በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ዛሬ ማለዳ በንጹሓን ዜጎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዛሬ ታኅሳስ 14/2013 በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አዲስ ማለዳ ከወረዳው ኗሪዎች ከደረሳት መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ የሚገኙ ኗሪዎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች ከማለዳው 11 ስዓት ጀምሮ በአራት ማዕዘን ከበው ጥቃቱን እንደፈጸሙት ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ለጊዜው አልታወቀም፡፡ ጥቃት ደርሶባቸው እስካሁን በቡለን ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና ለማግኘት ከ20 በላይ ዜጎች መግባታቸውን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ካሉ ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡
በመተከል ዞን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ታኅሳስ 13/2013 ከአካባቢው ነዋሪዎች እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሲመክሩ እንደነበር የሚታወስ ነው። በውይይቱም ጠቅላይ ሚንስትሩ በተፈጠሩት ችግሮች ተሳተፉ ከክልል እስከ ፌደራል የሚገኙ አመራሮች ለሕግ እንደሚቀርቡም መናገራቸው አይዘነጋም።