ኮቪድ 19 እና የአዕምሮ ጤና ጉዳይ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ››

Views: 174

በኤርሚያስ ሙሉጌታ

ከአዲስ አበባ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በ50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ  በሰባት ሐይቆቿ ታጅባ በምትገኘው ሞቃታማዋ የቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ነው። የባለ ታሪካችን የመኖሪያ አድራሻን እና ትክክለኛ ስም ከመጠቀም በመቆጠብ አዲስ ማለዳ ከስፍራው በመገኘት የሰበሰበችውን እና ታዘበችውን ግን እንደሚከተለው ለማድረስ ሞከራለች።

ታሪኩ ይበልጣል (ስሙ ተቀየረ) አዲስ አበባን ለቆ ቢሾፍቱ ከከተመ መንፈቅ ሊደፍን ምንም አልቀረውም። ለበርካታ ዓመታት በአገረ አሜሪካ የኖረው ታሪኩ ባለፈው ዓመት 2012 የመጀመሪያ ወራት ላይ በአዕምሮ ጭንቀት ምክንያት አሜሪካን ጥሎ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመራ ተገዶ ነበር። በወቅቱ ታዲያ ወደ አገር ቤት በመጣበት ወቅት ወገን ዘመድ ተረባርበው በመጀመሪያ የአዕምሮ ሐኪም ዘንድ ሕክምናውን እንዲከታተል ካደረጉት በኋላ እና ከኹለት ወር በኋላ ትንሽ ማሻሻል እያሳ ነ በነበረበት ወቅት ሕክምናውን አቋርጠው ወደ ዕምነት ስፍዎች (ፀበል) ቦታዎች ይወስዱታል። ታሪኩ ታዲያ ይወስድ የነበረውን መድኃኒት አቋርፆ ነበር እና ወደ ጸበል ስፍራ ያመራው የጤናው ሁኔታ ከመሻሻል በተቃራኒ መባባስ ይጀምራል ። ጉዳዩን በሚመለከት የባለታሪካችን እናት ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ ‹‹ወንድሞቹ እና እህቱ በአንድ ላይ ሆነው ሐኪም ዘንድ አድርሰውት ነበር፤ ነገር ግን የጤናው መሻሻል ዝግ ያለ ስለነበር ዘመድ ወደ ጸበል እንድንወስደው ገፋፋን ። እኛም የወዳጅ ዘመድ ምክርን ሰምተን ወደ ጸበል ቦታ ከሐኪሞች የተሰጠውን መድሐኒት እንዲያቋርጥ አድርገን ወሰድነው ነገር ግን እንደምታየው ምንም ለውጥ አላየንበትም እንዲያውም ከአሜሪካ መሲመጣ ከነበረበት የባሰበት ይመስላል›› ሲሉ በሩህሩህ የወላጅነት ዓይናቸው ተስፋ ባልቆረጠ እና በይድናል ተስፋ ሰንቀው እየተመለከቱት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በጸበል ስፍራ አንድ ወር ከቆዩ በኋላ የታሪኩ ጤና እንደተባለው መሻሻል እና ወደ ቀደመው የጤነኝነት አቋም አለመመለስ አዲስ አበባ ወደሚገነው መኖሪያ ቤታቸው ሔደው ያቋረጠውን መድኃኒት እንዲወስድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። በአፋጣኝ ወደ ተግባር የተቀየረው ውሳኔያቸው አዲስ አበባ በመምጣት ታሪኩ ያቋረጠውን መድኃኒት ከሐኪሞች ጋር በመነጋገር መውሰድ ይጀምራል ጤንነቱም ወደ ነበረበት ለመመለስ ምልክቶችን እና መሻሻሎችን ማሳየት ይጀምራል። ይሁን እንጂ ረጅሙ እና ጊዜ የሚጠይቀው የታሪኩ የጤና መሻሻል ጉዳይ ወደ አገራችን ኮቪድ 19 መግባቱን ተከትሎ ከፍተኛ እንቅፋት ገጠመው። የአዕምሮ ሕክምና ማዕከል ነበረው ኤካ ኮተቤ የለይቶ ማቆያ ማዕከል ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የአዕምሮ ሕሙማን ሕክምና በከፍተኛ ሁኔታ ሳንካዎችን መጋፈጥ ግድ ሆነበት። በኤካ ኮተቤ ተኝተው ለሚታከሙ ሰዎች በመንግሥት ጤና ጣቢያዎች በኩል አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ የሚያስታውቅ መመሪያም ወጥቶ ነበር። ይህ ግን አልነበረም ታሪኩን የጎዳው፤ ሰው በተሰበሰበበት ስፍራ መገኘት በኮቪድ 19 አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንብ መሰረት የተከለከለ መሆኑ እና ይህንንም ተከትሎ ለብቻው (በታላቅ እህቱ ቤት ነበር የሚኖረው) ረጅም ሰዓታትን መዋሉ። በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ በሳምንት ሦስት እና ከዛ በላይ እየተመላለሰ ከሐኪም ጋር የሚገናኘው እና ገጽ ለገጽ ሕክምናው በአንድ ጊዜ መቋረጡ ነው። መድኀኒት ብቻ ምንም ለውጥ ማምጣት ያልተቻለበት የታሪኩ የአዕምሮ መታወክ ዕዳውን በቤተሰብ ላይ ማብዛት ጀመረ። ብዙም ቁጡ ያልነበረው እና ብስጩነት ማይታይበት የነበረው ታሪኩ ቤት መዋል እና ከቤት መውጣት በማይቻልባቸው ቀናት ቤተሰቦቹን ለመደብደብ እስከመቃጣት መድረስ ይጀምራል፣አንዳንድ ጊዜም ደግሞ እርቃኑን ለመሆን መፈለግ እና አዳዲስ ችግሮች ማሳየት ይጀምራል።

በታሪኩ አይነት የሕመም ደረጃ የሚገኑ ሰዎች በዋናነት ተኝተው መታከም የሚገባቸው እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከፍተኛ የአዕምሮ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ዮናስ ላቀው ነገር ግን ተኝተው መታከም ያልተቻለበት ምክንያት በወረርሽኙ ምክንያት ሕክምና አሰጣጡን ከባድ እንደሆነባቸው እና በከፍተኛ መጠን ታካሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ መገደዳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ይህም ታዲያ ዶክተር ናስ ሲናገሩ ጫናው ቤተሰብ ላይ እንደሚሆን እና በተለይም ደግሞ እናቶች ላይ ከፍተኛ ሆነ ችግር እንደሚጋረጥባቸው ይናገራሉ። እንደምክንያት የሚያነሱት ደግሞ በቤት ውስጥ እናቶች እንዲህ አይነት የአዕምሮ እክል ያለባቸውን ልጆቻቸውን በዋናነት የመንከባከብ ኃላፊነት ስለሚጣልባቸው በልጆቻቸው ጥቃት ሊደርስባቸው እና ሊጎዱ ሚችሉበት አጋጣሚ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ያለውን የመጀመሪያ ወራት የኮቪድ 19 አዋጅ ተከትሎ ከሰዎች በመገለሉ እና ለብቻው በመቀመጡ የጤና ሁኔታው የተባባሰበት ታሪኩ ታዲያ በተደጋጋሚ በሚኖርበት እህቱ ቤት እንድ ክፍል ውስጥ እጁን እና እግሩን ለመታሰር ደርሶ ነበር። አዲስ ማለዳ ባየችጊዜ ለመታዘብ እንደቻለችው እጅጌ ጉርድ ሸሚዝ በማድረጉ በኹለቱም ክንዶቹ ላይ በገመድ የታሰረበት ምልክት በክፉኛ የመቁሰል ደረጃ ላይ ደርሶ አይታለች። ‹‹አሁን ወደ ቢሾፍቱ መጥ ከእኔ ጋር መኖር ሲጀምር እና ወጥቶ መንቀሳቀስ እንዲሁም ሰዎችን ማግኘት ሲጀምር በትልቅ ደረጃ ተሸለው እንጂ በመጀመሪያ ወቅት እማ እኔንም ሊገድኝ ይፈልግ ነበር›› ይላሉ የታሪኩ እናት።

እንደ ታሪኩ አይነት በርካታ ሰዎች ወደ አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማምራት የሕክምና ዕድል እንዲያገኙ እንደሚጠይቁ እና ከኮቪድ 19 ወዲህ ደግ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ዶክተር ዮናስ ይናገራሉ። ‹‹ከዚህ በፊት የሕክምና ታሪክ በሆስፒታሉ ያላቸውን ሳይጨምር አዳዲስ እና በተመሳሳይ በዋናነት በድባቴ ሕመም ተጠቅተው ወደ ሆስፒታላችን ሚመጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል። በቅርቡ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ጥናት በማካሔድ ወረርሽኙ በአዕምሮ ጤና ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ይፋ እንደርጋለን›› ሲሉም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ 19 ወረርሽ ግብረ ኃይል የቡድን መሪ ሆኑት ያለው ጌታቸው እንደሚሉት በእርግጥም በኮቪድ 19 ምክንያት የአዕምሮ ጤና ጉዳይ ትኩረት መነፈጉን እና ይህም ደግሞ በርካታ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል አስታውሰዋል። በተለይም ደግሞ በሆስፒታሎች ዘንድ ተሰራው የኮቪድ 19 ማቆያ ማድረግ ጉዳይ የአዕምሮ ሕክምና ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።

በእርግጥ በአዕምሮ ጤና ረገድ ከኮቪድ 19 በፊትም መዘናጋቶች እና በጤና ሚንስቴር ዘንድም ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው እንዳልነበር አዲስ ማለዳ ከዓመት በፊት ባደረገችው ማጣራት ለማወቅ ተችሏል። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ሚንስቴር ለአዕምሮ ጤና የበጀቱን 1 በመቶ ብቻ እንደሚበጅትለትም አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በጤና ሚንስቴር መመሪያ መሰረት እያንዳንዱ የመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ከ15 እስከ 20 አልጋዎች ለአዕምሮ ሕሙማን ተኝቶ መታከሚያ እንዲመድቡ ያዛል። ነገር ግን አሁንም በአዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ 5 የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ባደረችው ምልከታ ለአዕምሮ ሕሙማን ተኝቶ መታከሚያ በድምሩ 17 አልጋዎችን ነበር ማግኘት የተቻለው።

የዓለም የጤና ድርጅት በኮቪድ 19 ዘመን የአዕምሮ ጤና ሁኔታ ትኩረት እንደተነፈገው እና ከፍተኛ ድጋፍ የሚያሻው ደረጃ ላይ መድረሱንም አስታውቋል። በጥቅምት ወር 2020 ባወጣው ጥናቱ በ130 አገራት ላይ ባደረገው ጥትና ከፍተኛ ሆነ አዐምሮ ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን እና ጥናት ካደረገባቸው አገራት ውስጥ 93 በመቶ የሚሆኑት ላይ መታየቱንም አስታውቋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com