የትምህርት ቤቶች ዳግም መከፈት

Views: 440

የትምህርቱ ዘርፍ የተማረ ትውልድን በማፍራትና በተለያዩ ዘርፎች ችግር ፈቺ የሆነ ትውልድን ለመፍጠር ያለው ሚና ቀላል የሚባል እንዳለሆነ መናገር ይቻለል።
ከዚህ በተጨማሪም የተማሪዎች እንቀስቃሴ በራሱ አንዱ የአዲስ አበባ ድምቀት መሆኑን ለወትሮው ጭርታና ዝምታ የሚታይባቸው አካባቢዎች ዛሬ ላይ ምስክር ናቸው ማለት ይቻላል።

ቅድመ ነገር
የኮቪድ 19 ወረርሽ ወደ አገራችን ከገባ ድፍን አንድ ዓመት ሊያስቆጥር የቀሩት ሦስት ወራት ብቻ ናቸው። ታዲያ በዚህም ሳቢያ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር እንዲያስች በማለት በመንግሥት በኩል የተለያዩ ተቋማት በአፋጣ እንዲዘጉ መደረጋቸውም የሚታወስ ሲሆን ከነዚህም መካከል የትምህርት ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው።

በኢትዮጵያ 26 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትህርት ገበታቸው እንዲርቁም አስገድድዋቿል።

የትምህር ቤቶች መከፈት ዜና
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 12/2013 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉደዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጤና ሚኒስቴር አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርትና ምክረ ሐሳብ ላይ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ በዝርዝር ተመልክቶ አጽድቆታል።
ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መከላከልን መሰረት በማድረግ ክልከላ የተጣለባቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲፈቀዱ እና ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ሲልም ውሳኔ አሳልፏል።

ይህንን ተከትሎም በመማር መስተማር በኩል ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ከለዚህም መሀከል በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የሚታየው ቸልተኝነት የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳደር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ትምህርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲዩት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን መደበኛ ትምህርት በማስቀጠል ሂደት ላይ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሲያደርጉት በነበረው ምክክር ላይ የሃይማኖት አባቶች በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የመንግሥትና የሕዝብ ቸልተኝነት እያታየ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ቸልተኝነት የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ስጋታቸውንም ገልጸው መንግሥት ኮሮናን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎች እንዲተገበሩ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ የጠየቁት የሃይማኖት አባቶቹ፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ኅብረተሰቡን በማንቃት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገና ትምህርት ሳይጀመር ነበር አጋርነታቸውን ያሳዩት።

የስምንተኛ ክፍል እና የ12 ተኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ አድጓል። የስምነንተኛ ክፍል ተማሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት ብሔራዊ ፈተናዎችንም ወስደዋል።

በመቀጠልም መንግሥትም ትምህርት ለማስጀመር በቂ ሥራዎችን እንደተሠራ በመግለጽ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መስከረም 30/2013 ይጀመራል ብሎ ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ከ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ውጪ በተቀሩን ክፍሎች ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በኮቪድ-19 የቀውስ ጊዜ የትምህርት አመራርና አስተዳደር ስትራቴጂ እቅድ ላይ የተቀመጡ ስታንዳርዶችን ሟሟላት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አስፈላጊ ዝግጅቶች በተሟላ ደረጃ እስኪጠናቀቁ ድረስ በከተማዋ ለመጀመር የታቀደው የገጽ ለገጽ ትምህርት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ቢሮው ማስታወቁም አይዘነጋም።

በአዲስ አበባ ከተማ የ2013 የትምህርት ዘመን ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የገጽ ለገጽ ትምህምርት ኅዳር 28/2013 ተጀምሯል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መካኒሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት አስጀምረዋል ።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ልዩ ጥንቃቄ ለማድረግ ከ2 ሺሕ 300 በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እና 118 የመመገቢያ አዳራሾች መገንባቱን ገልጸዋል ።

አጠቃላይ የመማር ማስተማሩ ሂደት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በጸዳ መንገድ እንዲካሄድ ተማሪዎች መምህራን እና ወላጆች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው የትምህርት ሂደቱ በይፋ አስጀምረዋል ።

ምክትል ከንቲባ አዳነች በትምህርት ማስጀመር መርሐግብር ላይ ለተማሪዎች የተዘጋጀ ዩኒፎርም ፣የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ፤ለመምህራን ደግሞ የጋውን ስጦታ አበርክተዋል ።

በዕለቱም የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ዘላለም ሙላቱ ከዛሬ ጀምሮ ለተጀመረው ከአምስተኛ ክፍል በላይ ትምህርት ደግሞ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ25 ያልበለጡ ተማሪዎች እንዲማሩ ተደርጎ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ው መሰራቱን ገልጸው የትምህርት አሰጣጡም በኹለት ፈረቃ ሆኖ ሰኞ፣ ረቡዕ ፣ አርብ እና ማክሰኞ ፣ ሀሙስ እና ቅዳሜ እንደሚሆንም ተናግረዋል ።

በትምህርት ማስጀመር ወቅት ከዘጠኝ ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ለተመለሱት ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመምህራን የተሰጠ ሲሆን፣ የእጅ መታጠብ ሂደትን ጨምሮ የፊት መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እና ርቀትን መጠበቅ ግዴታ ስለመሆኑም ግልፅ ተደርጎላቸዋል።
ተማሪዎችም በትምህርት ቤት ውስጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የተሳካ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

የተሰሩ መልካም ጅማሮዎች
በአዲስ አበባ ትምህርት መጀመሩን ተከትሎም አዲስ ማለዳ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እና በግል ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው የገጽ ለገጽ ትምህርት ምን ይመስላል ስትል ተማሪዎችን፣ወላጆችን እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበርን አነጋግራለች።

አሸናፊ ሸጉ እና እሌኒ ደሜ በጋብቻ ስምንት ዓመታትን ያሳለፉ ሲሆን በነዚህ ዓመታት ውስጥ አንድ ሴት ልጅ እና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል። አሸናፊ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሠራ ሲሆን እሌኒ ደግሞ የራሷን የግል ሥራዎች ለመሥራ ት ብትሞክርም በአሁን ወቅት የቤት እመቤት ሆናለች።
ጥንዶቹ ከትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር በተያያዘ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ ትምህርት መከፈቱ በተለይም ልጆቻው ከጭንቀት እንዲላቀቁ እንደረዳቸው ይናገራሉ። ምንም እንኳን በአሁን ወቅት ወደ ትምሕርት ገበታዋ የተመለሰቸው ሴት ልጃቸው ባአምላክ አሸናፊ ስትሆን ፤እሷም ቢሆን ትምህርት ውላ መመለሷ እንዳስደሰታት ትናገራለች ። ታናሽ ወንድሟ ገና የቅድመ መደበኛ ተማሪ በመሆኑ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ አለመሆንኑም ጥንዶቹ ያስረዳሉ።

ከዚህ ሐሳብ ጋር በተያያዘም አሸናፊ ሲናገርም ትምህርት መከፈቱ ጥሩ እንደሆነ በመግለጽ እኔም ልጄ ወደ ምትማርበት ትምህርት ቤት ያለውን ነገር ለማየት ሄጄ ነበር። ተማሪዎች የፊት መሸፈኛ ጭምብል አድርገው ነው የሚገቡት ገና ከመግቢያው ላይ ያለ ቁጥጥር ነው ሙቀታቸውን ተለክተው ነው የሚገቡት በማለት ያስረዳል።
በአንድ ክፍል ውስጥም 23 ተማሪዎች ሆነው የሚማሩ እንደሆነ የሚገልጸው አሸናፊ የሚቀመጡትም ተራርቀው እንደሆነና ከንክኪ እንዲርቁ ተደርገው መሆኑንም በመልካም ጎን ያነሳል።

ሌሎቹ ጥንዶች ደግሞ ለምለም ተስፋዬ እና ሳሙኤል በቀለ ይባለሉ። እነዚህ ጥንዶችም በጋብቻ 13 ዓመታተን አሳልፈዋል።በነዚህ ዓመታት ውስጥም ኹለት ሴት አንድ ወንድ ልጆችን ማፍራት ችለዋል።

ሳሙኤል ለአዲስ ማለዳ ሲናገር ኹለቱም ሴቶች ልጆቹን የሚያስተምረው በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሆነ በመግለጽ ትምህርት እንደሚጀመር ዜና ስንሰማ ግራ ገብቶን ነበር ገና ወወርሽኙ ያልጠፋ በመሆኑ እንዴት ነው ደፍረን የምልካቸው በማለት የመጀመሪያውን ቀን ትምህርት ቤት ሳንልካቸው ቀርተናል ሲልም ያስረዳል።

ለምለም በበኩሏ፤ በርግጥ ልጆቻን በጣም ሕጻናት የሚባሉ አይደለም አንደኛዋ ልጃችን 11 ዓመቷ ሲሆን ወደ አምስተኛ ክፍል ተዘዋውራለች ኹለተኛዋ ልጃችን ደግሞ ስምንት ዓመቷ ሲሆን ወደ ኹለተኛ ክፍልም ተዘዋውራለች እንደ አጋጣሚም ኹለቱም አንድ ፈረቃ ናቸው ትምህርት ቤቱም ከመኖሪያ ቤታችን ብዙም ስለማይርቅ በእግራቸው መሄዳቸውም እፎይታን ሰጥቶናል ከምንም በላይ ደግሞ ትምህርት ቤት ደርሰው መምጣታቸውም ስላስደሰታቸው እኛንም ደስ ብሎናል ትለለች።
በትምህርት ቤቶች የሚደረጉ ቁጥጥሮችም ቢሆን ጥሩ ነው አሁን እኛ ልልጆቻን በተርም የከፈልነው አንድ ሺሕ ብር ነው። በተጨማሪም ደግሞ ለመመገቢያ ተብለን ሦስት መቶ ብር እንድናዋጣ ተደርገናል ይህንን ማድረጋቸውም የሚበረታታ ነው ትላለች።

ሌላው ትምህርት ቤቶች ጋር መከፈት በተያያዘ ሐሳቧን የነገረችን ኑሃሚን መኮንን ስትሆን የ14 ዓመት ታዳጊ ናት፤ ኑሃሚን የምትማረው በመንግሥት ትምህርት ቤት ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንትም የ8ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዳች።

ስላሳለፈቸው ወራት ስትናገርም በጣም የሚጨንቅ ነበር ከዘሬ ነገ ትምህርት ይከፈታል ብሎ ማሰቡ፤አሁን የእኛ ዕጣ ፈንታስ ምንድ ነው? እያልኩ አስብ ነበር ።ይሁን እንጂወደ ትምህርት ቤት ተመልሰን ክለሳ ተደርጎልን መፈተናችንም አሁን ተስፋ እንድናደርግ ረድቶናል በማለት ትናገገራለች።
በአጠቃላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሠዎች እንደገለቱት ከሆነም ተማሪዎች የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ፣ሳሙናና ሳታይዘር ይዘው እንዲመጡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ተጨማሪ የደንብ ልብስ(ዩኒፎርም) እንዲያዘጋጁ ማድረጋቸውም አስመስግኗቸዋል።

ሊሻሻሉ የሚገቡ ነገሮች
ከትምህርት ቤቶች ጋር መከፈቱን ተያይዞ በመንግሥት፣በትምህርት ቤቶች፣በወላጆችና በተማሪዎች ጭምር የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች መኖራቸው የሚበረታቱ እንዳሉ ሆነው በግልጽ የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

ከታዘበቻው ትዝብቶች መካከል ተማረዎች በመንገድ ላይ የፊት መሸፈኛ ጭምብል አርገው ያለመታየትና ማስካቸውን በአግባቡ ያለመያዝ፣ተራርቀው ያለመሄድ፣መጨባበጥ፣ለበሽታው በቂ ትኩረት ያለመሥት እና በትራንስፖርት ውሰጥም ተማሪዎች ከአቅም በላይ ተጭነው ተመልክታለች።
በተያያዘም ወረርሽኙ ገና በአገራችን ብሎም በዓለማችን ያልጠፋ በመሆኑ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ከእለት እለት እየቀነሱ ስለመምጣታቸውንም የጤና ሚኒስቴር ታህሳስ 01/2013 በሰጠው መግለጫ ላይ አመላክቷል። በመሆኑም በኢትዮጵያ በኮቪድ የታመሙ ጽኑ ሕሙማን ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን እና ተቋማትም ቢሆን የመቀበል አቅማቸው ከአቅም በላይ እንደሆነ መናገሩን አዲስ ማለዳ ዘግባለች።

እንዲሁም በአዲስ አበባ የፊት መሸፈኛ ጭምብል(የፊት ጭምብል) የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከ72 በመቶ ወደ 52 በመቶ ማሽቆልቆሉንም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።

ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ካጋሩት መሀከል አሸናፊ መስተካከል ስላባቸው ነገሮች ሲያስዳም ተማሪዎች ወደ ትምህርተ ቤታቸው ሲገቡ በር ላይ ሙቀታቸውን የሚለኩ መሆኑ የሚበረታታ ሲሆን የሚለኩት ባለሙያዎች ግን የጤና ባለሙያዎች ባለመሆናቸው ነገሩ አጠራጣሪ ስለሚመስል ይህ ነገር እንዴት ነው የሚስብል ጥያቄም ያስነሳል ይላል።

አሸናፊ ያክልና ሌላው ያየፊት መሸፈኛ ጭምብል ጉዳይ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ሲሆን መንግሥት ለግል ትምህርት ቤቶች የፊት መሸፈኛ ጭምብል በነጻ እንሚሰጥ ቃል የገባ ቢሆንም እስካሁን ምንም የተሰጠ ነገር የለም ይላል።

ገበያ ላይ ያሉት የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ቢሆኑም መንግሥት በቂ ቁጥጥር የሚደርግበት አይመስልም፤ ለዚህም አንዱ ማሳያ ሲናገር እንዲህ ይላል እኔ ለልጄ ሰርጂካል የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚባለውን ነው የምገዛው እሱም ቢሆን ቶሎ የሚበጠስ ነው በማለት ይናገራል። ወጪውም ቢሆን ቀላል አይደለም የሚለው አሸናፊ የጨርቅ የፊት መሸፈኛ ጭምብል ደግሞ የሚያፍን በመሆኑ መንግሥት ጥራቱም ላይ ይሁን ዋጋው ላይ ሊያስብበት ይገባል ይላል።
እሌኒ ደግሞ ስትናገር፤መምህራን እና ተማሪዎች ንክኪ ለማስቀረት ሲሉ የቤት ሥራ አይሰጣቸውም እስካሁንም ምንም የቤት ሥራ ተሠጥቷቸው አልተመለከትኩም በማለት ያስረዳች ሲሆን ይህም ቢሆን መስተካከል ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ነው የጠቆመችው።

ኑሃሚም በበኩሏ ገና እኛ ወደ ትምህርት ስንገባ ጥንቃቄ እንድናደር በመምራኖቻችን በኩል ዘወትር ይነገረን ነበር በኋላ ላይግን መቀዛቀዝ እንደነበርም ታስታውሳልች።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ደግሞ እስካሁን ትምህርት ቤቶች ለመከፈት የዘገዩበት ምክንያት የኮቪድን ፕሮቶኮል ለሟሟላት ታልሞ እንደሆነ የቢሮው የኮሙሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አበበ ቸርነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ አበበ ገለጻ ከሆነም ፕሮተሎኮሉ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መሀከል በአንድ ክፍል ውስጥ 25 ተማሪዎች ብቻ እንዲሆኑ እና በአንድ ወንበር ላይ ብቻ እንቂቀመጡ የሚያዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

እንዲውም የውሃ አቅርቦትምም በተመለከተ ከሚመለከታቸው ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለን በማለት የገለጹት አበበ ከግንዛቤ ጋር በተያያዘም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጠዋት ጠዋት የተማሪዎች ሰልፍ ላይ በሚኒ ሚዲያ አማካኝነት ኮቪድ ለመከላከል መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችም ለተማሪዎች እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻችንም ላይ የተለያዩ የግንዛቤ ሥራዎችን እየሠራን ነው ሰሉ አበበ ገልጸዋል።

በርግጥ ይላሉ አበበ፤ ተማሪዎች ለዘጠኝ ወራት ያህል ከትምህርት ገበታቸው የራቁ በመሆናቸውም የግንዛቤ ሥራ እየተሠራም ይገኛል ሲሉ ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አበራ ጣሰው በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ ከትምርት ቤቶች ዳግም መከፈት ጋር በተያያዘ ተማሪዎች የሚማሩበትን ሁኔታ የኮቪድ ፕሮሎቶኮል በሚያዘው መሠረት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ወላለጆች የልጆቻውን ሁኔታ በመጠየቅ የቤት ሥራም የማይሰጡ ትምህርተ ቤቶች ካሉ ወላጆች ይህን እንዲያስተካልሉ ለትምህርተ ቤቶቹ ሊነግሯቸው ይገባል ሲሉም ተናረዋል።

አበራ አክለውም ተማሪዎች ከዚህ ቀደም የነበሩበትን የትምህርት ሁኔታ ረስተዋል ብለው ደፍሮ መናገር ይቻላል ያሉ ሲሆን ለዚህም ወላጆች ሥራውን ለትምህርት ቤቶች ብቻ አሳልፈው ሳይሰለቹ በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉም አክለዋል።

በትምህርት ቤቶች ላይ እየተደረጉ ያሉ ጥንቃቄች ተስፋ የሚሰጡ እንደሆነ የገለጹት አበራ፤ ተማሪዎች ከኮቪድ 19 ራሳቸውን መከላከል የሚችሉት በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በአካባቢቸው በሌሎችም ቦታዎች ላይ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፍለጋል ሲሉመ አሳስበዋል።

በመንገሥት በኩል ለግል እና ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንደሚሰጥ ቃል የገባ ቢሆንም እስካሁን ለአንድም የግል ትምህርት ቤት የደረሰ የፊት መሸፈኛ ጭምብል የለም ብለዋል።

እስካሁንም ወላጆች በራሳቸው እየገዙ ነው ያሉት አበራ በአዲስ አበባ ላይ የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያርጉ ሰዎች መቀነስ አንድም ከገንዘብ አቅም አንድም በቸልተኝነት ሊሆን ስለሚችል መንግሥት ሊያስበብት ይገባል ሲሉ ነው ያስረዱት።
በአጠቃላይ ግን አዲስ ማለዳ ከነጋገረቻቸው ሰዎች እና ከታዘበቸው ነገር በመነሳት ትምህርተ ቤቶች ከሥጋት ነጻ ሳይወጡ ዳግም መከፈታቸው ለተማሪዎች ሥነ ልቦናም ቢሆን ይበል የሚሰኝ እና የሚበረታታ ጉዳይ ነው።

በመንግሥትም ይሁን በግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ፣የሙቀት መጠናቸው እንዲለካ መደረጉ ሳኒታይዘር እና ሳሙና እንዲመጡ፣መመገቢያ ቦታዎችን እንዲገነቡ ማድረጉም የሚያስመሰግነው ጉዳይ ሲሆን በመንገድ ላይም ይሁን በክፍል ውስጥ የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያወልቁ ተማሪዎች አሉና አሁንም ቢሆን የቁጥጥር ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል።
ሌላው ደግሞ ይህ ጉዳይ የትምህርት ቤቶች እና የመንግሥት ሥራ ብቻ በለመሆኑ ሁሉም ሰው የራሱን ድርሻ መወጣትም አስፈላጊ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com