት ረዳት ፕሮፌሰር ክቡር፣ ከእነርሱም ውስጥ አንዱ የስሜት ድጋፍ (Emotional support) እንደሆነ ይገልፃሉ። የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ እንደመሆኑ አንድ ጓደኝነትን ሲመሠርት፣ በሐዘኑም ሆነ ደስታው ወቅት ያንን ስሜቱን የሚያጋራውና ሐሳቡን የሚያካፍለው ሰው እንደሚፈልግም ይጠቅሳሉ።

ሌላው በጓደኝነት ሊገኝ የሚችለው ነገር የገንዘብ ድጋፍ (Financial support) ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል። ነገር ግን ይህ የገንዘብ ድጋፍ የጓደኝነት ግብ አለመሆኑንና እንደማንኛውም ድጋፍ እንደሚያደርግ የቤተሰብ አባል ሁሉ፤ ጓደኛም ችግር በገጠመን ሰዓት የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል ያስረዳሉ። ‹‹ይሄ በራሱ ነውር አይደለም›› የሚሉት ክቡር፣ የዚህም ምክንያት በጓደኝነት መሀል በሌላ ጊዜ ይሄ ድጋፍ ከእኛም ስለሚጠበቅ ነው ይላሉ።

በተያያዘ ጓደኝነት የእኛነት ስሜትን (Solidarity) እንደሚፈጥር የሚያነሱት ክቡር፣ እንዲህ አሉ፤ ‹‹አንድ ሰው ራሱን ሲገልፅ እንዲህ ነኝ እንደሚለው ሁሉ እንደ ቡድንም እኛ እንደዚህ ነን እንዲል ያስችለዋል። እኛ ጓደኛሞች ነን የሚል የአንድነት ስሜት ይፈጥራል። ያ የአንድነት ስሜት በተለያዩ ጊዜያት በችግር ውስጥ በምንወድቅበት ወቅት ወገን አለኝ፤ አለኝታ አለኝ በማለት ወደመመካትና መፅናናት ይወስደናል።›› ብለዋል።
እንደ ምሳሌም በአደጉ አገራት በጣም የሚያስቸግራቸው ነገር እራስን ማጥፋት (Suiside) እንደሆነ የሚገልፁት ክቡር፣ እነዛ ሰዎች ያንን ውሳኔ የሚወስኑት ጭንቀትን መቋቋም ባለመቻላቸው እንደሆነም ያስረዳሉ።

‹‹ጭንቀት ማናችንም ይገጥመናል። ነገር ግን ለምንድን ነው እራሳችንን ያላጠፋነው ሲባል፣ ጭንቀቱን ለመቋቋም በመቻላችን ነው። ያንን የተቋቋምነውም የምንወደውን ሙዚቃ በማዳመጥ፣ መጽሐፍ በማንበብ እንዲሁም ጓደኞችን አግኝተን በመነጋገርና ችግሮቻችንን በማካፈል ሊሆን ይችላል።›› በማለት የብቸኝነት አስተሳሰብ እንዳይኖር እንደ መዝናኛ ሁሉ ጓደኞችም መኖራቸው ከገባንበት ጭንቀት በማውጣት ሊገጥሙን ከሚችሉ መጥፎ ነገሮች ሊጠብቀን እንደሚችል ይገልፀሉ።
ከዚህ ባሻገር እራስን ይፋ ማድረግ (Self disclosure) ወይንም እኛ ለብቻችን መያዝ የማንችለውን፤ ነገር ግን ለብዙ ሰዎች ቢነገር እኛ ላይ ጉዳት ሊያመጣ፤ ወይንም ሥማችንን ሊያጠለሽ የሚችል ምስጢር ሊኖረን ይችላል። ያንን ምስጢር እንዳንደብቀው ለሰው በመናገራችን የምናገኘው ጥቅም ይኖራል። ስለዚህ መፍትሄ የሚነግረን ወይም የሚያፅናና ሲያስፈልግ፣ ያንን ከጓደኛ ማግኘት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።

‹‹ጓደኝነት ስንመሰርት ጥቅምን እናገኝበታን ብለን ከግምት ውስጥ በማስገባት የምንመሰርተው ሳይሆን፣ በሂደት በሚኖሩ ግንኙነትና ትስስሮች እነዚህን ጥቅሞች ሊገኙ ይችላሉ።›› የሚሉት ክቡር፣ ነገር ግን በእውነተኛ ጓደኝነት ውስጥ ሰዎች ይሄን እንኳን እንደማያስተውሉት ይገልፃሉ። ምክንያቱን ሲያስረዱም ‹‹የግንኙነታቸው ግብ ጓደኝነት ስለሆነና በየትኛውም ጊዜ ከጎናቸው እንደሚሆኑ ስለሚያስቡ ነው።›› ይላሉ። ይህም ከኹለቱም ወገን የሚፈጠር መሆኑን አክለው ይገልፃሉ።
በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ትውውቃቸው በደንብ ተጠናክሮ የጀመረው የሄኖክንና የሰለሞን ጓደኝነት እስከ 1983 ዓመተ ምህረት ድረስ በደንብ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከ1983 በኋላ ግን ኹለቱም በግል ሥራቸው ምክንያት ለጥቂት ዓመታት ተለያይተው እንደነበር ያሳታውሳሉ።

‹‹ነገር ግን ስንለያይም በጥሩ ወንድማማችነትና በፍቅር ስሜት ስለነበር፤ ስንገናኝ በጥሩ ፍቅር ሆኗል ጊዜያችንን የምናሳልፈው።›› የሚለው ሰለሞን፣ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት አንድ አካባቢ መኖር እንደጀመሩና ዳግመኛም የቀድሞውን ጓደኝነታቸውን በማደስ እንደቀጠሉ ይናገራል።
‹‹ያን ጊዜ በጣም መተሳሰብ አለ፤ እንደዛሬው መደባበቅ የለም። ያለንን ተካፍለን ነው የኖርነው። ሄኖክም በባህሪው በጣም መልካም ሰው ነው።›› የሚለው ሰለሞን፣ በጊዜ ሂደት በጸባይ ለውጥ የተነሳ የተለያቸው ሰዎች እንደነበሩ አስታውሶ፣ ‹‹ሄኖክ ግን ምንጊዜም የማይለዋወጥ አንድ አይነት ጸባይ ያለው ሰው ነው።›› በማለት ይመሰክራል።

ሄኖክም በበኩሉ ከቤተሰብ ሆነ ከመምህራን በላይ ብዙ ጊዜን ከጓደኛ ጋር የሚያልፍ እንደመሆኑ፣ ጓደኛ ‹እንደዚህ ብትሆን ወይንም እንደዚያ ብትሆን› ብሎ ለማማከርና በተቻለው አቅም እድሎችን ሊያመቻች እንደሚችልም ይናገራል።

አክሎም ‹‹የማይሆን መንገድ ውስጥ ስትገባ ደግሞ የሚመክርህና ወደ ቀናው መንገድ የሚመልስህ ጓደኛህ ነው። ምክንያቱም ረጅም ጊዜን አብረህ እንደማሳለፍህ አትደባበቅም። ለምሳሌ ሌላው ፈርቶ ወይንም አያገባኝም ብሎ የማይነግረንን ነገር፤ እኔና እሱ ግን ፊት ለፊት ነው የምንነጋገረው። በተጨማሪም ያሳለፍነውን ስናወራም የምንታደስበት ጊዜም ብዙ ነው። የሚያስቀን፣ የሚያሳዝነን የሚያስገርመን ብዙ ነገር አለ። የረሳነውን ነገር ሁሉ አስታውሶኝ ወይንም እኔ አስታውሼው የምንስቅበትና የምንዝናናበት ጊዜም ብዙ ነው።›› በማለት ያስታውሳል።

አያይዞም ‹‹ከምንም ነገር በላይ ብዙ ነገር አብረውን ያሳለፉ ጓደኞቻችን አሁን በሕይወት የሉም። እኛ ግን የሚጠበቅብንን ያህል ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ባናመጣም በተሰጠን እድሜና ጤና ደስተኛ ሆነን ስናወራው እራሱ ደስ የሚል ስሜትን ይሰጠናል።›› ሲል ከጓደኛው ጋር በሚያሳልፈው ጊዜ ምን ያህል እንደተጠቀመና ደስተኛ እንደሆነ ያስረዳል።

ጓደኝነት በዘመን መካከል
እውነተኛ ጓደኞች የደስታችን የቅርብ ተካፋዮች፣ የችግራችን ተጋሪ፣ በሐዘናችን አፅናኝ፣ ተስፋ ስንቆርጥ የሚያበረቱ፣ ስንወድቅ የሚያነሱ፣ የሳቃችን ምንጮች በአጠቃላይ ከጎናችን ሆነው የሕይወት ውጣ ውረዶቻችንን የሚጋሩን እንዲህ ብለን ዋጋ ልናወጣላቸው የማንችላቸው ውድ ስጦታዎቻችን ናቸው። ‹‹አንድ ወንድም ጓደኛ ላይሆን ይችላል፣ ግን ጓደኛ ሁልጊዜ ወንድም ነው።›› ይላል ቤንጃሚን ፍራንክሊን የጓደኝነትን ጥልቅነት ሲያስረዳ።

ታዲያ የጓደኝነት መገለጫዎቹ እነዚህ ከሆኑ በድሮ ጊዜ በነበረ ጓደኝነትና በአሁን ዘመን ባለ ጓደኝነት ውስጥ ልዩነት ይኖር ይሆን? ካለስ የልዩነቱ ምክንያት ምንድን ነው? ስንል ጠየቅን።

‹‹እንደኔ ድሮ የነበረውና አሁን ያለው ጓደኝነት ላይ በጣም ልዩነት አለው ብዬ አስባለሁ።›› የምትለው ዓለምፀሐይ ናት። ምክንያቷንም ስታስረዳ፤ ‹‹በፊት የነበረው ጓደኝነት በጣም ዘላቂነት አለው። አሁን ላይ ግን የሚፈጠር ጓደኝነት በኹለት ቀን በሦስት ቀን ተዋውቀህ ልትራራቅ ትችላለህ። ለምሳሌ ሰዎች ጓደኝነቱን ፈልገው ሳይሆን ለጥቅም ሊሆን ይችላል የሚቀርቡክ፤ አንተ እንድትገኝላቸው የሚፈልጉህ ቦታ ላይ ብቻ ይሆናል የሚገኙልህ። ነገር ግን የእውነት እና ውስጣዊ የሆነ ጓደኝነት ምንም አይነት ሁኔታ በመኻከል ቢፈጠርም ጉዳዩ ጓደኝነቱን ሳያሳሳው በመነጋገር አሳልፈኸው እስከ መጨረሻው ድረስ መሄድ ነው።›› ስትል ትገልፃለች።

ነዋልም በበኩሏ በእርሷ አመለካከት በድሮ እና በአሁን ጓደኝነት መካከል ብዙ ልዩነት አለ ብላ እንደማታስብ ትናገራለች። ‹‹አሁን አሁን ጓደኛማቾች እርስ በእርስ አብረው የሚያሳልፉበት ብዙ ጊዜ አያገኙም። በድሮ ጊዜ ጓደኞች ብዙ ግዜያቸውን አብረው ከማሳለፋቸውም በላይ አንዱ በአንዱ ሕይወት ላይ የጠለቀ ተፅዕኖ ነበረው። አሁን የማኅበራዊ ሚዲያውና የአኗኗራችን መለወጥ እነዚህን ነገሮች ሳያሳሳቸው አይቀርም።›› በማለት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰዎችን ግንኙነት እያቀዘቀዘው እንደሚገኝ ታስረዳለች።

የድሮውን ከአሁኑ ለማነፃፀር ይከብዳል የሚሉት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ክቡር ናቸው። በአደጉ አገራት በየዐስር እና ኻያ ዓመት የሚደረግ ጥናት እንዳለ አንስተው፤ ‹‹ከሆነ ጊዜ በፊት የሆነ ጥናት ይጀመርና በትውልድ ቅብብል እስከ መቶ ዓመትና ከዛ በላይ ይሄዳል። ይህም ጥናት የነበረውን ሁኔታ ለማሳየት የሚያደርጉት ጥናት ነው። አለመታደል ሆኖ እኛ አገር እንደዚህ አይነት ጥናት አናካሂድም። ለምሳሌ ከዛሬ ሥልሳና ሰባ ዓመት በፊት የተከናወኑ ጥናቶችን ብናያቸው ኖሮ አሁን ላይ የደረሰበትን ሁኔታ እያነፃፀሩ መናገር ይቻል ይሆናል።›› ይላሉ።

ዕይታቸውን ሲያጋሩ ታድያ፤ በጊዜ ሂደት በማኅበረሰቡ አንዳንድ መገለጫዎች ይለወጣሉ እንጂ ጓደኝነት ላይ ይሄን ያህል የሚጨበጥ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም አሉ። ‹‹የልብ ጓደኛ ድሮም ነበረ አሁንም አለ። መልካም ያልሆኑ ጓደኞች ድሮም ነበሩ አሁንም አሉ። መገለጫው ምንድን ነው? ያንን መልካም ያልሆነውን ነገር የሚያደርጉበት መንገድ ተለያይቶ ሊሆን ይችላል።›› ብለዋል።

የጓደኛ ምርጫ
አንዳንዴ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ባለን አመለካከትም ይሁን ስለ ሕይወት ባለን ግብ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ባህሪ ያላቸውን ጓደኞችን ልንይዝ እንችላለን። በአንጻሩም በጸባይ የማይመስሉን ነገር ግን በተለያዩ የሕይወት አጋጣሚዎች የፈጠርናቸው ግንኙነቶች ወደ ጓደኝነት ሊያድጉ ይችላሉ። ይህን ለይቶ ታድያ ጓደኛን እንዴት መምረጥ ይቻላል፤ ሌላው የአዲስ ማለዳ ጥያቄ ነበር።

‹‹እንደ እኔ ጓደኝነት ይመረጣል ብዬ አስባለሁ።›› የምትለው ዓለምፀሐይ ምክንያቷንም ስታስረዳ ‹‹ከኻያ ሠላሳ በላይ ጓደኛ ሊኖረን ያችላል፤ ነገር ግን ምስጢር የምናካፍለውና ብዙ ነገሮችን የምናጋራው አንድ ወይንም ኹለት የልብ ጓደኛ የምንለው ይኖረናል። ከዛ ከበዛ ከባድ ነው፤ ምስጢር ራሱ የሚባለው ነገር አይኖረንም ማለት ነው። ዛሬ ያወቀህ ራሱ ጓደኛዬ ሊልህ ይችላል ማለት ነው። ግን ያ አይደለም ጓደኝነት።›› ስትል ትናገራለች።

‹‹ጓደኛን ሙሉ ለሙሉ መምረጥ የለብንም ብዬ ባላምንም ጓደኞቻችን አንድም ከኛ በአመለካከት የላቁ፣ ሊያዳብሩንና ሊያሻሽሉን የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል።›› የምትለው ደግሞ ነዋል ነች። ‹‹በተለይም አብረናቸው ስንሆን ደስታና ምቾት የሚሰማን ቢሆኑ፤ አልያም እኛ ልንደግፋቸውና ልንቀይራቸው የምንችላቸውን ጓደኞችን ብንመርጥ መልካም ነው። ከምንም በላይ ግን ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ጠንካራና መልካም ጎን አለው።›› በማለት ጓደኛ ለመምረጥ መስፈርት ቢሆን ያለችውን እንዲህ አጋራች፤ ‹‹ጓደኛ ስመርጥ የመጀምሪያው መስፈርቴ ለኔ አክብሮትና ጥሩ አመለካከት ሊኖረው ይገባል የሚል ነው። ከዛ ባለፈ ሁሉም ሰው ውስጥ በግንኙነት የሚማረው ብዙ ነገር እንዳለ አምናለሁ።››

‹‹ከእኔ በተቃራኒ ያሉ ነገሮችን የሚወድና የሚያይ፣ የእኔን ጉድለት የሚሞላልኝ ወይንም እኔ የማልወዳቸውንና የማልችላቸውን ነገሮች የሚችልና የሚወድ ሰው ሲሆን ላይሰለቸኝና ሊስበኝ ይችላል።›› ሲሉ የሚናገሩት የማኅበራዊ ሳይንስ መምህሩ ክቡር ናቸው።

‹‹ተመሳሳይ ነገር ውስጥ ስላለን ብቻ ሳይሆን በተቃራኒውም ደግሞ ተሳሳቢ ሊኖር ይችላል። ያም መሳሳብ አንዱ የአንዱን ጉድለት እየሞላ በሌላ አተያይና በሌላ አቅጣጫ ነገሮችን የሚያይለት ሰው አግኝቶ ነገሮችን እየተወያየ ሐሳቡንም እየተካፈለ የሚኖር ሰው ብዙ አለ። ይሄ በራሱ መጥፎ አይደለም።›› በማለት ያስረዳሉ።
በአንጻሩ የአቻ ግፊት የሚባለውና ብዙ ጊዜ ለአፈንጋጭ ጸባዮች ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን እንድናደርግ ጓደኞች ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚሉት ክቡር፣ ለምሳሌ በወንጀል የተዘፈቁ፣ የተለያየ ሱስ ያለባቸው ወይንም መልካም ስዕብና የሌላቸው ጓዋደኞች ይኖሩናል። እነርሱም ያላቸውን ባህሪ ወደ እኛ ሊያጋቡብን ይችላሉ በማለትም ያስረዳሉ።

‹‹ችግሩ ግን….›› ይላሉ ክቡር ‹‹ችግሩ ግን የሰው ልጅ መገለጫዎቹ ብዙ ናቸው። አንድ ልጅ በቤተሰቦቹ ዘንድ የተወገዘ ጸባይ ያለው ወይንም ሱስ ያለበት ጓደኛ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ያ ሱስ ያለበት ልጅ ሌሎች መገለጫዎች አሉት። ለምሳሌ አንባቢ፣ ጥሩ ተናጋሪ፣ በትምህርቱ ጎበዝ ወይም ሰው በመርዳት የሚታወቅ ሊሆን ይችላል አልያም በማኅበረሰብ ውስጥ መልካም ፍቃደኛ በመሆን ብዙ ግልጋሎቶችን የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ያ ሰውም በእነዚህ መልካም ነገሮች ይሳብና ሌሎቹን መጥፎ ነገሮችን ከዛ ጓደኛው ላያይ ይችላል።

መጠንቀቅ የሚያስፈልገው አንድ ሰው ምን ያህል ተፅዕኖ ሊያሳድርብኝ ይችላል? ወይንስ መልካም ጎኖቹን በመፈለግ ነው አብሬው እየዋልኩ ያለሁት? አብሬውስ በምውልበት ወቅት ያንን መጥፎ የሚባለውን ባህሪውን እንዳያጋባብኝ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለውን ማሰቡ ላይ ነው።›› ብለዋል።
አክለውም፤ ‹‹አብሬው የማሳልፈውን ጊዜ በመቀነስ አልፎ አልፎ ማግኘት ነው? ወይንስ ከእኔ ጋር እያለ ያንን መጥፎ ነገር እናዳያደርግ በተቻለኝ አቅም መሞከር ነው? ወይንስ ደግሞ እርሱን ከዛ ነገር ውስጥ ፈፅሞ ማውጣት ይጠበቅብኛል? በውስጡ ያለውን መልካምነቱን ለምን ይሄ ትንሽ ነገር ታጠለሸዋለች? ስለዚህ በምን ልርዳው ብለን ማሰብ እንደሚጠበቅብን በመግለፅ ጓደኛ መምረጥ ሳይሆን በጓደኞች አፈንጋጭ ምግባር ላለመሳብ የራስን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com