የጠቅላይ ሚንስትሩ ስንብት ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (ከ1938-2013)

Views: 528

በአገራችን በ1966 ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ፤ በሰኔ 21/ 1966 የተቋቋመው የክቡር ዘበኛ፣ የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊት እና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ የኮሚቴ አባል ነበሩ። ከአየር ኃይል አባልነት አንስተውም በኢትዮጵያ አብዮታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለ17 አመታት በዘለቀው የደርግ ዘመነ መንግሥት ውስጥ እስከ የኢትዮጵያ ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ደረጃም ደርሰዋል። ሻንበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ

ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ከአባታቸው ወግደረስ ወንድምተካሁና ከእናታቸው አበቤቴ አርጋው ሐምሌ 7 ቀን 1937 በአዲስ አበባ ከተማ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለዱ።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቀጨኔ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን የቄስ ትምህርት ቤት፣ በቁስቋም ትምህርት ቤት እንዲሁም በዳግማዊ ሚኒሊክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለው ያጠናቀቁ ሲሆን፤ አገራቸውን በውትድርና ሙያ ለማገልገል በነበራቸው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ሚያዚያ 8 ቀን 1954 ዝነኛውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠራዊት ተቀላቀሉ።

በአየር ኃይል ሠራዊቱ የቴክኒክ ትምህርት ቤት የተሰጣቸውን የአውሮፕላን ጦር መሣሪያና ኤሌክትሮኒክስ ትምህርት ለሰባት ወራት ተከታትለው ጥሩ ውጤት በማስመዝገባቸውም፤ በ1958 ለከፍተኛ የሙያ ሥልጠና ወደ አሜሪካ ተልከው አሪዞና በሚገኘው የአንድሪው የአየር ኃይል ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ተምረዋል። በተቋሙም በወቅቱ ዝነኛ በነበሩት F-5 ለተባሉት ተዋጊ ጄት አውሮፕላኖች ተስማሚ የሆነ የጦር መሣሪያና የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ሥልጠናን ለስድስት ወራት ያህል ተከታትለዋል።

ከዛም በማስከተል ፍቅረ ሥላሴ ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለስ በአየር ኃይል የዕጩ መኮንኖች ትምህርት ቤት የ6ኛ ኮርስ ተወዳዳሪ በመሆን ለሰባት ወራት ያህል የተሰጠውን ሥልጠና አጠናቀው በመቶ አለቅነት ማዕረግ ጥቅምት 30 ቀን 1961 ተመረቁ።

የየዛን ጊዜው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለትምህርት የነበረው መነሳሳት ከፍተኛ ነበርና ወጣቱን መቶ አለቃ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ ገብተው የከፍተኛ ትምህርትን እንዲከታተሉ እድሉ ቢያመቻችላቸውም ፍቅረ ሥላሴ ግን ፍላጎትና ዝንባሌያቸው ከሚወስዱት ትምህርት ጋር ባለመመጣጠኑ ኹለተኛ አመት ተማሪ ሳሉ ትምህርታቸውን በማቋረጥ በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያና በአስመራ ምድብ ውስጥ ተመድበው ማገልገላቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

‹‹ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ
ላገር ብልፅግና ለወገን መከታ….
ኢትዮጵያችን ትቅደም ብለን እንገስግስ
ለትውልድ እንዲተርፍ የያዝነው ጥንስስ
ሀ…ሁ ኢትዮጵያ ትቅደም
ኢትዮጵያ ትቅደም….››

የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ ሥርዓትን አስወግዶ ሥልጣን የጨበጠው የደርግ ሠራዊት የሥልጣን ጉዞው መጀመሪያ ላይ የወጣው፣ ‹‹ተነሳ ተራመድ›› የተሰኘው ዜማ የለውጡ ማቀጣጠያ፣ የመለዮ ለባሹን ሞራል መገንቢያና ማነሳሻ፣ በወኔ ወደ ፊት ማስዘመቻ የዘመኑ ልዩ መዝሙር እንደነበር ይታወሳል።
ታዲያ የተለያዩ ከፍተኛ የአየር ኃይል ሥልጠናዎችን በመውሰድ ወታደራዊ ስብዕናን በሚገባ የተላበሱት የወቅቱ መቶ አለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ሕዝባዊ ንቅናቄውን ተከትሎ በሰኔ 21 ቀን 1966 የተቋቋመው የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ደርግ፣ በ4ኛ ክፍለ ጦር ሲሰበሰብ አየር ኃይልን ወክለው ከተገኙት መኮንኖች ወስጥ አንዱ ሆኑ።

የደርግ ወታደራዊ መንግሥትም የመጨረሻውን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከዙፋናቸው ለማውረድ፤ መስከረም 2 ቀን 1967 በፖሊስ ሠራዊት ተወካዩ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ መሪነት ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በላከው ቡድን ውስጥም የአየር ኃይሉ መኮንን ፍቅረ ሥላሴ ተካተውበት ነበር።

የኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የሚል መጠሪያን ይዞ መንግሥት ሲሰየም በሂደት የሻምበልነት ማዕረግን ያገኙት ፍቅረ ሥላሴ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ውስጥ የመጀመርያው ኃላፊነታቸው የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ መምርያ ኃላፊነት ነበር። ጊዜያዊ አስተዳደሩም ወደ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በ1968 ሽግግር ከተደረገ በኋላ፣ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም (ማሌ) ትምህርት እንዲቀስሙ ወደ ሶቪየት ኅብረት ከተላኩ የደርግ አባላት መካከልም ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ይገኙበታል።

ከዛም በማስከተል በጥር 26 ቀን 1969 በደርግ ውስጥ የከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ አካል የነበረው የደርጉ የቋሚ ኮሚቴ አባልና የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ዋና ጸሐፊ በመሆን ከሊቀመንበሩ ቀጥሎ በአገሪቱ የስልጣን እርከን ላይ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቁ።

በ1972ም በአገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ድርጅቶች ሽኩቻና ጥልፍልፍ ከስሞ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) ሲቋቋም የኮሚሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ከመመስረታቸውም በላይ፤ በዛኑ አመት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ሲመሰረት የፓርቲው የፖለቲካ ቢሮ አባል በመሆን አገልግለዋል።

የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከ1967 እስከ 1979 ለ13 ዓመታት የጨበጠውን ሥልጣን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) መሥርቶ ሲያስረክብም፣ ከመስከረም 1 ቀን 1980 ጀምሮ በ‹‹ጤና›› ምክንያት ስራቸውን እስከ ለቀቁበት ጥቅምት ወር 1982 ድረስ የመጀመርያው የኢሕዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆንም ሠርተዋል።

በመጨረሻም በ1983 ወርኃ ግንቦት በኢሕአዴግ አማካይነት የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፣ በ1989 እሳቸውኒና ሌሎች 42 የደርግ አመራሮች በግድያ፣ በዘር ማጥፋት እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ ቀርቦባቸው በ2000 የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከሦስት ዓመታት በኋላም የሞት ቅጣታቸው በይቅርታ ተነስቶ ወደ ዕድሜ ልክ በመቀየሩ በ2003 ከእስር ተፈቱ።

ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ከኹለት አሥርተ አመታት የእስር ቆይታ በኋላ፤ በእስር ላይ በነበሩበት ወቅተ ያዘጋጇቸውን ‹‹እኛና አብዮቱ›› (2006)፣ እንዲሁም ‹‹እኔና አብዮቱ›› (2013) የተሰኙ መጻሕፍትን አሳትመው ለአንባቢያን አብቅተዋል።

በተጨማሪም በእስር ቤቶች ያሳለፉትን ሕይወትና ገጠመኞቻቸውን የሚመለከት ‹‹እኔና ስምንቱ እስር ቤቶች››፣ እንዲሁም በእሳቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ የተመሠረተውን ክስና የፍርድ ሒደቱን በተመለከተ የሚዳስሰው ‹‹እኛ እና ፍርድ ቤቱ›› መጻሕፍትም እንዳሏቸውና ወደፊትም ለማሳተም እቅዱ እንዳላቸው ‹‹እኛና አብዮቱ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረው እንደነበር ይታወሳል።

‹‹አለባበስ እንደ ወግደረስ›› የሚል ብሂልን በዘመነኛና ቄንጠኛ አለባበሳቸው ያተረፉት ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው፣ ታኅሳስ 3 ቀን 2013 በ75 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም ቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስና ሌሎች ትላልቅ የእምነት አባቶች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ቀደምት የደርግ ሠራዊት አባላትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ በ8፡30 ተፈፅሟል።

ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ የኹለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንደ ነበሩ በቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ላይ በቀረበው የሕይወት ታሪካቸው ተጠቅሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com