አዋሽ 90.7 ኤፍ ኤም የማን ነው?

Views: 924

በኢትዮጵያ ካሉት የመገናኛ ብዙኃን ውስንነት የተነሳ በአየር ላይ ያሉትን አንድ ኹለት ብሎ መቁጠር ቢታሰብ ለቁጥር አዳጋች አይሆኑም። ለረጅም ዓመታት በአንድ ለእናቱ የኢትዮጵያ ራዲዮ ብቻ ሕዝብን ሲደረስ ተቆይቷል ። ይሁን እንጂ በኹለት አስርት ዓመታት ወዲህ አማራጭ የሬዲዮ ጣቢያዎች ወደ ሕዝብ መድረስ ጀምረዋል። ከጥቂቶቹ የሬዲዮ ጣቢያዎች ውስጥም ቀድሞው ዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም እና የአሁኑ አዋሽ ኤፍ ኤም ይገኝበታል።

በርካታ ውዝግቦች ሲነሱበት የከረመው አዋሽ 90.7 ኤፍ ኤም ከመጀመሪያዎቹ የጣቢያው ባለንብረቶች ሚሚ ስብሀቱ እና ባለቤታቸው ዘሪሁን ተሾመ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሌላ ግለሰብ ለማዛወር እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። በዚህ ሒደት ላይም ታዲያ የቀድሞው አክቲቪስት እና የአሁኑ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል የሆነው እና በማረሚያቤት ዪገኘው ጃዋር መሐመድ ጣቢያውን ገዝቶታል ፤ አዋሽ ኤፍ ኤም 90.7 በጃዋር ንበረትነት ነው የሚተዳደረው በሚልም በሕብረተሰቡ ዘንድ እየተስተጋባ ይገኛል። እነዚህን እና መሰል ጉዳዮች ለሕብረተሰበቩ ግልጽ ይሆኑ ዘንድ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ አዋሽ ኤፍኤምን በከፍተኛ ደርሻ (በባለቤትነት) ከሚመራው ድርጅት ጋር ቆይታ አድርጓል ። የአዋሽ ኤፍኤም ዋና ስራ አስኪያጅ ብሩክ ግዛቸውን በመወከል በሽር ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በአዋሽ ኤፍ ኤም 90.7ን በሚመለከት በሕብረተሰቡ ዘንድ የተዛቡ መረጃዎች እና ግልጽ ያልሆኑ እውቀቶች ሲንሸራሸሩ ቆይተዋል። በተለይም ደግሞ ከጣቢያው ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ብዥታ ተፈጥሯል። ይህን በሚመለከት እስኪ ግልጽ ያድርጉልን።
ወደ አዋሽ ኤፍ ኤም እንዴት እንደገባን ነግሬህ ልጀምርልህ። በመጀመሪያ አዋሽ ኤፍ ኤም ይሸጣል የሚባል ወሬ ነበረ። በእርግጥ ሙሉ በሙሉ አይሸጥም ነገር ግን አክሲዮን ለመግዛት ነው ነው ሊሆን የሚችለው። ከዛም ሔደን ዘሪሁንን ነው ያናገርነው የሚሚ ስብሀቱን ባለቤት። ይህ ጣቢያ ወይም አዋሽ ለናሁ ቴሌቪዥን ተሸጦ ነበር። ሙሉ በሙሉ ተሸጦ የናሁ ቴሌቪዥን ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያህል ቀብድ ከፍለው ነበር። ከዛ በኋላ ግን በአከፋፈልም ይሁን ወይም በሌላ ብቻ ግን የፍርድ ቤት ጉዳይ ተጀምሮ ነበር፤ ተካሰው ነበር።

በዛ መሐል ላይ እነ ዘሪሁን ለመንግስት የሚከፍሉትም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ገንዘብ ስላስፈለጋቸው መሸጥ ፈለጉ። ያው መሸጥ ሲባል በሙሉ መሸጥ ሳይሆን የአክሲዮን ድርሻን ብዙ እጁን ወደ ሌላ ማስተላለፍ ነበር የፈለጉት። ይህም ደግሞ ያለባቸውን ዕዳ ለመክፈል ገንዘብ ስላስፈለጋቸው ነው። በዚህም ወቅት እኛም ሔደን አናገርናቸው የፍርድ ቤቱም ጉዳይ በግልግል ዳኛ እንደሚጨርሱ ታወቀ። እኛም ስናጣራ አንደኛ የግልግል ዳኛጉዳዮን አየን እንዲሁም የገቢዎችም እዳ ነበር የገቢዎችንም እዳ አየን። ቀጥሎ ዋጋ ድርድር ጉዳይ ነበር ከእኛም ጋር ዋጋ ድርድሩ ተስማማን፤ የሆነው ይኸው ነው አዋሽም ወደ እኛ ንብረት ተዘዋወረ ማለት ነው።
ጣቢያውን ገዝተን ሥራ ከጀመርን በኋላም እንደዳንድ ወሬዎች ይናፈሱ ነበር በተለይም ደግሞ ጣቢያው የጃዋር መሐመድ ነው ይባልም ነበር። እኛ ግን ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም። ነገር ግን እዚህ ያሉ ሰራተኞችን ስንጠይቅ ጀዋር መሐመድ አንድ ቀን በጣቢያው ዋና መስሪ ቤት ተገኝቶ መጎብኘቱን ነግረውናል። ከዛም በተቸማሪ ደግሞ ጣቢያው ጃዋር መሐመድ በአዋሽ ኤፍ ኤም 90.7 የአየር ሰዓት በመውሰድ ሊሰራ እንደሆነ እና በተደጋጋሚም በጣቢያው ማስታወቂያ በመነገሩ ሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ ገብቷል እንጂ ጀዋር አዚህ ጣቢያ ላይ ምንም አይነት ድርሻ ሆነ ግንኙነት የለውም።

አሁን ለምሳሌ እኔ አላውቀውም፤ ከእኛ ውስጥም ማንም የሚያውቀው የለም ግንኙነትም የለውም በምንምም አንገናኝም። ጃዋር የሚደገፍም ወይም የማትደግፈውም አቋም ሊኖር ይችላል ወይም ላይኖርም ይችላል። ነገር ግን ከአዋሽ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም። እርሱንም አናውቀውም ነገር ግን ሰው በሌላ መንገድ ጣቢያውን ስለተረዳው በጣም ጎድቶናል።

በጣቢያው ጃዋር መሐመድ አየር ሰዓት ገዝቶም እንደነበር መረጃዎች ሲወጡ ነበር እንዳሉኝም ማስታወቂያም ሲነገር ነበር
በእርግጥ በቀደመው ጊዜ እንዳልኩት ጃዋር በጣቢያው ተገኝቶ እና ጎብኝቶ እንደሄደ ሰራተኞች ነገረውናል። በወቅቱም ጃዋር አየር ሰዓት በመግዛት በጣቢያው በአማረኛ እና በኦሮምኛ ዝግጅቶችን ለማስተላለፍ መወሰኑንም በወቅቱ ለነበሩ ሰዎች ተናገረ እና በወቅቱም ማስታወቂያ ተነገረ እንጂ ምንም አይነት አየር ሰዓትም ሆነ ዝግጅት በጣቢያው አላስተላለፈም። ጃዋር በወቅቱ በራሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኦኤም ኤን ተናግሯል አሉ እንደገና በዚህም ጣቢያ ደግሞ ለአንድ ወር ያህል ማስታወቂያ አስነግረናል ብለዋልም በወቅቱ። ነገር ግን ከዛ ቀን ወዲህ መጥቶም አላየውም የተጀመረም ነገር የለም።

የጣቢያው ባለቤትነት ጉዳይ ለሕዝብ ግልጽ ባለመደረጉ ምክንያት በርካታ ጉዳዮች እንደተከሰቱ እና በጣቢያውም ላይ አስተዳደራዊ ጉዳት እስከማድረስም የዘለቀ እንደነበር መረጃዎች አሉን በዚህ ጉዳይስ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ ወደዚህ ስንመጣ ያጋጠመን ችግር አንዱ ‹‹ዛሚ›› የሚለው ስያሜ ነው። ዛሚ የሚለውን ስያሜ ሕብረተሰቡ አልፈለገውም። ሬዲዮ ጣቢያው አዋሽ ነው ሚለው ነገር ግን ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበሩ ግን ስያሜው ዛሚ ነው የሚለው። ወይም ‹‹ዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽን›› ነበር የሚለው። በዚህም ምክንያት ታዲ ስፖንሰሮችን አግኝተን ልንፈራረም ጫፍ ላይ ደርሰን ዛሚ የሚለውን ሲያዩ በቃ እንደውላለን ብለው ይልኩናል ወይም ይመልሱናል። አስፈላጊውን ሕጋዊ መስመር ተከትሎም አሁን ስያሜው ከዛሚ ወደ አዋሽ ፐብሊክ ኮኔክሽን ተቀይሯል። ከዚህ በኋላ ዛሚ የሚባል የለም ምንግስትም ሚያውቀው ‹‹አዋሽ ፐብሊክ ኮኔክሽን›› በሚል ነው።

በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ የተለያዩ ስፍራዎች ስፖንሰር ለማግኘት ስንሔድ አሁንም ድረስ ጃዋር ነው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ነገር ግን አሁንም አስረግጠን መናገር ምንፈልገው ጉዳይ አዋሽ ኤፍ ኤም 90.7 የጃዋር አይደለም ጃዋርም በአዋሽ ላይ ምንም አይነት ድርሻ የለውም።

አዋሽ ኤፍ ኤምን የእናንተ ድርጅት ወይም እናንተ በምን ያህል ገንዘብ ገዛችሁት?
አሁን አዲስ መመሪያ ወጣ እንጂ በቀደመው ጊዜ ወይም አዋሽም በገዛንበት ወቅት መጀመሪያ ከመንግሥት የኤፍ ኤም ፍሪኩዌንሲ የተቀበሉ ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ማስወጣት አይቻልም ነበር። ስለዚህ እኛ ምንድነው ያደረግነው ፤ የአክሲዮኑን መጠን ከፍ በማድረግ እና ያለባቸውን ዕዳ የአቶ ቴዎድሮስንም ሆነ የመንግሥትን ዕዳ በሚከፍል መጠን ነው አክሲዮናችንን ከፍ አድርገን የገዛነው። ለዚህም ደግሞ ወጣው ወጪ 15 ሚሊዮን ይሆናል።

ዋይ ኤ ጄ በአዋሽ ኤፍ ኤም ላይ ምን ያህል የአክሲዮን ድርሻ አለው?
ዋይ ኤ ጄ በአዋሽ ኤፍ ኤም 90.7 ላይ ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ አክሲዮን ድርሻ አለው።

አዋሽን የገዛው የእናንተ ድርጅት ምን ይባላል ሌላስ በምን ንግድ ላይ የተሰማራ ነው?
አዋሽን የገዛው የእኛ ድርጅት ዋይ ኤ ጄ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ይባላል። የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራ ድርጅት ሲሆን ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ በቴሌኮም ዘርፍም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመስራት ካርዶችን ያቀርባል ከዛም በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችን (ሪል ስቴት) የሚሰራ ድርጅት ነው።

ድርጅታችሁ ወይም ዋኤጄ ከዚህ ቀደም በሚዲያው ዘርፍ ላይ ኢንቨስት አላደረገም፤ ልምድም እንደሌለው ይታወቃል። ሆኖም እንዴት ወደ ሚዲያው ዘርፍ ፊታችሁን አዙራችሁ መዋእለ ነዋያችሁን ልታፈሱ ደፈራችሁ ወይም ፍላጎት አሳያችሁ?
በእርግጥ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ልምድ የለንም ነገር ግን ሁሉም በመጀመሪያ አንድ ተብሎ ነው የሚጀመረው። ነገር ግን በተለያየ መንገድ በሚዲያው ዘርፍ እና ሚዲያ ጋር የተያያዙ ልምዶች ያለን ሰዎች አለን እዚህ ውስጥ። በዚህም ምክንያት ሚዲያ በጣም ገቢ የሚገኝበት እና ቢዝነስም ሚሰራበት ዘርፍ ነው። ለምሳሌ አሁን እኛ ዋይ ኤ ጄ የምንሰራቸው ስራዎች ቢኖሩ ፤ ለምሳሌ ዋይ ኤጄ በቅርቡ ኦንላይን ዩኒቨርስቲ ይጀምራል። አሁን ኢትዮጵያ መንግሥት ፈቅዷል፤ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ማስተርስ ላላቸው በኦንላይን በመመዝገብ እና በከፍተኛ ትምህርት ተያያዥነት እና ጥራት ኤጀንሲ ማረጋገቻ አግኝቶ የሚያስተምር እና የሚያስመርቅ ነው። ለዚህ ዓላማም ይህን አዲስ ስቱዲዮ በማስገንባታችን ይጠቅመናል። ኤጀንሲውም በአካል በመገኘት አይተውታል። መምህራኖች ወደዚህ በመምጣት ይቀርጻሉ የሚሟሉ ነገሮች አሉ እነርሱንም ለማሟላትም እየተንቀሳቀስን ነው።

ኦንላይን ይኑቨርስቲው ከአዋሽ ኤፍ ኤም መገዛት ጋር ተያይዞ መጣ ጉዳይ አይደለም። እኛ አዋሽን ለመግዛት በድንገት ነው የወሰንነው። ይሸጣል ሲባል ነው እንጂ እንዲያውም ያሰብነው ነገር ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ነበር። ለዚህም ደግሞ ጥናት አስጠንተን ጥናቱ ሁሉ አልቆ ነበር። ይሁን እንጂ አዋሽ ይሸጣል ሲባል ገዛነው ነገር ግን አሁንም ወደፊት ወደ ቴሌቪዥን እናሳድገዋለን።

የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሚዲያ በመንግሥት በኩል የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ እንዳይነገር ሕግ ከወጣ በኋላ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑ የሚታወቅ ነው። ነባራዊው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ወደ ሬዲዮ ቢዝነስ ለመግባት እንዴት ደፈራችሁ?
በፊት የነበረው አሰራር የቢራ እና አልኮል መጠጦችን የሚያስተዋውቁት እና ከዛም ገቢ የሚያገኙበት መስመር ነበር እውነት ነው፤የስራ አመራሮችም ከዛ የሚገኝ ገንዘብ እና ገቢ እንዳለ ያውቃሉ ገቢም ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ የንግድ አሰራር ገና እንደሆነ ማየት እንችላለን። የማስታወቂያን ቢዝነስም እያወቁ ሲሄዱ ገቢው እየበዛ ሊሄድ ይችላል። አሁን የኮቪድ 19 ወቅት ነው፤ ከኮቪድ በኋላ ድርጅቶች ወደ ማስታወቂያ ይመጣሉ። ከዚህ በኋላ ያሉትን ንግዶች የኦንላይን ንግድ ነው የሚሆኑን፤ በማስታወቂያ ነው የሚሰሩት፤ ነጋዴውም እያወቀ እገባው ሲሄድ ብዙ ጊዜ ሚዲያዎችን ይጠቀማል፤ ከሌላውመ አገር እኛ በምንም አንለይም። ሰለዚህ የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ መቅረቱ ምንም አይነት ጉዳት አያስከትልብንም።

አዋሽ ኤፍ ኤምን በሚመለከት በአሁኑ ሰዓት ሰዎች አቀባበል ምን ይመስላል? በእናንተ ስር ከሆነ ማለትም ዛሚ የሚለው ቀርቶ አዋሽ ፐብሊክ ኮኔክሽን ሲሆን እንዴት ነው ሰው እየተቀበለው ያለው?
ሰው ሁሉም አንድ አይነት አይደለም፤ ሰውንም ሁሉ በአንድ ማየት አያስፈልግም። አዋሽ አሁን በስፋት ይደመጣል፤ ኢ መደበኛ በሆነ መንገድ ጥናት ስናደርግም ብዙ ሰው አዋሽን ያዳምጣል እንዲሁም ስልክ በምንከፍትበትም ጊዜ በርካታ ሰው ስልክ እየደወለ ይነግረናል። የምንሰራቸው ስራዎች አገራዊ ናቸው፤ በተለይ ደግሞ ለምሳሌ በአባይ ጉዳይ ሰፊ ስራዎችን እሰራን እንገኛለን። ለዚህም ደግ በሳምንት አራት ጊዜ ስለ አባይ ልዩ ልዩ ስራዎችን እንሰራለን። በዚህ ጉዳይ በጣም ብዙ ሰው ፍላጎት አለው አዋሽን ለማዳመጥ፤ ሌላው ደግሞ ከሌላው ተለየ የምንሰራው ሌላው መርሃ ግብሮች እንዳሉ ሆኖ በተጨማሪም የአረብ ሚዲያዎች ስለ አባይ ምን ያወራሉ? ስለኢትዮጵያ ምን ያወራሉ? የሚለውን ጉዳይ በሳምንት ሦስት ጊዜ ዳሰሳ እናደርጋለን። ይህ ደግሞ ለሕብረተሰቡ ትልቅ ግብዓት ነው፤ ገና ችግሮችም ቢኖሩ ሳይመጡ ጠላትህም ሆነ ወዳጅህ ስለ አንተ ምን እያሰበ ነው የሚለውን ጉዳይ በትክክል አስቀድመህ ለማወቅ ይረዳሀል። ይህን እንሰራለን ስለዚህ አብዛኛው ሰው ደግሞ ሚገመግምህ በምትሰራው ስራ ስለሚሆን አዋሽ ዛሜ ይሁን ምንም ሳያውቅ ግን በምትሰራው ስራ እና ይዘት ሊመዝንህ ይችላል።
እኛ አሁን የምንሰራው ሕዝብን አቀራርቦ አገርን አንድ የሚደርግ ስራ ነው። ይህቺ አገር ለሁሉም እኩል ናት ስለዚህ እኛ ደግሞ በዚህ ላይ የምንጨምረው ጉዳይ ይረናል ስለ አገር አንድነት እና ስለ ሕዝቦች እኩልነት።ሁሉም እኩል ዜጋ ነው ፤ እኩል መብት አለው፤ ብሔር ለእኛ ተጨማሪ ሀብት እንጂ አያለያየንም። አዋሽም እስካሁን እሰራ ነበረው ይህንን ነው ከዚህ በኋላም አጠናክሮ ይቀጥላል።

አዋሽ አዳዲስ ፎርማቶችን ወይም ደግሞ አቀራረቦችን ይዞ መጥቶ ልዩ መርሃ ግብሮችን ሲያቀርብ እና ወደ ሕዝብ ሲደርስ አይታይም ስለዚህ ምን ይላሉ?
አዳዲስ ፕሮግራሞችን ይዘን መጥተናል አሁንም ወደ ሕዝብ እያደረስን እንገኛለን። የራሳችን ቀለም ይዘን በመምጣት ወደ ሕዝብም እየደረስን ነው። ለምሳሌ በቅርቡ ‹‹ይመለከተኛል›› የሚል ፕሮግራም ጀምረናል በዚህም ሕብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ያደርጋል። ይህ ፕሮግራም ሁሉንም ጉዳዮች የሚዳስስ ሲሆን ከባባድ ጉዳዮችም ይነሳሉ ነገር ግን በዚህ መሐል ሕብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖረው እናደርጋለን ይህም ለአገር ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለት ነው። ‹‹አዋሽ ስፔሻል›› የሚል አዳዲስ ዝግጅቶችም አሉን ፤ እንደአዲስ እያደራጀንም ነው በዚህም የሰው ኃይል አዳዲስ እየቀጠርንም ነው። ከሚቀየረውም ውስጥ ዜና ክፍሉ እንዱ ነው እንዲሁም ፕግራም ክፍሉም ለውጥ እየተደረገ እና እያደራጀን ነው። አዋሽ ከሌላው ሚለየው ምንድነው የሚለውን ሰርተን በዚህ ሳምንት ውስጥ ጀምሯል። ሰሞኑንም እያስተዋወቅን ነበር ፤ በአዲስ መልክ በአዲስ አሰራር እንመጣለን እያልን ማስታወቂያ እያስኬድን ነበር።

ያለንበት እና ሳለፍናቸው ወቅቶች ከባባድ ነበሩ። በተለይም ደግሞ ኮቪድ 19 ከባድ ተጽዕኖ በሁሉም ዘርፍ ላይ አድርሷል። በእናንተ ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ ምን ያህል ነው?
እንደማንኛውም የሚዲያ ተቋም እኛንም ጎድቶናል። በዛ ላይ ደግሞ እንደ ጀማሪ ሚዲያ ተቋምነታችን በኪሳራ ነው እየተንቀሳቀስንም ያለነው። አሁን ወደ አንድ አመት ሊሆነን ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኑ እኛ ከገዛንበት ጀምሮ ኮቪድ 19 መጣ ከዛ ቀጠሎ ደግሞ የአሁኑ የሕግ ማስከበሩ ጉዳይም መጥቶ ትንሽ እንቅስቃሴውን እንዲገታ አድርጎት ነበር። ከዛም በፊት ደግሞ በገዛንበት ወቅት ይሄ ዛሚ ሚለው ጉዳይ ፣ ጃዋር ስም አብሮ ከጣቢያው ጋር ተያይዞ መነሳት እና ሌሎች ጉዳዮች ከባድ ተጽዕኖ አድርሰውብን ነበር። ይሁን እንጂ አበአሁኑ ሰዓት ራሱን ወደ መቻል እየተጠጋ ነው።

ዋይ ኤጄ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር እንደ አዋሽ ሁሉ ወደ በሌሎች ጣቢያዎችም ላይ እንዲያው ባለድርሻ ለመሆን ፍላጎት ያድርበት ይሆን በቀጣይ?
አሁን እኛ ፈለግነው መጀመሪያ ይህን ጣቢያ በእግሩ ማቆም ነው። ከዛ ግን በቀጣይ ተለያዩ ለአገር ሚጠቅሙ ንግድ ዘርፎች ስላሉ ወደ እነርሱ ፊታችንን ልናዞር እንችላለን። እንዳልነው በሚዲያው እና በትምህር ዘርፍ ላይ በጣም መስራት እንፈልጋለን ምክንያቱ ደግሞ አገሪቱ በጣም ተጎድታለች። አገሪቱ ላይ ያለው ትምህርት ስርዓት የተበላሸ ስለሆነ እና የትምህርት ስርዓቱ እስካልተቀየረ ድረስ ይሕቺ አገር የትም አትሄድም። ስለዚህ ይህን ታሳቢ በማድረግ በትምህርት ዘርፍ ላይ ለመሳተፍ እና መዋእለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት አለን።

በሚዲያው ዘርፍ ያለው የበቃ ክህሎት ያላቸው ሰዎችን ማግኘት ከባዱ ጉዳይ ነው። ይህንንም ተከትሎ በሚዲያው በኩል የልህቀት ማዕከል እንዲቋቋም በርካቶች ይወተውታሉ። በዚህ ጉዳይ አርስዎ ምን ይላሉ?
እንዲያውም የእኛም ፍላጎት ይህ ነው በሚዲያው በኩል ስልጠናዎችን መስጠት ነው። ዋይ ኤ ጄ አንዱ ሚያደርገው ነገር ስልጠናዎችን መስጠት ነው በዋናነት የፋይናንስ ስልጠናዎችን መስጠት ነው። አሁን ደግሞ ሚዲያ ሰዎችን አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ማብቃት ፍላጎታችን ነው። ይህ አሁን የኮቪድም ጉዳይ እና አገራችንም ሰላም ከተመለሰ በኋላ ወደ ስራ እንገባለን። በየጊዜው ሰራተኞችን ካላሰለጠንን ፤ በየጊዜው ሰራተኞችን ካለበቃን እንኳን በሚዲያ ቀርቶ በሌላውም ዘርፍ ከባድ ነው የሚሆነው። ለእኛም ብቻ ሳይሆን አዚህ መጥተው ሰልጥነው ራሳቸውን እንዲችሉም ማድረግ ሀሳባችን ነው።

አዲስ የሚዲያ ሕግ እየወጣ ይገኛል እንዲሁም አዳዲስ ፖሊሲዎችም እየወጡ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም አሁን ያለውን እና ወደፊት ሊመጣ ይችላል ሚሉትን የሚዲያ መልክኣምድር እንዴት ያዩታል ጠቅለል አድርገው ቢመልሱልን።

ከዚህ ቀደም የነበረው የሚዲያ መልክአምድር በጣም ውስን እና አካታች ያለነበረ ነበር። ከዚህም ጋር ተያይዞ እንዲያውም ዲያስፖራዎችንም የሚያሳትፍ አልነበረም። አዲሱ ግን አሳታፊ ነው ስለዚህም ደግሞ ብዙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ እንዲሁም ብዙ ዕውቀቶችም ይሸጋገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ አዲሱ ሕግ ለሚዲያዎች ተሸለ እና ሰፋ ያለ ነጻነትን የሚሰጥ ይመስለኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com