ለሕወሓት ጂምክሮው ሕግ ለብሔርና ለጎሳ ፌደራሊዝም ዘብ ቆመናል የግልገል ጁንታዎች ነጠላ ዜማ

Views: 270

የጂምክሮው ሕግ በታላቋ አሜሪካ ውስጥ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረና በዜጎች መሀከል የፊት ቀለምን መሰረት ያደረገ አድሎአዊ ስርዓትየገነባ ነበር። ይህ ሕገ መንግሥት ዛሬ በዴሞክራሲያዊ ሥልጣኔ ማማ ላይ ላለችው አሜሪካ ጥቁር ጠባሳን ለትውልድ ትቶ አልፏል። ጁሃር ሳዲቅ ኢትዮጵያን እየተጠቀመችበት ያለውን ሕገ መንግሥት ብሔርን መሰረት ያደረገ ሕገ መንግሥት ነውና እንደ የጂምክሮው ሕግ የከፋ ጥቁር ነጥብ ሳያመጣ በጊዜ ሊታረም የሚገባው የመንግሥት የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል ይለናል።

አንዳንዶች ፌደራሊዝም አይነኬ አድርገው ብቸኛ አማራጭም አድርገው ልክ እንደ ለሊትና ቀን አዝካሮች/ውዳሴዎች ሲያወድሱት ይገርመኛል። ይህ የሚስተዋለው በተለይ የቀድሞ የሕወሓት ኢህአደግ ስርዓት አጋፋሪዎች ባህል የነበረ ሲሆን አሁንም ብልፅግናዎች ተመሳሳይ ሥነልቦና ውርስ እንደወረሱ ተገንዝቤያለሁ ።

እኔ ከፌደራሊዝም ጋር ምንም ችግር የለብኝም ከአሃዳዊም ቢሆን ዋናው ነገር እነዚህ መንግሥት የሚገነባባቸው አስተሳሰቦች ለአገር ግንባታ ፣ለዴሞክራሲ ግንባታ ፣ለዜጎች አብሮ መኖር፣ለአገር እድገትና ብልፅግና(ፓርቲውን አይደለም)የትኛው መንግሥታዊ ስርዓት የበለጠ ጥሩ ነው/ ያመቻል የሚለው ብቻ ነው የኔ ኮንሰርን ።
ከዚህ አኳያ ስለፌደራሊዝም በሰፊው የምመጣበት ሲሆን ለጊዜው ግን የኔ ብቸኛው ተቃርኖ ኢትዮጵያ ከምትከተለው የብሔር/የጎሳ እና የቋንቋ ፌደራሊዝም ከዴሞክራሲ መርህ ጋር የማይጣጣም ስለሆነ ኢትዮጵያ በሕወሓት የዘረጋችው የዘውግ ፌደራሊዝም ለአገሪቱ ትልቅ ጋንግሪን ስለሆነ መወገድ አለበት የሚል እምነት አለኝ፣ ከዛ በፊት ግን ለሁሉም ችግር ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ስለሆነ ይህ ሕገመንግሥት በአሜሪካ በአንድወቅት ከነበረው ከመርዘኛ የጂምክሮው ሕግ ሁሉ የከፋበመሆኑ ኢትዮጵያ እንደአገር መቀጠል ካለባት መስተካከል ይኖርበታል ባይ ነኝ ።

አይነካም ለሚሉ ቁርአን/መጽሃፍ ቅዱስ አይደለምም ለማለት ወደድኩ ።ወደ ሕገ መንግሥቱ ክፋት ለመጓዝ የብሔርብሔረሰቦች ቀንን መንደርደሪያ በማድረግ በታንኳ አብረን እንቅዘፍ፣ ሕገመንግሥቱ ጂም ክሮው ስለው በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች ስላሉበት በዋነኝነትም የችግራችን መንስኤ ስለሆነ ነው እንደ ሕዝብ እንዳንቆም የተለያየን አድርጎን ሲያበቃ የተለያየን ሕዝቦች ለመሆናችን የተለያየ ሥነ ልቦና እንዳለንም በራሳችን አንደበት በአደባባይ የምንገልፀውም በዚሁ ሁለንተናዊነት በጎደለው ሕገመንግሥት የተነሳ ነው። ለዚሁም ሲባል ባለፈው ህዳር ወር 15ተኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተከብሮ አልፏል። ሌጋሲ መሆኑ ነው።

የእውነት የብሔሮች መብት በትክክል ተከብሯል? በየወቅቱ የሚነሱ ጥያቄዎች ብቻ በቂ ናቸው። ታዲያ ለማንና ለየትኛው ነው የብሔር ጥያቄው የተመለሰው ?…ሆድ ይፍጀው ቢባል ይሻላል። የዚህኛው የብሔሮች ቀን ኮቪድ በመሆኑ በተለያየ ቦታ ሲከወን ስለነበር የጠለያ የብሔር ፖለቲካ ተናጋሪዎችንም ሲናገሩ አድምጠናል።
አቤት!ግብዝነት ግን ትጠላላችሁ። ኢትዮጵያ ፌደራሊዝም እኩልነት ምናምን ወዘተ በሰፊው አድምጠናል በሌላ ቦታ ደግሞ ኢትዮጵያን ሲረግሙ አጀብ ይሰኛሉ ልክ አሳ ከወሃ ሲወጣ እንደሚሞተው፣ እነሱም ከዚህ ከብሔር ዘውገኝነት ከወጡ እንደሚሞቱ አይነት ሲሆን ይመለከቱታል ።

እውነት ነው የእኔ እንጂ በጋራ የሠራነው ምናለ ደግሞስ እኔ እንድንል እንጂ እኛእንድንልስ የሚያደርግ ምን አለን ? ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ሕዝቦችን አንድ የሚያደርግ ሳይሆን የሚነጥል መጥፎ አስተሳሰብ የተለወሰ ነውና እናም እንደተለመደው ዲስኩራቸው፣ የይስሙላ ፌደራሊዝማችን ዐይነካም ሕገመንግሥታችን ለኅብረብሔራዊ አንድነታችን ምናምን ነው።

ስታደምጡ አቤት ለውጥማ አለ ማለቶ አይቀርም ሆኖም መሬት ላይ ያለው ፌደራሊዝም የሚታወቅ ነው። የቲፎዞና የጉልበት መሆኑን ኮፒ ፔስት ግን ትጠላላችሁ። በመሰረቱ ህዳር29 የሕወሓቱ አፋኝ የጂምክሮው ሰነድ /ሕገ አራዊት የፀደቀበት ቀንነው ለዚህም ነው ከአምልኮ ባልተናነሰ ሁኔታ የሚያከብሩት እኔን የገረመኝ ሕወሓትን ሲረግሙ ውለው ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ቁስሉን ማከማቸው ነው።

ምናልባት ባለሥልጣናቱ ለሕገ መንግሥቱና ለብሔር ብሔረሰቦች የማንነት ፖለቲካ ሌጋሲ በማስቀጠሉ ረገድ ድርድር የለንም በሚል ሲያስተላልፉት የነበረው መሃላ ቀረርቶ ፉከራ ፅንፍ የረገጠ አካሄድ ስትሰሙ የሕወሓት ን ፖሊሲ እየተቹ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነው የፓርቲ ርእዮተአለም እንዲሁም የፓርቲ አላማ ማስፈፀሚያ ለሆነ ሕገመንግሥት አዛኝ ቅቤ አንጓች መሆን የሕወሓት ጂምክሮው ሕግ ሌጋሲ አስቀጣይ የመንፈስ አምላኪያን ግልገል ጁንታ ከመሆን በምን ይተናነስ ይሆን ?
በመጀመሪያ በቅጡና በአግባቡ ብሔር ብሔረሰቦች ያልተሳተፉበት ያልወሰኑበት ሕገ መንግሥት በምን መመዘኛስ ነው የሁሉም ሆኖ የሚቀርበው? በምን መመዘኛ ነው የአማራ ሕዝብ ያልወሰነበት ሕገ መንግት የጉራጌ ሕዝብ ያልተካተተበት የሶማሌ ሕዝብ ያልተሳተፈበት ሕገ መንግሥት የብሔሮች ሕገመንግሥት የሚባለው ? እንዴተስ ነው ሪስቶር ማድረጉ አንደራደርበትም ብሎ ብሔር ብሔረሰቦችን አከብራለሁ ማለት የሚቻለው ? ወይስየሌሎች ይሁንታ አስፈላጊ አይደለም ? የኢዮጵያ ሕገ መንግሥት/የሕወሓት ማኒፌስቶና የፌደራል መንግሥቱ ሕገመንግሥት ብቻነው።

በወቅቱ የፌደራል መንግሥቱ ሕወሓት ስለነበር አሁን ደግሞ የሕገመንግሥቱ ፈላጭ ቆራጭነት ወደ ኦሮሚያ ብልጥግና ፓርቲ እና አክቲቪስቶች ተዘዋውሯላ ።ለዚህም ነው ሕገመንግሥቱ በሽተኛ ነው በሽተኛ በሆነ ሕግ ደግሞ አገርና ሕዝብን ማከም መፈወስ አይቻልም ለማለት የምደፍረው/የምሞግተው ።

ለምሳሌ የአሜሪካ ሕገመንግሥት ውስጥ አንድ የሚገርም አረፍተነገርአለው ፣እሱም የአሜሪካ ሕገመንግሥት የፌደራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥት ብቻአይደለም የሁሉም (ከሃምሳበላይ የሆኑ ስቴቶች )የጋራ ሰነድ እንጂ ይላል። ምክንያቱም ሁሉም ሐሳብ አዋጥተውበታልና። አበው ሲተርቱ ተመካክረው የፈሱት ፈስ ….አይሸትም ማለት ምሳሌው ይሄው ነውና ።

ሕወሓት ግን የራሱን ከጂምክሮው በላይ መርዘኛ ሕግ ለማስቀመጥ በራሱ አምሳል ኦህዴድ ብአዴንና ደኢህዴን ጠፍጥፎ መሥራቱን አይዘነጋም ።እንግዲህ ይህንን ነው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕገመንግሥት እያሉ ዛሬም የሚያወሩብን።

በዚህ ርእስ ዙርያ ከአንድ ጓደኛዪ ጋር ስለ ሕወሓቱ ሰነድ ሕገ መንግሥት እያወራን እንዲህ አለኝ፣ ሕገ መንግሥቱ ላንስማማ ተስማምተናል ብለው የማሉበት ነው። በጋራ ለመቆም የወሰኑበት አይደለም ብሎ የገለፀበት አገላለፅ ገላጭ ይመስለኛል ።

ዛሬም ያሉ ሰዎች አንዴ ከኢትዮጵያ አንዴ ከመገንጠል ኹለት ልብ የሆነባቸው የትየለሌ ናቸው። እነዚህ ሕወሓት የማይሻሉ ናቸው ዛሬም ከአንደበታቸው እንደምንሰማው ከጋራ ማንነቱ በላይ ብሔርተኝነቱን ይፈልጉታል። ሕገ መንግሥቱ የቸራቸው ስጦታ ነውና። ለዚህ ግራየተጋባ አስተሳሰባቸው ደግሞ በዚህ ጨቋኝ የሕወሓት ጂምክሮው ብሔር ተኮር ሕገመንግሥት ሲደገፉ ይታያል ለመሆኑ ጂምክሮው ምን ዓይነትሕግ ነው ? ከኢትዮጵያው ሕገ መንግሥት ምን ያገናኛቸዋል ?ማለታችሁ አይቀሬ ነውና ወደዛው ልለፍ።

የጂምክሮው ሕግ በአሜሪካ ከ1870ዎቹ ጀምሮ በጂምክሮው ፀድቆ ለበርካታ አመታት ዜጎችን በማፈን በአሜሪካ ትልቅ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎችን የፈጠረ የእርኩሳኖቹ የነጭ ብሔርተኞች ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ጥርቅም ውጤት ነበር። ይህ ሕግ ዘርን መሰረት ያደረገ ስለነበር በአብዘሃኛው ጥቁር አሜሪካውያን ላይ ታሪክ የማየረሳው በደል አስቀምጦም ለማለፍ የቻለ ሕግ ነበር።

በዚህ ሕግ በርካታ ነጭ አሜሪካውያን ያፍራሉ። ምክንያቱም መርዘኛ ስለነበር የጂምክሮው ሕግ በአሜሪካውያን ታሪክ ውስጥ አሜሪካን የከፈለ ሕግ በመባል ነው የሚታወቀው። ምክንያቱም ሕጉ የሚታወቅበት አንድ መርህ ነበረው ፣እሱም << separate but equal >> የተለየ ሆኖም እኩል ናቸው፣ የሚል እርስ በርሱ የተጣረሰ። ተፍሲር ያለው አግላይ ሕግ ነበር ፈረንጆቹ racial segregation በማለት የሕጉን መሰረትይገልፁታል።

ዛሬ በዴሞክራሲ ማማ ላይ የምትገኘው አገረ አሜሪካ ለዘመናት በጥቁሮች ላይ የጭቆና ቀንበር አጥምዳ የነበረው በዚህ ሕግ ነበር። ታዲያ ይህ ሕግ በአብዛኛው በደቡብ አካባቢ በሚኖሩ ድሆች ላይ ነበር በአብዘሃኛው የተጫነው ነጮች ጥቁሮችን ለኛ እንዲያገለግሉን የሠጠን ጊፍቶች ናቸው ሙሉ ሰውነት መብት ምናምን ከተፈጥ ሮሕግ እንደመቃረን ይቆጥሩት ስለነበር እጅግ ከባድ የሆነ Right violation የመብት ገፈፋ ያካሂዱባቸው ነበር።

ጥቁሮች ከባርነት ነፃ ለማውጣት መንግሥታዊ ፖሊሲ ያረቀቀው የአሜሪካ ፕሬዝደንት አብራሃም ሊንኮን/Abraham Lincon ይህንን የመንግሥታቸው እቅድ ይፋ ባደርጉ ግዜ የሴኔቱ አባል የነበረው ጀፈርሰን ዴቪስ/jaferson Devis የፕሬዝደንቱን ቃላት በመቃወም ወደ ደቡቡ ክፍል በመግባት ራሱን የደቡብ ክፍለ ግዛት አስተዳዳሪነቱን አወጀ።

መጨረሻም ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርቷል ሆኖም የጀፈርሰን ዴቪስ ደቡብ ገብቶ የገጀረበት ምክንያት ጥቁሮች በፍፁም ነፃ ሊወጡ አይችሉም እነሱ የእኛ ናቸው አይነት አስተሳሰብ የያዘ ፈር የለቀቀች ሐሳብ ነበረችው፣ ግን አልተሳካለትም ።የጂም ክሮውሕግደቡብ አካባቢ የበለጠ ጉዳት ለማሳደር የቻለው ደቡብ አካባቢ ያሉት ጥቁሮች በእውቀትም በገንዘብም የነበራቸው ጠቅላላ ሁኔታ ኋላቀር የሠለጠኑ ስላልነበር ነው።

ሌሎች ከነዚህ የተሸለ ሁኔታ ስለነበራቸው በአንፃሩ የተሸለ ነገር ነበራቸው ። የጂም ክሮውሕግ ጥቁሮችን ከማኅበራዊ ከፖለቲካዊ እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ተሳትፎ መብት የሰው ልጅ ካለው ተፈጥሮ ከቸረው universal right እንኳ የሚያግድ ነበር።

ለምሳሌ ጥቁር ባህሉን እምነቱን መግለጽ አይችልም ፣በፈለገበት ቦታ ሰርቶ መብላት፣ መዘዋወር ፣ ምርጫ መምረጥ፣ አይችሉም ፣ሽንትቤት፣ት/ቤት፣ቤተመጽሐፍት ፣የመዝናኛ ቦታ፣የስፖርትቦታ፣የገበያ ስፍራ ፣የጤና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እና ጥቁር ከነጭ መጋባት ወዘተ ልዩነት የተደረገባቸው ቦታዎች ስለነበር የትኛውም ጥቁር ሕጉን ቢጥስ ለከፍተኛ ቅጣት ሲዳረግ ነጮቹ ቢጥሱ ግን ከትንሽ ጓጓታ ውጪ ከበድ ያለ ነገር ወፍ አልነበረባቸውም።

ታዲያ እነዚህ ሕጎች በሙሉ የነጮች የበላይነት በጥቁሮች ላይ ለማረጋገጥ ታስቦ በአክራሪ ነጮች የተደረገ ነበር። የአገሪቱም የሥልጣን መዋቅርም በነሱ የተያዘ ጥቁሮችደግሞ ተመልካች ተመሪ ነበሩ። በነ ማርቲን ሉተርስኪንግ ማልኮም ኤክስና ሮዛ ፓረከስ መሪነት በሚሊየኖች በሚቆጠሩ ጥቁሮች ባደረጉት ትግል ጥቁሮች ይህንን አፋኝ ሕግ ለመቀየር ለረዥም ግዜ የቆየ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈሉ ሲሆን በመጨረሻም ድል በማድረግ በ1968 Civil right act በመተካት የጂምክሮውሕግ ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዲቀርና የዛሬዋን አሜሪካ እውነተኛ ዜጎች መሆናቸው በሕግ እንዲረጋገጥ አድርገዋል ።

ከትላልቅ የድል ችቦዎች አንዱ የጂም ክሮውሕግ ከአሜሪካ በመወገድ ዕጣ ፈንታው ‹‹አሜሪካን እና አሜሪካውያንን የከፈለ ሕግ››የሚል ስም ተሰጥቶት ትውልድ እየረገመው እንዲኖር በአሜሪካ ታሪክ በዝገብ ውስጥ በቅሌት እንዲቀመጥ ማድረግ መቻላቸው ነው።

ታዲያ በአገረ አሜሪካ ሰፍኖ የነበረው የጂምክሮው ሕግ በአገራችን ሕወሓት ላለፉት 27 አመታትና ከዛ በላይ ካሰፈነው ብሔር ብሔረሰቦችን ከጨቆነበት የጭቆና ሰነድ ጋር በትልቁ ይመሳሰልብኛል። ምክንያቱም ሁለቱም ዘርና ብሔር እና የፖለቲካ የበላይነት ፈላጭቆራጭነት መሰረት አድርጎ የተጠነሰሱ በመሆናቸው እና ኹለቱም ሕዝቦችና አገርን የሚከፋፈሉ አስተሳሰብ ስብስብ በመሆናቸው ያመሳስላቸዋል።

የሕወሓቱ የሚለየው ለይስሙላም ቢሆን የዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌዎችን ማካተቱ ብቻ ነው ልዩነቱ። ተግባሩ የኢትዮፕያ ሕዝብ ይመስክር። ሕወሓት ያሰፈነው ሕግ/ያረቀቀው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብን በጎጥ በመንደር የከፋፈለበት ከመሆኑ ባሻገር በሕዝቦች መካከል የውሸት ትርክቶችን ጥላቻን በመፍጠር እንዳይስማሙ በማድረግ የጠላትነት ስእል ለመሳል በሰፊው ሰርቷል።

ከዛባሻገር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስት ሚሊየን በላይ የማይሆን ቁጥር ያለው ሕዝብ በአገሪቱ ሥልጣን ላይ ፍፁም አግላይ በሆነ መልኩ ፈላጭቆራጭ በመሆንም አንባገነናዊ ስርአቱን ተክሎ አገሪቱን በአንድ ብሔር የበላይነት እንድትመራ ያደረገ ፖሊሲ ነበር ተፈፃሚ ያደረገው።

ሲያደርግ ሥልጣን ላይ የቆየው ከወረዳ እስከ ቀበሌ እስከ ክፍለ ከተማ ዛሬስ መዋቅሩ በማን እንደተያዘ ግልፅ ነው። ከሁሉ በላይ በደቦና በድብቅ ያለማንም ተሳታፊነት የፃፉት ሕገ መንግሥት በመጠቀም በሥልጣን ላይ እንደ ፊርአውን/ፈርኦን ረዥም ግዜ ለመግዛት ሲልም አገሪቱን በብሔር እና በክልል ከፋፍሎ እንደ መስቀል/አረፋ ቅርጫ አድርጓት በል ያዝ ስትፈልግ ትገነጠላለህ ኢትዮጵያ እኛ እናፈርሳታለን ብለው ምለው ተነስተው ፅንፍ የረገጠ የብሔር ስነልቦና በመፍጠር ብሔራዊ ማንነቷ ፈተና ውስጥ እንዲወድቅ ሰርተዋል።

አገራዊ አንድነት መከባብር መተባበር ወዘተረፈ እሴቶቻችን ላይ ክፉኛ ተጫውቶባቸዋል ይሄ በሕገ መንግሥት ጭምር የተካተተ በመሆኑ ነው በሃይማኖት በማባላት በብሔር በማባላት በፖለቲካ ማባላት እንዲሁም ለሥልጣን ሲልም በርካቶችን በአስከፊ ሁኔታ ቶርች አድርጓል ፣አስሯል ፣ከአገር አባሯል፣ብዙዎችንም ገሏል……ይህ ሁሉ ሲሆን ሁሌም የወያኔው አብዮታዊ ዴሞክረሲ በላይ ስለነበር ንጉሥ አይከሰስ ነበር ማለት ይቻላል።

እኔም በትንሽዋ ዕድሜዪ በርካታ ጓዶቼ ያለምንም ጥፋት ሲታሰሩ ሲፈቱ ሲታሰሩ ሲፈቱ አይቻለሁ እና የሕወሓት ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያው ጂም ክሮውሕግብየዋለሁ። ምክንያቱም ከጭቆናውጪ አንድም ሰው በአግባቡ ተዳኝቶበት አያውቅም ነበርና ።

ይህ የሕወሓት የጂምክሮው ሕገመንግሥት ፍትህን እኩልነትን ከማስፈን የግለሰብ መብትን ከመስጠት/ከማክበር እንዲሁም ከዜግነት ይልቅ ለማይታየው የፅንፍ ብሔርተኛ በማስተዋወቅ አገሪቱን በአፈና መዋቅሩ ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ የከፋፈለ ሕግ ነው ማለት ይቻላል ።

አሜሪካውያን በከፋፈላቸው ሕግ የተነሳ ይሸማቀቃሉ የኛ ድኩማን ብሔርተኛ ባለሥልጣናትና ምሁራን ግን ዜጎች በብሔራቸውና አገሪቱ በተከተለችው ሕገመንግሥታዊ የብሔር ፖለቲካ ምክንያት ሲፈናቀሉ ሲገደሉ ሲገለሉ መብት ሲነፈጉ እርስ በርስ ሲሰዳደቡ አንድ ተራ የክልል ግልፍተኛ የፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ሲጋፋ ጣልቃ ሲገባ ወዘተ ችግሮች መፍትሄ ላልሰጠ አፋኝ ዘውጌው ለሆነው ለኢትዮጵያ ጂምክሮው ሕግ ደረታቸውን ነፍተው ይሟገቱለታል ።

ዘይገርም እኮ ነው። ስለዚህ አፋኙ የጂምክሮው ሕግን የሚስተካከለው የሕወሓት ሕገመንግሥት እና የዘውግ ፖለቲካ ሌጋሲ አስቀጣይ ነኝ ማለት ሌላ አምባገነናዊ ስርዓት እንሁን ከማለትና ግልገል ጁንታ ከመሆን አሳንሼ አላየውም። ምናልባት ይሄንን ኢትዮጳውያንና ኢትዮጵያን የከፋፈለ ሕገመንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምርጫው በኋላ ይዘው ያዘግማሉ ወይስ ታሪክ ያደርጉታል …….ወደፊት የሚታይ ይሆናልና እስከዛው ………ሰላማችሁ ይብዛ እያለኩ አሳርጋለሁ ።
በጁሃር ሳዲቅ (ጋዜጠኛ)colomunistjuhar@gimal.com
ኢትዮጵያ ትቅደም !!

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com