ኢንቨስትመንቶች ለሚደርስባቸው ውድመት ወጥ የሆነ የካሳ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

Views: 216

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ጉዳት ሲደርስባቸው ለደረሰባቸው ውድመት ማካካሻ የሚያገኙበት አንድ ወጥ መመሪያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በተደጋገጋሚ በተለይም ከግጭቶች ጋር በተያያዘ ፕሮጀክቶች ሲወድሙ ፣ ሲቃጠሉ ፣ ሲጎዱ እና በነዚህ ጥፋቶች ኪሳራ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደተናገሩት እየተዘጋጀ ያለዉ መመሪያ ከዚህ በፊትም የነበረ ሲሆን ነገር ግን በአንድ ላይ በተቀናጀ መልኩ ስላልሆነ በተቀናጀ መልኩ መመሪያ መሰራት ተጀምሯል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ኢንቨስትመንቶች ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት ሲደርስባቸው መንግስት ብድሮችን ማመቻቸት ፣ ከወለድ ነፃ እቃዎችን እንዲያስገቡ ማድረግ ፣ የብድር ጊዜን ማራዘም የመሳሰሉትን ድጋፎች ያደርግላቸው ነበር ያሉት ተመስገን አሁን ግን በመመሪያ ማዕቀፍ የተሰራ መሆን እንዳለበት ስለታመነበት እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል።
ይህ መመሪያ አሁን ያሉትን የእርዳታ ሁኔታዎች በህግና በማዕቀፍ ወጥ እና ለሁሉም የሚያገለግል በሆነ መንገድ እንዲመሩ የሚያደርግ መመሪያ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እነዚህ አይነት ችግሮች ሳይታሰብ በሆነ አጋጣሚ የሚፈጠሩ ችግሮች ሲሆኑ መንግስትም የካምፓኒዎቹን ጊዜያዊ ችግሮች ለመፍታት ሲል የሚያደርጋቸው ነገሮች ናቸው ስለለዚህ ይህ መመሪያ መዘጋጀት በዋነኝነት ለመንግስትም ለኢንቨስተሩም ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል።

መመሪያውን ወጥ በሆነ መንገድ የማዘጋጀት ስራው እንደተጀመረና በቅርቡም ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመት ተመስገን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መመሪያው በገንዘብ ሚኒስቴር ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፣ ልማት ባንክ እና ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች በጋራ በመሆን የሚያዘጋጁ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህግ አስተማሪ እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ የህግ አማካሪ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) እንዳሉት ይህ መመሪያ ሲወጣ ለኢንቨስተሮች ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የሚደርሱ ጉዳቶች ላይ መንግስት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የተለያዩ እገዛዎችን ጉዳቱ ለደረሰባቸው ባለሀብቶች እንዲያገግሙ ሲያደርግ እንደቆየ ተናግረዋል።

በ 2012 ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ግን ከዚህ ቀደም ሌሎች ጉዳትለደረሰባቸው ኩባንያዎች ሲደረግ እንደነበረው ያልተደረላቸው እንዳሉ ጠቁመዋል።
በአገራችን ያለዉ የመድን ስርኣት ይህን ለመሸፈን የሚያስችለው ሁኔታ ላይ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግር በተፈጠረ ቁጥር መንግስት ነው የሚሸፍነው ለአብነትም በ2008 በጀት አመት የተከሰተውን ችግር በተመለከተ በሦስት ተከታታይ ዙር ጉዳቶችን ለመጠገን መንግስት ሲሸከም መኖሩ ይታወቃል ብለዋል።

ይህ መመሪያ ተዘጋጅቶ ሲያልቅ የሚፈጠረውን የእገዛ ዓይነት ይወስናሉ በዚህ ምናልባትም የሚቀነሱ ወይም የሚጨመሩ የእርዳታ አይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንት ለአንድ አገር እድገት ከፍተኛ ሚና አለው፤ በአገራችን ያለውን የዶላር እጥረት ለመቅረፍ ፣ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም አገርን ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ከፍተኛ የህግ አማካሪው አያይዘው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ባለፉት አመታት ኮቪድ 19 ካሳደረበት ተፅዕኖ በዘለለ በግጭቶች ምክንያት በከፍተኛ መልኩ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ይታወቃል ፤ በዚህም በደረሱ ጉዳቶች 300 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ውደመት እንደደረሰባቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com