‹የተነጠቁ ርስቶች› ቀጣዩ የጠቅላይ ሚንስትሩ ራስ ምታት

Views: 324

የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ተጠናቅቆ የጁንታውን አባላት ለፍት ለማቅረብ እየተደረገ ካለው ሂደት ጎን ለጎን የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፤ አንዲሁም የፈረሱ የአስተዳደር መዋቅሮችን የማቋቋም ሥራ እተከወነ ነው፡፡ከእነዚህ ተግባራት ባለፈ በራያ፣ በሁመራና ወልቃይት ጠገዴ ቦታዎች ላይ ‹በጉልበት የተነጠቀ ርስት› በጉልበት አስመልሰናል በሚል ጥያቄ፤ ዘለል ሲልም በእጃችን የገባን ርስት ሰጥተን አንጠይቅም የሚሉ አደገኛ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ መሆኑ ከማንነት እና ወሰን ጋር በተገናኘ የሚነሱትን ጥያቄዎች ቀጣዩ የጠቅላይ ሚንስትር ዐይ አሕመድ ቀጣይ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ዳዊት አስታጥቄ በሐተታ ዘ ማለዳ ባለሙያዎችን አናግሮ እንዲህ አዘጋጅቶታል፡፡

የድህረ-ሕወሃት ኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ እንደ ጉም በነው፣ ተስፋ እንደ ንጋት ኮከብ አብርቶ የኢትዮጵያ መጻኢ እድል እድገት እና ብልጽግና ብቻ ይሆናል ብሎ የሚያምን ሞኝ ዜጋ ባይጠፋም፣ሕውሃት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጫንቃ ላይ ተወገደ ማለት የኢትዮጵያ ችግሮች ግብአተ መሬት ገቡ ማለት እንዳልሆን ብዙዎች ይረዳሉ።ሕውሃት ላለፉት 27 ዓመታት ሲያራምዳቸው የነበሩ የአስተሳሰብ አጋሞችን ነቅሎ መጣል ከባዱ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ ቢሆን ሌሎች ከፊት የተደቀኑ እና ብልሃት የሚጠይቁ፣ከአስተሳሰብ እስከ መዋቅራዊ ማተካከያ የሚሹ በርካታ ጉዳዮች አሉ።

መዋቅራዊ ማስተካከያ ቢደረግ እንኳን በመለስ አስተምህሮ የተጠናገረን ከታች እስከ ላይ ያለን ማሊያ ብቻ ቀይሮ ከህውሃቱ-ኢህአዴግ ወደ ብልጽግና የገባን ካድሬ ይዞ የመፍትሄ አካል አድርጎ ማሰለፍ በራሱ የአስተሳሰብ ተራማጅነቱን ዘገምተኛ ያደርገዋል። የመለስ ሌጋሲን ሲምል እና ሲገዘት ከነበረ ካድሬን አስተሳሰብ መቀየር ኢህአዴግን በብልጽግና እንደመቀየር ቀላል አይደለም።የሰሞኑ የታዬ ደንደኣ እሰጥ አገባ ልብ አስረጅ ማድረግ ያቻላል።

በድህረ ሕውሃት የኢትዮጵያን ክፉ ውርሶች ማራገፍ ወይም/እና/ ማስተካከል የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ።ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣የብሄር ፌደራሊዝምን ማራገፍ ወይም ማስተካከል፣የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን መመለስ ወዘተ ቁልፍ ጉዳዮች ይሆናሉ። እነኚህ ጉዳዮች በቀጥታም ሆን በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም የልማት እና ዲሞክራሲን መረጋጋጥ የሚወስኑ ነጥቦች በመሆናቸው ናቸው።

ብዙዎቹ ጊዜ የሚሰጡ ቢሆኑም የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎቹ ግን ለፊት ያሉ የጠቅላይ ሚንስተር ዐብይ መንግስት ቀጣይ ተግዳሮቶች እንደሚሆኑ ያታመናልና።በተለይ የአማራ ክልሎቹ የራያ፣የጠገዴ እና ሁመራ መሬቶች እና የማንነት ጥያቄዎችን በብልሃት መፍታት ነጥብ ከመጣል እና ከማቆጠርም በላይ ‹የፓንዶራ ቦክሱን› ጨዋታ ስለሚያመጣ ትኩረት የሚሻ ትልቅ ነጥብ ነው።

የራያ፣ወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ጉዳይ
ጁንታ የተባለውን የህውሃት ቡድንን አድኖ ለፍትህ ማቅረብ እየተሰራ ያለ ሥራ ቢሆንም ካለ ፍርድ ‹የተነጠቀ ርስት› ጉዳይ ሌላ ደጅ ላይ ያለ ቀጣይ የቅርብ ጊዜ ፈተና እንደሆነ ይታመናል።

“በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ ያለ ፍርድ የሄደች…….እያለ ለሚያንጎራጉር ሕዝብ ፣ያለ ፍርድ ወልቃይትጠገዴ እና ሌሎች ቦታዎች ‹በጉልበት› ተወስደው ቆይቷል፣ እኛ በጉልበት የተወሰደብንን በጉልበት አስመልሰናል። ስለሆነም ከዚህ በኃላ ወልቃይት ጠገዴን ሰጥተን እንደገና አንጠይቅም! በማለት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በዳንሻ ከተማ በተደረገው ሰልፍ ላይ መናገሩ ልብ ይሏል።

እዚህ ጋር የአማራ ክልል ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል በህግ ማሥከበሩ ሂደት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በአንድነት በመቆም የተዋደቀበትን ጉዳይ ይዘን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል(ዶ/ር) ርስት አስመላሽ ምናምን የሚሉዋቸው አብረው እየወጉን ነው በማለት የተናገሩትን ስንይዝ፣እነኚህ ኃይሎች የተዋጉበት ገፊ ምክንያት ቁልጭ ብሎ ይታያል።

ጠቅላይ ሚንስትሩም በሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊቱ ላይ አሰቃቂ እርምጃ በህውሃት ጁንታ ቡድን መፈጸሙን በተናገሩ ማግስት የቡድኑን የተስፋፊነት እቅድ የመከተው እና በከበባ ውስጥ የነበሩትን የሰሜን እዝ ሠራዊት አባላትን ከከበባ ያወጣው የአማራ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል ነው ብለው በአድናቆት ማመስገናቸው ይዘን፤ የህግ ማስከበሩ ዘመቻ መጠናቀቁን ተከትሎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ግን ማመስገናቸውን ትተው ‹ሃምብል ሁኑ› ማለታቸው ውለታቸውን ከመርሳት ሳይሆን ሌላ ጣጣ ይዞ እንዳይመጣ በማሰብ ነው። ማዶ ያሉት ሰዎች ርስት የማስመለስ ጉዳይ ሳይሆን ሕግ የማስከበር እርምጃ እንደሆነ ለማስገንዘብ ነው።
በጉልበት ስለተወሰዱ መሬቶች በጨረፍታ

ገና ከጥንስሱ ሕውሃት ቁፍ የሚባሉ መሬቶችን አንድም ለሰፊፉ እርሻዎች ለማዋል ፤አንድም ወደ ሱዳን መውጫ በር ለማግኘት ሲል የቋመጠባቸው አካባቢዎች ነበሩ።ምኞቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሕገ መንግሥት እንኳን ማጽደቅ ሳይጠበቅበት በጉልበት ጠቅልሎ ያዘ።
“ሕውሃት መሬቶቹን በጉልበት ይዞ በኃላም ሕገ መንግሥታዊ ሽፋን ሰጥቶ ወሰወዷል”ሲሉ መርሃጽድቅ መኮንን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አማካሪ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሕገ መንግስቱ የፀደቀው በ1987 ነው፤ ወልቃይትና ራያ ወደ ትግራይ በኃይል ከዚያም በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ትግራይ የተካለሉት ግን በ1982-83 ዓ ም ነው፤ ታድያ ዛሬ ወልቃይትንና ራያን ወደ እናት ምድራቸው ወደ አማራ ለመመለስ “በህገ መንግስቱን አሰራር ተከትሎ” ይታያል የሚል ማደናገሪያ አይሰራም !ሲጀምር መች በህግ ሄደና ነው በህገ መንግስቱ አሰራር የሚመለሰው ሲሉ የህግ ባለሙያው ሙሉጌታ ወርቁ አበክረው ይናገራሉ።
የባለሙያው ምላሽ በጉልበት የተወሰዱ መሬቶች ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ እና እሱን ተከትሎ በተቋቋመው የወሰን እና ማንነት ኮሚሽን በኩል ይፈታል ለሚሉ ሰዎች የመልስ ምት መሆኑ ነው።

አንደ ራይ ወለወቃይት እና ጠገዴ ያሉት ሕገ መንግስት ሳይፀድቅ፣አንደ ግጨው ያሉት ደግሞ በፖለቲካዊ ውሳኔ መካለላቸውን ሙሉጌታ ያነሳሉ።
መሬቶቹ በሀይል የተወሰዱት ዋናው ምክንያት ደግሞ ወደ ሱዳን መውጫ ‹ኮሪዶር› ፍለጋ እነደነበር ከህውሃት መስራቾቹ አንዱ የሆኑት አረጋዊ በርሄ አንስተው ያውቃሉ። ለዚህም ነው በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸሙ ማግሥት በሁመራ በኩል ያለውን መሬት ለመቆጣጠር እና ወደ ሱዳን መውጫና መግቢያ ለማድረግ አስበው ሲሰሩ የነበሩት።

ጥቅምት አጋማሽ ላይ ለንባብ የበቃው የ‹ፎሬን መጽሔት በዘገባው የጦርነቱ መርዘም ሆነ ማጠር የሱዳን መውጫን ከመቆጣጠር እና ከሱዳን ጋር ባለው ግንኙበት ይወሰናል በዘገባው ሲል ያሰፈረው።

ከሕግ ማስከበሩ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሳለን የርስት ይገባኛል ጥያቄዎች ቀጥለዋል።በጉልበት የተነጠቀው ‹ርስት›ነገር እንዴት ይፈታ? በሚለው ጉዳይ በፖለቲከኞች እና በመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ሳይቀር እሰጥ አገባ ውስጥ የከተተ ጉዳይ የሆነው።

የተነጠቀው ርስት ጉዳይ እንዴት እልባት ያግኝ?
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚነሱ የማናንነት እና የድንበር ውዝግቦችን በተቋቋመው የድንበር እና ወሰን ኮሚሽን በኩል መፍትሄ ይሰጣቸዋል ሲሉ የተናገሩት የአካባቢውን ሰዎች እንደማያስደስት ይታመናል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚም ሙሉ ካህሳይም በትግራይ ክልል የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮች ለማቋቋም የሚያደርጉትን ሂደት አስቸጋሪ ያደርገባቸው ያመስላል።ቅድሚያ ከጁንታው የተላቀቁትን አካባቢዎች ትተው እንደዚህ ዓይነት ውዝግብ የማይነሳባቸውን እንደ እነ ሽሬ ያሉ ቦታዎች ላይ መዋቅር እየዘረጉ ያሉት ጉዳዩ ሌላ ውዝግብ አንደሚያስነሳ በመገንዘብ ይመስለል።በእርግጥ ጉዳዩንም ውስብስብ የሚያደርገው ይህ ነው።

የአካባቢው ተወላጆች ሃሳብ
የሕግ ማስከበሩ በተጠናቀቀ ማግስት የራያ ተወላጆች በተፈጠሩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይና የሕዝቡ ጥያቄዎች ላይ የመፍትሄ መንገዶች የሚያመላክት የምክክር ባደረጉበት ወቅትም በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ የራያ ህዝብ ላለፉት ዓመታት ባልተገባ መንገድ ከወገኖቹ ተነጥሎ ቆይቷል ይህም በሰሞኑ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት አንድ መሆን በጉልህ አሳይቷል ብለዋል።
‹ራያ የወሎ ባህላዊ ትውፊቶች ትልቁ ነፀብራቅ ነው። ያለፍላጎቱ ተካሎ በአፈና ውስጥ የኖረ ነው። በመሆኑም ህዝቡን ከቆየበት አፈና የሚያወጡ ውይይቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል› በማለት የማንነት ጥያቄ መልስ ለማግኘት እየተንደረደረ ስለመሆኑ አመላክተዋል።

ዣንጥራር አክለውም፣ ለነፃነት የተዋደቁትን የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ በማሰብ ተነጥሎ ከነበረበት ህዝቡ ጋር የሚኖርበትን ምቹ መንገድ የሚፈጥሩ ስራዎችን መስራት እነደሚገባልም አንስተዋል።

ሌላው በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ ዛዲግ አብረሀ በበኩላቸው የራያ ጉዳይ የሚያገባቸው ሁሉ ለህዝቡ ምንም ከማይፈይድ የርስ በርስ መጠላለፍ ወጥተው ታፍኖና ከወገኖቹ ተነጥሎ ለኖረው ህዝብ በሚጠቅም መንገድ መነጋገር አለባቸው ብለዋል።

የራያ ህዝብ ያገኘውን ትልቅ ዕድል ማሳጣት የለብንም። ህዝቡ የደረሰበትን ግፍ አስቦ በአንድነት መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት።የራያ ህዝብ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ አልነበረም። የትህነግ ባለሀብቶች ህዝቡን ከለም መሬቱ አፈናቅለው የራሳቸው የኢኮኖሚ ማዕከል አድርገውት ቆይተዋል ብለዋል።

የራያ ህዝብ ከትህነግ አፈና ለመውጣት ለዓመታት ተጋድሎ ሲያደርግ ነበር። በዚህ ተጋድሎ ብዙ ወጣቶች ተሰውተዋል፣ ተፈናቅለዋል ብሎም ታስረዋል። በነበረው ትግል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለልተኛ ባለመሆንና ጥያቄዎችን በማድበስበስ፣ ያገባናል የሚሉ ፓርቲዎችና ኮሚቴዎች የሀሳብ ልዩነትን አለመቀበል፣ የምሁራን ዝምታ፣ ህዝብና ርስትን ነጣጥሎ መመልከት የነበሩ ችግሮች ናቸው ተብሏል።

ትህነግ ነጮች አፍሪካን በቅኝ ግዛት ከጨቆኑበት በላይ በራያ ህዝብ ላይ በደል አድርሷል። ቦታው የወሰንና የማንነት ጥያቄ ሲነሳበት የነበረ ነው። ትህነግ ይህንን ጥያቄ ባለመቀበል የህዝቡን ፍላጎት ረግጦ ሌላ ማንነት ጭኖት ቆይቷል። የራያ ህዝብ የወሎ አማራ ማንነት ያለው በመሆኑ አማራዊ ማንነቱ ተከብሮ ወደ አማራ ክልል መመለስ አለበት ሲሉ የአካባቢው ነዋሪ በነበረው ስብሰባ መግልጻቸው ይታወሳል።

ትግራይ በወረራ አብጣለች። ወሎንና ጎንደርን በመውረር አቅማቸውን አሳድገዋል። የወደፊቷን ሀገረ ትግራይ ለመመስረትም አቅደዋል ዳኛቸው አሰፋ(ዶ/ር) ተናገረው ነበር።

ህዝቡ የሚያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች እንዲከበሩ እና ለዚያም መስራት እንደሚገባም አንስተው፤ ምሁራን ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠርና በቦታው የሚንቀሳቀሱ

የፖለቲካ ፓርቲዎች
ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠበቅባቸው እና የፖለቲካ ድርጅቶቹም አካሄዳቸው እንዲያስተካክሉ ይጠበቃል።ፖለቲከኞቻችን የሚናገሩዋቸውንም ሆነ የሚያወጧቸውን መግለጫዎች ግን የሚያረጋጉ መሆንእንዳለባቸው የአማራ ክልል የርእሰ መስተዳደሩ አማካሪ መርሃጽድቅ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ስር ሊቀጥሉ አይገባም ምክንያቱም ወልቃይት እና ራያ በግፍ ከአማራ የተነጠቁ በመሆናቸው እና ከስፍራው ከ500ሺህ ያላነሱ አማራዎች በግፍ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉበት፤በሺዎች በግፍ የተጨፈጨፈበት ስለመሆኑ አንስተው የሚሟገቱ አሉ።

የደረሱ ጉዳቶች ምንም ያክል የከፉ ቢሆኑም የራያ፣የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይን መፍትሄ መስጠት ቀላል የሚባል ጉዳይ አይደለም ይላሉ የርእሰ መስተዳድር አማካሪው።ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች ከሰላሳ ዓመታት በላይ የ‹ዲሞግራፊ› ለውጥ ስለተደረገት ጉዳዩን ውስብስብ ያደርገዋል ይላሉ።
በመሆኑም በቀጣይ ሊኖው የሚገባው አስተዳደር ምን አይነት መልክ መያዝ እንዳለበት ዝርዝር ጥናት ተደርጎ ለየት ያለ እና ዘላቂ መፍትሔ መሻት እነደሚያስፈልግ ያነሳሉ፣እስከዚያ ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፖሊስ ኃይሉንና ሚሊሺያውን አዋቅሮ የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተቋማትን ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው እና ከመሬታቸው ተነቅለው ወደ ሱዳንና ወደ ተለያዩ አማራ አካባቢዎች ተበትነው የነበሩ ወገኖችን በፍጥነት መመለስ ግን ይዋል ይደር የሚባል መሆን የለበትም። በግፍ በክልሉ ሰው በላ ደም መጣጭ ጁንታ በስፋት የተያዙት መሬቶች በፍጥነት ለአራሾቹ መመለስ ይገባቸዋል ይላሉ አቻምለህ ታምሩ በጉዳዩ ላይ በማህበራዊ ገጻቸው “የወልቃይት ጉዳይ” ብለው ባሰፈሩት ጽሁፍ።

የታሪክ ባለሙያው አቻምለህ ሲቀጥል፣ሁለቱ ሰፊ ሥፍራዎች በጉልበትና ታሪካዊ ዳራዎችን ባላገናዘበ አግባብ በትግራይ ክልል ጁንታ በጉልበት ተነጥቀዋል። በወልቃይት ይዞታ ጉዳይ በርካታ ቀዳሚ የታሪክ ማስረጃዎች መኖራቸውን በተለይ የወልቃይት ጉዳይ በአሳማኝ ማስረጃዎች እና መረጃዎች በዝርዝር የተቀነበበ ነው።
ወልቃይትና ራያ መወሰዳቸው ብቻ ሳይሆን ተከትሎ የተፈጠረውን ግፍ በአማራ ክልል ውስጥ ለአብነት አርጎባ እና ኦሮሞ በራሳቸው አመራሮች ይተዳደራሉ፣ በራሳቸው ቋንቋ ይማራሉ፣ በቋንቋቸው ይዳኛሉ ወዘተ፤ የወልቃይት እና ራያ አማራዎች ግን “አማራ ነኝ”፤ በማለታቸውና አማርኛ በመናገራቸው ብቻ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፣ ተሰደዋል፣ በማንነታቸው ምክንያት የሰው ልጅ የማይሸከመውን ስቃይ አስተናግደዋል፣ ተሸማቀዋል ይልና ማይካድራን ሕያው አብነት አድርጎ ያነሳል።

የ29 ዓመታቱ ግፍ ማሳረጊያ በገሀድ ማይካድራና ሁመራ ላይ ታይቷል። በቀጣይ የምንሰማውም የሚዘገንን ይሆናል። በምን ሞራላዊ ህግና ካሳ የእነዚህን ወገኖች ዕንባ ማበስና መካስ ይቻል ይሆን?!ያላል አቻምለህ።

በማይካድራ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያ፣ የፍጅቱ መሪ የክልሉ ዋና አመራር ብቻ ሳይሆን፤ በየደረጃው ባለ አመራር እና ነዋሪዎች ጭምር ተዋናይነት ጅምላ ጭፍጨፋ (Genocide) በጠራራ ፀሐይ ተፈፅሟል።

በአሁኑ ሰአት በግፍ ከቀያቸው፣ ከእርሻቸው፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አማሮች ወደ ሥፍራው በሰፊ ቁጥር እየተመለሱ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በተገቢ መርህን የተከተለ አካሄድ እንዴት የነዋሪዎችን ፍላጎት ባማከለ፤ አግባብ መፍትሔ ይሰጥ የሚለው ቁልፍና በጥናት መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው።
ወልቃይት፣ ጠለምትና ጠገዴ የተደረገው ወረራ እና ነጠቃ ነው። ተራ ሰፈራ አይደለም የተደረገው። የተፈፀመው ወንጀል በቅርብ ይወጣል። የወደፊት የትግራይ ሃገር ምስረታ ኘሮጀክት ሆኖ የተፈፀመ ነበር።

የወልቃይት ጉዳይ በህግ ሳይሆን በፖለቲካ ነው የሚወሰነው። ይሄን ደግሞ በጣም በፍጥነት ማስወሰን ይጠይቃል። ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፤ የሚሉ ፖለተከኞች አሉ።ጉዳዩ ግን ስክነትን የሚጠይቅ እንደሆነ መርሃጽድቅ ያነሳሉ፡

መሬቶቹ የተወሰዱበት አግባብ
ህገ መንግስቱ የፀደቀው በ1987 ነው : ወልቃይትና ራያ ወደ ትግራይ በኃይል ከዚያም በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ትግራይ የተካለሉት ግን በ1982-83 ዓ ም ነው : ታድያ ዛሬ ወልቃይትንና ራያን ወደ እናት ምድራቸው ወደ አማራ ለመመለስ “በህገ መንግስቱን አሰራር ተከትሎ” ይታያል የሚል ማደናገሪያ አይሰራም !ሲጀምር መች በህግ ሄደና ነው በህገ መንግስቱ አሰራር የሚመለሰው : ህገ መንግስት ሳይፀድቅ እኮ ነው በሀይል የተወሰደው ነው ይህም ወደ ሱዳን መውጫ ‹ኮሪዶር› ፍለጋ እነደነበር ከህውሃት መስራቾቹ አንዱ የሆኑት አረጋዊ በርሄ አንስተው ያውቃሉ።

የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) ሊቀመንበር “ራያን በተመለከተ” በሚል ርዕስ የራያን ሕዝብ ትግልና የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚመለከት ሀሳብ ሲሰጡ።ባለፉት 29 አመታት ደግሞ የትህነግን ግፈኛ አገዛዝ በመቃወም ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፤ አሁንም እየከፈለ ይገኛል። ይሁን እንጂ የራያ ህዝብ ይህን ሁሉ ትግል ያካሄደው የተለየ ብሔረሰባዊ ማንነት አለኝና ያንን ለማረጋገጥ ነው ብሎ ሳይሆን ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ለፍትህና ለነጻነት ብሎም ራስን በራስ ለማስተዳደር በማሰብ አንደነበር የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሃባቸውን ሰንዝረዋል።

ለምን ቢባል ምንም እንኳ የራያ ህዝብ ተመሳሳይ የሆነ ባህልና ወግ፣ ስነልቦናዊ አንድነት ያለው እና በኩታገጠም መልከዓ ምድር የሚገኝ ቢሆንም ከብሔረሰባዊ ማንነት አንጻር ከታየ ህብረብሔራዊ መሆኑ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ አይነሳበትምና። ይህም ማለት ራያ ውስጥ የራያ አማራ፣ የራያ ኦሮሞ፣ የራያ አገው እና የራያ ትግርኛ ተናጋሪ ህዝቦች ስላሉ ራሱን የቻለ ብሔረሰብ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ የለም።

በሌላው በኩል የራያ ህዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ የሰነዘረው አማራጭ ሀሳብ ቀደም ሲል ያራምደው ከነበረው አቋም ፍጹም የተለየ ፣የራያ ህዝብ በልዩ ዞን ተደራጅቶ ከወሎ ወገኑ ጋር እንዲሆን ወደ አማራ ክልል መምጣት አለበት የሚሉመ አሉ።
ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ለተመለከተው ዘላቂ እና ሕገመንግስታዊ መፍትሄ እስኪበጅለት ድረስ ያም ቢሆን ክፋት እንደሌለው የህግ ባለሙያ የሆኑት ሙልጌታ ወርቁ ሃሳባቸውን ሰጥተውናል።

እንደ መውጫ ድህረ ህውሃት ኢትዮጵያ ተግዳሮት አልባ እንደማትሆን እና ከፊት ያሉትን አጀንዳዎች በጥንቃቄ እና ሌላ ቀዳዳ በማይከፍት መልኩ መፈታት ይገባል።በህግ ስላልሄደ በህግ አንጠይቅም በማለት ከ ሃሳብ አቀንቃኞች እና በተቃራኒው ሃሳብ ከሚያምታቱ የብልጽግና ሹማምንት አጀንዳ ወጥቶ ሰፊውን ስእል ማየት ተገቢ ነው።በጋራ ለመኖር መዘጋጀት እንደሚገባ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com