ከፖለቲካ ቱማታ ወደ ነብስ ይማር!

Views: 210

ላለፉት ጥቂት ሳምንታት የብዙኀንን ቀልብ ሰቅዞ ይዞ የነበረው የፌደራሉ መንግሥት በሕወሓት ላይ ከወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ጋር በተያያዘ ነበር። ይሁንና ከሳምንታት በኋላ ሁሉንም የትግራይ ከተሞች በመያዝ መቀሌን መደምደሚያ በማድረግ የትግራይ ሕዝብም ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ላይ ይገኛል።

የተሰየመው ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራውን የጀመረ ሲሆን ሕዝቡ የታጠቀውን የጦር መሣሪያ በማስፈታት፣ ሰብኣዊ እርዳታ በማዳረስ፣ የመብራት እና ሥልክ አገልግሎት ወደ ነበረበት በመመለስ የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዲቀጥል ተደርጓል። ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መቀሌ በመሄድ ከከፍተኛ የጦር መሪዎች ጋር መነጋገራቸው እንዲሁም ኀሙስ፣ ታኅሣሥ 8 የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ28ኛ ጊዜ ከሦስት ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁ የመቀሌም ሆነ የክልሉ በአጠቃላይ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ ማሳያ ትዕምርት ናቸው የሚሉ ብዙዎች አሉ። ይሁንና የሕወሓት ቁንጮ አመራር የት ገቡ የሚለው ጥያቄ እስካሁን እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሏል።

የሕግ ማስከበሩ ዜና የተለመደ ተራ ወደ መሆን በተሸጋገረበት ወቅት በዚህ ሳምንት የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ሰሞነኛ የታላላቆች ሕልፈተ ዜና ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችም ሕይወታቸው ባለፉ አንጋፋ ግለሰቦች ምስል፣ ሥራዎች እና ትዝታ ተሟሙቆ ሰንበቷል።

የመጀመሪያው ዜና እረፍት የተሰማው በደርግ ዘመነ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ነው። ፍቅረሥላሴ የኢትዮጵያ አየር ኀይልን በመወከል ደርግን ካቋቀቋት መካከል ሲሆኑ በተለይ በታማኝነታቸው እና ሀቀኛነታቸው ሥማቸው በሠፊው ይነሳል። ‘ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል’ የሚል ይትባህል በተሰራፋበት ማኅበረሰብ፥ ፍቅረ ሥላሴ ኑሯቸው ከተራ ሕዝብ የተለየ እንዳልሆነ፣ በዘመነ ሥልጣናቸውም ሕዝብን ከማገልገል ውጪ ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው ሀብት እንዳላጋበሱ በተግባር እንዳስመሰከሩ ይነገራል። ለአብነትም የፍቅረ ሥላሴ እኅታቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሰል ቸርችረው ሕይወታቸውን ይገፉ እንደበር ይነገራል።

ፍቅረሥላሴ የኢሕአዴግ የመንግሥትነት መንበረ ሥልጣኑን መቆጣጠር ተከትሎ ባልደረቦቻቸው ከነበሩት ከፍተኛ የደርግ ሹማምንት ጋር ለኹለት ዐሥርታት በእስር ቤት የማቀቁ ሲሆን ከእስር ከተፈቱ በኋላም “እኛ እና አብዮቱ” በሚል ኹለት ቅጽ መጻሕፍት አበርክተዋል። በመጨረሻ ቀናት ከጎናቸው ነበርን የሚሉት አንዳንዶች በማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ላይ ፍቅረሥላሴ መንፈሳቸው ደስ ብሎት እንደነበረ ጽፈዋል። ለዚህም ምክንያት ተደርጎ እኒህ ውስጥ አዋቂዎች የጠቀሱት “አገር ገንጣይ”፣ “ጸረ ኢትዮጵያ” በማለት ሲታገሏቸው የነበሩት ወያኔዎች ቀድመዋቸው ወደ መቃብር መግባታቸውን በሕይወት እያሉ ለመታዘብ መቻላቸው መሆኑን አጋርተዋል።

ሌላው ከፍቅረሥላሴ ጋር የሚነሳውና በርካቶች ሲጠቅሱት የነበረው ጉዳይ የሰውየው ዘናጭነትን ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘም “አነጋገር እንደ ጓድ ሊቀመንበር፥ አለባበስ እንደ ጓድ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ” ይባል እንደነበር ብዙዎች አስታውሰዋል።

ኹለተኛው ዜና እረፍት የተሰነማው የአንጋፋው ሁለገብ የጥበብ ሰው የተስፋዬ ገሠሠ ነው። ተስፋዬ በተለየ ሥሙ የሚጠራው ከእነ ጸጋዬ ገብረመድኅን እና መንግሥቱ ለማ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ቴአትር ያዘመነ መሆኑ ነው። ዘርፈ ብዙ ባለሙያው ተስፋዬ የዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ፣ ተዋናይ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ዳይሬክተር፣ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ እና የቴአትር ቤቶች አስተዳዳሪ በመሆን አገልግሏል።

የበርካታ የጥበብ ትሩፋቶች ያበረከተው ተስፍዬ፥ በስተእርጅናው ሳይቀር ታታሪነቱን አስመስክሮ ያለፈ ለመሆኑ ብዙዎች በስተመጨረሻ ላይ ያቀረባቸውን ሥራዎች ለአብነት አስታውሰዋል። የታላቁን የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን ዳጎስ ያለ ግለ ታሪክ “Long Walk To Freedom” በመተርጎም እና “የመጨረሻ መጀመርታ” የሚል መጻሕፍትን ለተደራሲያን ማቅረባቸውን እንዲሁም በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ “ልኬት” የተሰኘ ፕሮግራም እንደነበራቸውም ተጠቅሷል።
ሌላው ዜና እረፍት የተሰማው የታዋቂ ጋዜጠኛ፣ ታሪክ አዋቂ፣ ደራሲ እና አንደበተ ርቱዕው እያሱ በካፋ ናቸው።

አንዳንዶች የፕሮፌሰር መስፍንን ወልደማሪያምን ጨምሮ ከሰሞኑ በሕይወት ያጣናቸውን አንጋፋዎቻችንን በተመለከተ ስጋት እንደገባቸው ጭምር ገልጸዋል፤ አገር ያለ እነዚህ እሙር ልኂቃን ወና መቅረቷ በእጅጉ አሳስቧቸው አዋቂ የእድሜ ባለጸጋ አያሳጣን ሲሉም ተመኝተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com