ኮቪድ 19 እና ‹መልካም› አጋጣሚው – በጤና አገልግሎት

Views: 165

የ53 ዓመቷ ዝናሽ አየለ ከሳምንቱ አራቱን ወይም አምስቱን ቀናት ሆስፒታል ማሳለፍ ግድ ካላቸው ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። እንደ ባለሥራ ማልዶ ሆስፒታል መሄድና መመለሱን ሰለቸኝ ብለው አያውቁም። ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከመሰማቱ ኹለት ሳምንት ቀደም ብሎ ያደረጉት የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምናም፣ የተለመደና ከአምስት ዓመት በላይ የቆዩበትን የሕክምና ክትትላቸውን አጥብቀው እንዲገፉበት አድርጓቸዋል።

በየካቲት 12፣ ዘወዲቱ ሆስፒታል እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መደበኛ የሕክምና ክትትል አላቸው። ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ግን ፍርሃትና ስጋት ያዛቸው። ‹ላም እሳት ወለደች› እንዲሉ ዓይነት ተረት፣ ወደ ሆስፒታል እንዳይሄዱ የወረርሽኙ ስጋት፣ እንዳይቀሩ ደግሞ የጤናቸው ነገር ሐሳብ ሆነባቸው።

ለመቋቋምና ለመጋፈጥ በሚደረገው ሩጫ መካከል ሌሎች ሕመሞች እንዳይዘነጉ የሚለው ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ነበር። ይህንንም ተከትሎ የጤናው ዘርፍ እንቅስቃሴ ማሳየት ጀመረ። እናም ዝናሽ ጋር አንድ ቀን ስልክ ተደወለላቸው። ከየካቲት 12 ሆስፒታል። ጤናቸው እንዴት እንደሆነና በቀጠሯቸው ቀንም ከሆስፒታል እንዳይቀሩ የሚል መልዕክት ደረሳቸው። ከነበረባቸው ስጋት በተጓዳኝ ይህ ለጭንቀታቸው እረፍት የሰጠ ኹነት ነበር።

በኢትዮጵያ ብዙ መሻሻሎችን ከሚፈልጉ ዘርፎች መካከል አንደኛው የጤና አገልግሎት ስርዓት ዘርፍ መሆኑ እሙን ነው። የጤና አገልግሎት ሲባልም ለደንበኞችና ታካሚዎች ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር የሚተነተን ነው። ይህም ከአቀባበል ጀምሮ ክትትልና የተሟላ ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲሁም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሟላትን ይጠይቃል።

በመመላለስ የሕክምና ክትትል የሚያደርጉ እንደ ዝናሽ ያሉ ሰዎች፣ ኮቪድ 19 እንደ አምላክ ቁጣ ክፉ የሆነ ክስተት ነው ይበሉ እንጂ፣ ያንን ተከትሎ የመጣ መልካም ነገር እንዳለ አይደብቁም።

‹‹ድሮ ካርድ ለማውጣትና ሐኪሙን ለማግኘት ድካሙ ቀላል አልነበረም። አሁን ግን እንደውም ራሳቸው ደውለው ነው ቀጠሮዬን የሚያስታውሱኝ፣ እንዳልቀር የሚያሳስቡኝ። አንዳንዴም ደኅንነቴን ብቻ ለመጠየቅ ይደውላሉ›› ሲሉ መገረማቸውን ጠቅሰው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

‹‹በሕክምና ክትትል ረጅም ጊዜ ቆይቻለሁ። የምሄድባቸው ሆስፒታሎች ንጹህ አልነበሩም፣ መስተንግዶም ላይ የሚነጫነጨው ነበር የሚበዛው። ግርግሩም ቀላል አልነበረም። በዛ ላይ ወረርሽኝ ሲጨመርበት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ነበር የገመትኩት። ቀላል ሊሆን አይችልም። ነገር ግን በፊት ከነበረው የተሻለ ነገር ደግሞ ዐይቻለሁ።›› ዝናሽ ቀጥለው ያሉን ነው።

‹‹እንደውም…›› አሉ፤ ‹‹እንደውም ይህ ወረርሽኝ ጥሩ ነገር አመጣልን ይሆን አሰኝቶኛል።›› በገጻቸው ፈገግታን አክለው። እውነት እንዲህ ያለ ወረርሽኝ በጤና ስርዓት ላይ በጎ ለውጥ እንዲመጣ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ወይ? አዲስ ማለዳ ጠይቃለች።

ምዕራብ አፍሪካን እንደ ማሳያ
በእርግጥ ኮቪድ 19 የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርኣት ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ብሎ መናገር ቀልድ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ግን በፈተና ውስጥ አዲስ መንገድና ጥንካሬ ይወለዳል እንዲሉ፣ ይህን መሰል ፈተና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የተሻለ የጤና ስርዓትን ሊወልድ ይችላል የሚሉ ዕይታዎች አሉ።
ወደ ምዕራብ አፍሪካ እናቅና፤ በአካባቢው ሴራሊዮን፣ ጊኒ እና ላይቤሪያ በኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ተመትተዋል። ይህ በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2014 የጀመረ ወረርሽኝ ዓመታትን ተሻግሮ አሁን ድረስ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። ወረርሽኙ በአገራቱ የነበረው የጤና ስርዓት ምን ያህል ደካማና ‹የለም› ከማለት የማይተናነስ እንደነበር ያጋለጠም እንደሆነ በወቅቱ የነበሩ ዘገባዎች ሽፋን የሰጡት ጉዳይ ነው።

በእድሜ አንጋፋና የቀደሙ ከሚባሉ ጥናታዊ መጽሔቶች (ጆርናል) መካከል ተጠቃሸ የሆነው የብሪቲሽ የሕክምና ጥናቶች መጽሔት (BMJ Medical Journal) የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን በአንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አስነብቧል። ይህም ‹ከ2014-2015 የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ የኅብረተሰብ ጤና ላይ ያደረሰው ተጽእኖና ለወደፊት የፈጠራቸው እድሎች› በሚል ርዕስ የቀረበ ነው።

ይህ ጥናት ወረርሽኙ የምዕራቡን አፍሪካ ክፍል ምን ያህል ክፉኛ እንደጎዳው አስረድቷል። በተለይም የጤና ባለሞያዎች እጥረትና በቫይረሱ የተነሳም ብዙዎቹ መሞታቸው ጥፋቱን አስከፊ እንዳደረገው ጠቅሷል። ቫይረሱ እንዲሰራጭ ያደረገውም በቂ ያልሆነ የጤና ተቋም፣ ያልተሟላ ቁሰቁስ፣ ደካማ የሆነ አመራር፣ የጤና ባለሞያች እጥረት እንዲሁም የገንዘብ ችግር፣ ከሌሎች ጤና ነክ ካልሆኑ ችግሮች በተጓዳኝ ተጠቃሽ ነበሩ።

ሌሎችም ቢዘረዘሩ የማያልቁና የቱም ሰው ሊገምታቸው የሚችሉ ችግሮች ተዳምረው በአካባቢው የነበረውን ዳዴውን ያልጨረሰ የጤና አገልግሎት ስርዓት የበለጠ አቀጭጨውታል። ከዚህ በኋላ ነው፣ የዓለም ትኩረት ወደ ምዕራብ አፍሪካ የዞረውና ምክረ ሐሳቦች ከዛም ከዚህም የተነሱት። ይህም የመልካም አጋጣሚ መግቢያው ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት ሰፊ የጤና ምርመራዎች እንዲካሄዱ፣ በተለያዩ ስልቶች ሕሙማንን መለየትና ስርጭቱን መቆጣጠር የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲኖር መከረ። ይህንን ተከትሎ ኢኮኖሚው ተዳከመ፣ ድህነት ተባባሰ፣ የምግብ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ገባ።

ሆኖም ይላል ጥናቱ፣ ሆኖም ኢቦላ ሊጠቀስ የሚገባና በዘላቂነት ጥበቃ የሚያሻው ለውጦችን አስመጥቷል። አንደኛውም በአካባቢው ለጤና ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ማስቻሉ ነው። ለምሳሌ ጊኒ ለጤና ዘርፍ የመደበችውን በጀት ስትጨምር፣ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ የጤና እንክብካቤ ባለሞያዎችን በአንድ ጊዜ ቀጠረች።
ከዚህ በተጨማሪም ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የተገኘው ድጋፍ ቀላል የሚባል አልነበረም። ይህም የጤና ስርዓትን ለመሻሻል የዋለ እንደሆነ ጥናቱ ጠቅሷል። በዚህም የበሽታ (ኢንፌክሽን) ቁጥጥር ብቃት፣ ለጤና ጥበቃ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲሁም የበሽታ ክትትል አቅም አድጓል። በተጨማሪም ክትባቶችን ለማዘጋጀት የተፈጠሩ ዓለማቀፍ ግንኙነቶች ለአገራቱ ልምድ ማግኛ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ይህ ሁሉ ትንሽ የሚመስል ለውጥ ተዳምሮ አገራቱ ወረርሽኙን በተወሰነ መንገድ ቢሆንም እንዲቆጣጠሩት አስችሏል። ለሌላ ማንኛውም ወረርሽኝም ዝግጁ አድርጓቸዋል።

ኮቪድን እንደ መልካም አጋጣሚ?
የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዝደንት ዶክተር ተግባር ይግዛው እንዲህ ያሉ ፈተኛ የጤና ችግሮች የሚከሰቱባቸው ወቅቶች ለጤና አገልግሎት ስርዓት መሻሻል ትልቅ እድል ናቸው ይላሉ። ‹‹እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ያለንና የሌለንን፣ ድክመትና ጥንካሬን ለመለየት ያስችላሉ። አንዱ የሚጠበቅና ዘመናዊ የሚባል የሚማር የጤና ስርዓት የሚባለው ከውድቀቱም፣ ከጥንካሬውም፣ ከድክመቱም የሚማር ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ እንደ ማኅበረሰብም፣ እንደ ጤና ስርዓትም የጤና ተቋማት ችግሮች ምንድን ናቸው የሚለውን ዐይተናል።›› ሲሉ አክለዋል።

አያይዘውም እድሉን ከተጠቀምንበት የምንማረው አለ ያሉት ባለሞያው፣ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ የተቋቋመው የሙያ ማኅበራት ምክር ቤት ዓላማም በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ የጤና ስርዓቱ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ምን ይማራል የሚለውን ለማየት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

መሠረት ጫኔ በአርሾ ላቦራቶሪ የላቦራቶሪ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው በበኩላቸው በቅርበት ከሚያውቁት በመነሳት ኮቪድ 19 ከላቦራቶሪ አገልግሎት አንጻር ያለንበትን ደረጃ ያሳየንና ያስተማረን ነው ብለዋል። አገልግሎትን በተሻለ መንገድ ለማስተካከልና በዘርፉም አቅም ለማሳደግ አዲስ ዘመን አምጥቷል ባይ ናቸው። ከማኅበረሰብ ጤና አንጻርም በተለይ ከንጽህና ጋር በተገናኘ ጥሩ ግንዛቤ አምጥቷል በማለት አክለዋል።

‹‹እጅ መታጠብ ተገቢ እንደሆነ ማንም ሰው ያውቃል። ተግባር ላይ ነበር ድክመታችን። በሚያስፈልገን መጠንና ሁኔታ አገልግሎቱ ነበር ለማለትም ያስቸግራል። ያንን እንድናስተካክል ረድቶናል። ከጽዳት ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችም ቀንሰዋል።›› ሲሉ በጤናው ዘርፍ ሊጠቀስ የሚችል ጉልህ በጎ አጋጣሚ እንደተፈጠረ ጠቅሰዋል።
ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ወንድማገኝ ወንድሙ (MPH) ‹በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ፈተናና መልካም አጋጣሚ› በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የዳሰሳ ጥናት፣ ይህን ተመሳሳይነት ያለውን ነጥብ እንመለከታለን። ከባድ ሁኔታዎች ፈተናዎችን ብቻ ሳይሆን ፍሬያማ የሚያደርጉ እድሎችን ያመጣሉ ብሎ የሚጀምረው የዳሰሳ ጥናቱ፣ ይህንንም መሠረት አድርጎ ወረርሽኙን ተከትሎ ለጤና አገልግሎት ስርዓቱ የመጡ ጥሩ የሚባሉ አጋጣሚዎችን ይጠቅሳል።

ከእነዚህም አንደኛው ከሕክምና ጋር የተገናኙ ጥናቶች እንዲደረጉ እድል የፈጠረ መሆኑ ነው። ክትባቶችን ለማዘጋጀትም ቤተሙከራዎች ተከፍተዋል፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ለወትሮ ሥራቸው እንደሆነ የዘነጉትን ጥናታዊ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያነቃቃ ነበር በማለት ይጠቅሳል፤ ጥናቱ። ያም ብቻ አይደለም፣ የባህል ሕክምናም ግምት ውስጥ የገባው በዚህ ወረርሽኝ መነሻነት ነው የሚል ነጥብ ተቀምጧል።

በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ሽግግር በስፋት ታይቷል። ከላይ በመግቢያችን ያነሳነው ታሪክ ለዚህ ማሳያ ነው። እንደ ዝናሽ ያሉ ተከታታይ የሕክምና ክትትል የሚጠይቅ ሕክምና ያላቸው ሰዎችን በስልክ ደውሎ መከታተልና ማስታወስ፣ ያሉበትን ሁኔታም መመርመር አንዱ ነው። በየወረዳው ያሉ የጤና ቢሮዎች በየቤቱ እየተንቀሳቀሱ ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ለመለየት ያደረጉት ጥረትም በተመሳሳይ የተቀናጀና የተሰባሰበ መረጃ ለማግኘት የሚያግዝ እንደሆነ ነው የተጠቀሰው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች ያሳይዋቸው የአገልግሎት ለውጦች በእርግጥም ወረርሽኙን ተከትለው የመጡ ይሁኑ እንጂ፣ ከለውጦቹ ውስጥ ባለድርሻ አካላት በየጊዜው ለማሻሻል ቃል የገቧቸው ይገኛሉ። ያም ሆነ ይህ በድንገት የተከሰተው ኮቪድ 19 ለውጦች ባልታሰበ መንገድ እንዲታዩ አስችሏል። ይህ በቂ ሆኖ አይደለም፣ አሁንም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለም ወረርሽኙ ግልጽ አድርጓል።

የሁሉም ጥያቄ ደግሞ የቀጣይነቱ ነገር ነው። እነዚህ ወረርሽኙን ተከትሎ የታዩ የአገልግሎት፣ የንጽህና እንዲሁም ጥንቃቄና መሰል እንቅስቃሴዎች ባሳዩት መልካም ለውጥ ይቀጥላሉ ወይ? ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ከኮቪድ 19 መከሰት በኋላም ሆነ በፊት የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን ለማስቀጠል እሠራለሁ ብሏል። ለድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችም ጠንካራ ምላሽ የሚሰጥ አሠራር እንገነባለን ማለቱን ከጤና ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ተመልክተናል። ይህም በጊዜ ተፈትኖ የሚታይ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com