የእለት ዜና

ዝክረ ተስፋዬ ገሠሠ

ታላቁ የጥበብ ሠው ተስፋዬ ገሠሠ የተወለዱት መስከረም 17/1929 በኢትዮጵያ የምሥራቁ ክፍል፣ ሐረር ልዩ ሥሙ ጎሮ ጉቱ በሚባል አካባቢ ነበር። ተስፋዬ ለወላጆቻቸው ብቸኛ ልጅ የነበሩ ሲሆን እንዳለመታደል ሆኖ ገና የኹለት ዓመት ከስምንት ወር ሕጻን ልጅ እያሉ ነበር እናት እና አባታቸውን በሞት የተነጠቁት። ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአክስታቸው ጋር መኖር ጀመሩ። በታዳጊነታቸው የቤተክርስትያን ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን መዝሙረ ዳዊትን ደግመዋል፤ የጸሎት መጻሕፍትንም በሚገባ ተምረዋል። በስምንት ዓመታቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በመግባት መደበኛ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ።

በመቀጠል የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በወቅቱ ቀዳማሚ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሎጅ ይባል በነበረው የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በ1951 የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በ‘ሂውማኒቲስ’ ትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል።

በዚህ ወቅት ለተስፋዬ አንድ ሕይወታቸውን ሊቀይር የሚችል አጋጣሚ መጣ፤ ይህም ተስፋዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበሩነት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን የእዮብን ታሪክ በመድረክ ላይ ሲሠሩ የተመለከቱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመድረኩ ላይ ታድመው ነበር። ይህን ያዩትም ንጉሡ ‹‹ቴአትር መማር እንዳለብኝ አሳሰቡኝ።››ሲሉ ተስፋዬ ከመጽሔቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ነበር።

ከመጀመሪያ ድግሪ በኋላም ባገኙት የትምህርት ዕድል ወደ ሰሜን አሜሪካ በማምራት ኢቫንስትን በሚገኘው ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ትወና፣ ዳይሬክቲንግ እና የመድረክ ግንባታ በስኬት ካጠናቀቁ በኋላ በ1954 የኹለተኛ ዲግሪያቸውን ጭነው ወደ አገር ቤት ተለመልሰዋል።

ትምህርታቸውን ተከታትለው ከመጡ በኋላም ተስፋዬም የእነ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ዱካ በመከተል የቴአትር ዓለምን ተቀላቀሉ።
‹‹ቴአትር እድገት ከጊዜው ጋር እንዲሄድ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረት እንዲሆንና ከባህላዊ አሠራር እንዲወጣ እንዲሁም በዘልማድ እናዳይሠራም አድርገናል።›› በማለት ነበር ተስፋዬ በወቅቱ ስላመጡት ለውጥ የተናገሩት።

ይህም ብቻ አይደለም ተስፋዬ የሰሩት ቴአትርን በተመለከትም፤ የቴአትር አጻጻፍ ስልትም በሚገባ በማስተማር ድርሻቸውን የተወጡ እንቁ ባለሙያ እንደነበሩም ሁሌም የሚታወስ ነው።

አንጋፋው የጥበብ ሠው ተስፋዬ ከመጽሔቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ከነበሩት ጉዳዮች መካከልም ‹‹በወቅቱ ብቁ የሆነ የቴአትር ባለሙያ አልነበረም እናም እኔ ቴአትሮችን እየጻፍኩ ዳይሬክትም አደርግ ነበር።›› ብለዋል።

በኪነጥበብ ዓለም ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ መሥራት የቻለው አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴም ከመጽሔቱ ጋር ባደረገው ቆይታ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ቴአትር እድገት ስላበከቱተ ነገር ምስክርነቱን ሲሰጥም እንዲህ ነበር ያለው ‹‹የኢትዮጵያን ቴአትር ዘመናዊ የሆነ አቀራረብ ወይም ስልት በማስተዋወቅ ከሠሩት ጥቂት ባለሙዎች መካከል ተስፋዬ አንዱ ነው።››

ተስፋዬ በበርካታ ሥራዎች ላይ በተዋናይነትም መሳተፍ የቻሉ እንቁ ባለሙያ የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህም ሥራ የሆነውን ‹‹የእሾህ አክሊል››፣ በመንግሥቱ ለማ ዳይሬክት የተደረገውን ‹‹ጸረ-ኮሎኒያሊስት››፣ የመላኩ አሻግሬ ሥራ የሆነውን ‹‹ዓለም፣ ጊዜ እና ገንዘብ›› የተሰኙ ይገኙበታል። በተለይ ‹‹ዓለም፣ ጊዜ እና ገንዘብ›› የተባለው የመድረክ ሥራ በወቅት በነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ትዕዛዝ ከአንድ ጊዜ የመድረክ ዕይታ በኋላም የታገደ ሥራ ነበር።

በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዘርፍ ከ60 ዓመት በላይ ያገለገሉት የባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤት የሆኑት ተስፋዬ፥ በትወና እና በዳይሬክቲንግ ሥራዎች ብቻ አልተገደቡም፤ የራሳቸውን ወጥ ድርሰቶች እንዲሁም የትርጉም ሥራዎች አበርክተዋል። ከድርሰት ሥራዎች መካከለም ‹‹የሺ›› የሚሰኘው በአማርኛ ቋንቋ ካበረከቱት መካከል የሚጠቀስ ሲሆን በእንግሊዝኛም ‹‹ላቀችና ማሰሮዋ›› የሚል ተውኔት ደርሰዋል።

ተስፋዬ ከትወና፣ ከድርሰት እና ከዳይሬክቲንግ በተጨማሪም የአገር ፍቅር ቴአትር ቤትንም በሥራ አስኪያጅነት ማገልገል ችለዋል።
የቴአትር ቤቱ መድረክ በዘመናዊ መልክ በማስገንባት ተጠቃሽ ሥራ የሠሩት ተስፋዬ፥ በጥበብ ሥራ አበርክቷቸውም እጅግ በጣም የተወደደላቸውን ‹‹ማነው ኢትዮጵያዊ?›› የሚለው ሙዚቃዊ ተውኔት በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ ለመድረክ ከበቁት ሥራዎቻቸው ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ ዘርፍ የተስፋዬ አበርክቶ የላቀ መሆኑን አንጋፋው ሥመጥር ተዋናይ የሆነው ደበበ እሸቱ ምስክርነቱን በያዝነው ዓመት የ84 ዓመት ልደታቸውን አስመልቶ በተዘጋጅ መድረክ ላይ ‹‹እኛን እንደ እርሳስ ቀርጾን ለዚህ ያበቃን እሱ ነው›› በማለት ተናግሯል።

ተስፋዬ የቴአትር ቤት ኀላፊ ሆነው በሚመደቡበት ሁሉ የመድረክ ግንባታ ላይ ትኩረት በመስጠት እንዲዘምንና ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ በማድረግ ከሌሎች በተለየ አሻራቸውን አሳርፈዋል። ለክዋኔ ትዕይንቱም የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን እና መሣሪያዎችን በማሟላት በትኩረት ሠርተዋል ሲሉ ባልደረቦቻቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በ1956 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል እንዲመሰርት ሲሠሩ ከነበሩት ሠዎች ውስጥ ተጠቃሽም ናቸው – ተስፋዬ።
በ1971 ደግሞ የቴአትር እና የኪነጥበብ ክፍል እንዲቋቋም የሠሩት ሥራ ቀላል የሚባል እንዳልሆን ሥራው ይመሰክራል።
ማዕከሉ በተስፋዬ በሚመራበት ጊዜም ታዋቂው ኦርኬስትር ኢትዮጵያ ተቋቁሟል። ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ እድገትም ጉልህ ሚና መጫወቱን ብዙዎች ሲጠቅሱ ይሰማል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ለዘመናዊ የሙዚቃ እድገት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል›› ሲሉ በአጽንዖት ይገልጻሉ።

በዚህም ተስፋዬ ማዕከሉን ውስጥ በነበሩበት ጊዜ በቁጥር ሊሰፈር እና ሊለካ የማይችል ሥራዎችን አበርክተው ያለፉ ስለመሆናቸው ከማንም የሚሸሸግ አይደለም።
ብቻ ተስፋዬ እዚህ ለደረሱበት ስኬታማ ሕይወት ድርሻ የተወጣላቸው ነገር ቢኖር በጣም ቀለል ያለ የሕይወት ስልትም በመከተላቸው ነው። ይህም ከጭንቀት የራቀ ሕይወት እንዲኖራቸው በማድረጉ ደስተኛ ሕይወትን እንዲያሳልፉ አድጓቸዋል።

‹‹እግዚአብሔር ያውቃል›› በማለት ፅኑ እምነት የነበራቸው ተስፋዬ ‹‹በአንድ ወቅት አንድ ዶክተር አብቅቶልሃል ብሎኝ ነበር ግን ሕይወቴ በተአምር በቅዱስ ሚካኤል ጸበል ተርፋች›› በማለትም ያላቸው ጽኑ እምነት ከመጽሄቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ነበር።

ተስፋዬ ከጠቀስናቸው ሥራዎች በተጨማሪም የኡመር ካየምን መጽሐፍ ‹‹ሩብ አያት‹‹ በማለት ተርጉመው ማሳተም ችለዋል ‹‹ እዚህ ሥራ ላይ ተስፋዬ የቋንቋ ሀብታምነቱን እና የቋንቋ ጥራቱን ያሳየበት ነው ›› ሲል አሰፋ ምስክርነቱን መስጠት ችሏል።

የተስፋዬ ታሪክ ቢዚህ ብቻ አይቋጭም ፤የደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋይ የሆኑንት የኔልሰን ማንዴላ ግለ ታሪክ ላይ ያተኮረውን ‹‹ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም››ን ጨምሮ ከ10 በላይ መጸሐፍትን ማበርከት የቻሉም ጸሐፊ ነበሩ።

በተጨማሪም ተስፋዬ በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችንም አገልግለዋል። ከነዚህ መካከል ፤ኢትዮ ቴሎኮም ወይም በቀድሞ ስሙ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠቃሾቹ ናቸው።

60 ዓመታትን ያለምን ዝቅታ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ዘርፍ ብዙ ሥራዎችን ያበረከቱት ተስፋዬ፤ በሠሩት ሥራም ለኹለት ጊዜያት ያህል ለእስር ተዳርገው ነበር።
ተስፋዬ‹‹እቃው›› የተሰኘው ሥራቸውም ለእግድ ተዳርጎ የነበረ ሲሆን በደርግ ዘመነ መንግሥትም ለእስር ተዳርገዋል ይህም ለኪነጥበብ እድገት የተከፈለ ዋጋ ነው።
ያላቸውን እውቀት ያለምንም ስስት ለኪነጥበቡ ያዋሉት ተስፋዬ ዜና እረፍታቸው ሲሰማ ተማሪዎቻቸው እንዲሁም የኪነጥብ ባለሙያ የሆኑ ሠዎች ሀዘናቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል።

ከነዚህም መካከል የቀድሞ ተማሪያቸው የነበረው ነብዩ ባዬ ‹‹መምህራችንን ጋሽ ተስፋዬ በአካለ ስጋ ተለይቶናል። አዋቂ፣ ብርሃናማ፣ የወጣለት ምሁር፣ ቅን የንጉሥ ምርጥ፣ የቴአትር ሞያ ሞገስ፣ የመጀመሪያው የአገራችን የቴአትር ተመራቂ። ዘመናዊ የቴአትር አስተዳዳሪ። የሚዲያ መዝናኛ ፕሮግራም ጀማሪ፣ ፅኑ ደራሲ፣…ድንቅ ተርጓሚ…የዑመር ኻያም ጓደኛ…ግሩም ተዋናይ። አንዱ ብዙ ጋሽ ተስፋዬ እግዚአብሔር ነፍስህን ከደጋጎቹ አጠገብ ያኑርልን።›› በማለት ነበር የመምህሩን ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሃዘን የገለጸው።

ሌላው የሙዚቃው ሊቅ ሰርጸፍሬ ስብሃትም እንደ ነብዩ ባዬ ሃሳቡን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዲህ ሲል ከትቧል ‹‹እውነተኛው የቴአትር ምሁር፣ የዘለቀ የጥበብ ዕውቀትን ከተማሪ ቤት በመቅሰም የመጀመሪያው፣ታላላቆቹን የጥበብ ተቋማት በኀላፊነት የመሩ፣ዕውቀታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ያካፈሉ፣ የኪነ ጥበብ ወቴአትር መሥራቹ፣ የተዋጣላቸው ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ደራሲ እና ተርጓሚው፤ የታላላቆቹ ጠቢባን የነ ጋሽ ጸጋዬ፣ የገብረ ክርስቶስ፣ የጋሽ ስብሐት፣ የየኔታ አፈወርቅ … የልብ ወዳጅ፤ ኢትዮጵያ አገራቸውን ከልብ መውደዳቸውን እስከ ዕለተ ኅልፈታቸው በዘለቀ ፍቅር ያረጋገጡት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ዛሬ ተለዩን። ከልቡ የሠራ ሰው ኅልፈቱ የሥጋ እረፍቱ ቢኾንም፣ ጉድለቱን ግን አገር በምን እንደምትሞላው ቢያስቡት መልሱ ቅርብ አይደለም። ነፍስ ኄር የኔታ ታላቅ መምህር!›› በማለት ነው ጥልቅ ሃዘኑን የገለጸው።

በ2008 አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሲሠራ የነበረው ደረጄ ትዛዙ ደግሞ የተስፋዬን የሕይወት ታሪክ የሚዳስስ መጽሐፍ አዘጋጅቶ አጠናቋል ። መጸሐፉን ያሰናዳበትም ምክንያት ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዳም ‹‹በ2008 አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በምሠራበት ጊዜ ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። ወደዱት።በዚያው ተግባባን በሂደት በሥነ-ጹሑፉ እና በቴአትሩ እንዲሁም በመምህርነቱ ለአገራችን ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽዖ መሆኑን ስረዳ ማንነታቸውን መጽሐፍ እንደሚወጣ አመንኩ።ስጠይቃቸውም ደስ ብሏቸው ፈቀዱ። ጀመርኩት።›› ሲል ያስረዳል።

‹‹ታላቁ የጥበብ ባለሟል›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ ‹‹አሁን እያለቀ ነው።ጥቂት የሚስተካከሉ ነገሮች አሉ። ከሕልፈታቸው በኋላም የሚጨመር ምዕራፍ ይኖራል›› በማለት ደረጄ ይጠቁማል።

መጽሐፉ 12 ምዕራፎች እና 300 ገጾች ያሉት ሲሆን ስለ ተስፋዬ መረጃዎችን ከራሳቸው ጋር ባደረገው ተደጋጋሚ ቃለምልልሶች፣ ከመጽሐፎቻቸው፣ከጋዜጦች ከቴሌቪዥንና ራዲዮ፣የሥራ ባልደረቦቻቸውን፣ተማሪዎቻቸውን፣ቤተሰቦቻቸውን፣ጓደኞቻቸውን፣ቴአትር ቤቶችን ፣የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም መረጃዎችን በመስጠት ተባብረውኛል ሲልም አስታውቋል ።

ደረጄ ታላቁን የጥበብ ሠው ተስፋዬን ሞት ነጠቀበት እንጂ መጽሐፉ ታትሞ በ85ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ላይ ለማስመረቅ ታቅዶ ነበር።
ሌላው ከ1953 እስከ 2013 የተስፋዬን የ84ኛ ዓመት የልደት በዓልና ከ60 አመታት በላይ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ለአገራችን ያደረጉትን አበርክቶት ለመዘከር በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ አቢሲኒያ ባንክ ሃያት በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ የሚከፍተውን ቅርንጫፍ በሥማቸው ለመሰየም ገና በሕይወት እያሉ ቃል መግባቱን የሚታወስ ነው።
እንዲሁም መስከረም 17/2013 ተስፋዬ በሕይወት እያሉ ስለ ሠሯቸው ሥራዎች የጥበብ ቤተሰቦች ተገኝተው ምስክርነታቸው መስጠታቸውም የሚበረታታ ነገር እንደሆነ እና ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ የለፉ ሠዎችን በሕይት እያሉ ማመስገን እንዲሁም መዘከር መቀጠል የሚገባው ጉዳይ እንደሆንም መጠቆም ያሻል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣም የአንጋፋው የጥበብ ሠው ተስፋዬ ገሠሠ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ሕልፈተ ሕይወት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፤ለቤተሰቦቻው-፣ ለወዳጆቻው እና ለአክባሪ አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ትመኛለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com