መተከል – የዘመናችን አኬልዳማ!

Views: 98

ሰሞኑን የማኅበራዊም ትስስር መድረኮችም ሆኑ መደበኛው መገናኛ ብዙኀን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ትኩረታቸውን በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን የንጹሃን እልቂት በተመለከተ መረጃዎች ሲያቀብሉና ሐዘናቸውን በመግለጽ ተጠምደዋል። በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በርካቶች ጥልቅ ሐዘናቸውን ለመግለጽ ምስላቸውን በተለኮሰ ሻማ ወይም ሙሉ በሙሉ ጥቁር በማድረግ ስሜታቸውን አጋርተዋል።
ነገሩ እንደዚህ ነው! ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 በክልሉ ውስጥ በሚገኘው መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኀይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና ተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሲሆን ይህንኑም የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን በማግስቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አረጋግጧል።
ጥቃት የተፈጸመባት በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞ እና አማራ ተወላጆች ይኖሩባታል። በተጨማሪም ጨላቆ እና ዶሼ በተባሉ ቀበሌዎች ቤቶች መቃጠላቸውም እንዲሁም በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆኑም ዘገባዎች አመልክተዋል።
በጣም የሚያሳዝነው ድርጊቱ የተፈጸመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ክልሉን በመጎብኘትና ሽማግሌዎችን፣ የክልሉን የበታች ባለሥልጣናትና ካድሬዎችን አነጋግረው ክልሉና የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት የንጹሃንን እልቂት ለማስቆም የተቀናጀ ሥራ እንዲሠሩ አቅጣጫ አስቀምጠው በተመለሱ ማግስት መሆኑ ነው። ተራ ገጠመኝ በማያስብል ሁኔታ ከወራት በፊት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ የተመራ የልዑካን ቡድን ችግሩ ባለበት አካባቢ ጉብኝት አድርጎ፣ ይመለከታቸዋል የተባሉ ባለድርሻዎችን አነጋግሮ እና የጸጥታና ደህንነት ችግር እንዳይፈጠር ለጸጥታ አስከባሪ ኀይሎች መመሪያ ሰጥቶ በተመለሰ በቀናት ልዩነት የበርካቶች ንጹሃን ዜጎች ግድያ መፈጸሙና ንብረት መውደሙ ይታወሳል።
ከድርጊቱ መፈጸም በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ሐዘናቸውን ከመግለጽ ባሻገር በክልሉ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ለማስቀረት መንግሥታቸው በተለያየ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን አምነዋል። መንግሥት ችግሩን ከሥረ መሰረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኀይል እንዲሰማራ አደርጓልም ብለዋል። በዕለቱም መንግሥት የደርጊቱ ተሳታፊዎች ናቸው ያላቸው 42 ታጣቂዎች መደምሰሱን አስታውቋል፤ በሰፊውም ተዘግቧል።
በፊት በፊት መንግሥት የቤኔሻንጉል ጉሙዝ የጸጥታ ችግር ከሕወሓት የእጅ አዙር እንቅስቃሴ ጋር ያያይዝ የነበረ ሲሆን ሕወሓት ወደ ታሪክነት ከተለመጠ ማግሥት ጀምሮ ደግሞ የውጪ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት ነው ሲል ጣቱን ወደ ውጪ ጠቁሟል። በርግጥ ክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገኛ መሆኑ ለውጪ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት አመክኗዊነት ብዙዎች ይስማማሉ። ይሁንና የመንግሥት ለክልሉ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት ችግሩ ውስብስብ፣ መፍትሄውም ቀላል እንዳይሆን አድርጎታል ሲሉ ትችት አቅራቢዎች በዋናነት የፌደራል መንግሥቱን ቸልተኛነት አጽንዖት ይሰጣሉ፤ ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው በጊዜው መፍትሄ ያለመስጠት ውጤት መሆኑን በማከል!
በሌላ በኩል ደግሞ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የእኛ ነው በማለት ግድቡን ይዘው ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች የመኖራቸው ወሬ መናፈስ መጀመሩን ብዙዎችን አስገርሟል። በርግጥ እስካሁን ድረስ ይህንን መሰል እንቅስቃሴ እያደረኩ ነው በማለት ራሱን በይፋ የገለጠ ኀይል ባለመኖሩ ስለመረጃው እውነተኝነት ማረጋገጥ ባለመቻሉ ጥርጣሬው እንዲጎላ አድርጓል።
አንዳንዶች በበኩላቸው የችግሩን ሥረ መሰረት ከክልሉ ምስረታ ጋር በቀጥታ ያያይዙታል። ከቀድሞ ጎጃም እና ወለጋ ክፍላተ ሃገራት ተወጣጥቶ የተመሰረተው ቤኔሻንጉል ጉሙዝ፥ የተጠመደ ፈንጂ በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ መፈናዳዳት ጀመረ ሲሉ መከራከሪያቸውን አስቀምጠዋል። ሌሎች ደግሞ ነገሮች አጥቦ ከማየት የኢትዮጵያ የሰላምና ጸጥታ እጦትም ሆነ ህልውናዋን ፈተና ላይ የጣለው በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በመሆኑ ይህ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው የሚባለው እስካልተለወጠ ድረስ አሁን ቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ ክልል ሕዝብ በስጋት እንዲኖር፣ አገሪቱም በሰላም ማጣት ስትናጥ ትከራማለች ብለዋል፤ ችግሮቹ ተባብሰው ከቀጠሉ ደግሞ ኢትዮጵያ የመበታተን እጣ ሊገጥማት ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው ሰዎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
የሆነው ሆኖ በአጠቃላይ ቤኔሻንጉል በተለይ ደግሞ መተከል የደም መሬት ሆኖ እስከመቼ ድረስ ይቀጥላል የሚለው ብዙዎች ምላሽ ለማግኘት የሚፈልጉት ጥያቄ እንደሆነ ቀጥሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com