የሲሊንደር ጋዝ ዋጋ በኹለት ሳምንት የ350 ብር ጭማሪ አሳየ

Views: 257

በአዲስ አበባ የሲሊንደር ጋዝ ዋጋ በኹለት ሳምንት ውስጥ እስከ 350 ብር ጭማሪ ማሳየቱን የሲሊንደር ጋዝ የሚጠቀሙ ምግብ ቤቶች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
በአዲስ አበባ ለተጠቃሚዎች ሲሊንደር ጋዝ በችርቻሮ በሚሸጡ ጋዝ ቤቶች ከኹለት ሳምንት በፊት 650 ብር ሲሸጥ የነበረ 12 ኪሎ ግራም ሲሊንደር ጋዝ እስከ አንድ ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን ተጠቃሚዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ የተጠቃሚዎቹን ጥቆማ ይዛ በአዲስ አበባ ሲሊንደር ጋዝ ለተጠቃሚዎች የሚቸረችሩ ጋዝ ቤቶችን ተዘዋውራ ተመልክታለች። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ የገበያ ሁኔታውን በተመለከተችበት ጊዜም በትክክልም የተባለው የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ለማረጋገጥ ችላለች።

የዋጋ ጭማሪው በተለያዩ የጋዝ መሽጫ ቦታዎች የተለያያ መሆኑን አዲስ ማለዳ ለማረጋገጥ ችላለች። የዋጋ ጭማሪው በአንዳንድ ጋዝ ቤቶች 12 ኪሎ ግራም ሲሊንደፈር ጋዝ ከ 800 ብር አስከ 900 ብር ሲሸጥ እንደ ፒያሳ ባሉ አካባቢዎች እስከ አንድ ሺሕ ብር እየተሸጠ ነው።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ሲሊንደር ጋዝ ከሚጠቀሙ ምግብ ቤቶች ውስጥ ደስታ ምግብ ቤት አንዱ ነው። የደስታ ምግብ ቤት ባለቤት የሆኑት ደስታ ብርሃኑ ከኹለት ሳምንት በፊት 650 ብር የገዙት 12 ኪሎ ግራም ሲሊንደር ጋዝ አንድ ሺሕ ብር በመድረሱ ምግብ ቤታቸው በከሰል መግብ ማብሰል መጀመሩን አስረድተዋል። ደስታ እንደሚሉት ከሆነ የሲሊንደር ጋዝ ዋጋ በመናሩ እና ሲሊንደር የሚቀርቡ ጋዝ ቤቶች ሲሊንደር ባለማቅረባቸው የከሰል ገበያውም መጨመሩን ገልጸዋል።

ሲሊንደር ጋዝ ማግኘት ያልቻሉ ምግብ ቤቶች ምግብ ለማብሰል የኤሌክትሪክ ኃይል አንደማያገኙ ተናግረዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት የምግብ ማብሰያ የኤሌክትሪክ ፍጆታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ለመሥሪያ የተከራዩት ቤት ለምግብ ማብሰያ ኤሌክትሪ መጠቀም የተከለከለ በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል። በዚህም ከሰልን አንደ አማራጭ በመጠቀማቸው የከሰል ዋጋ ከመጨመሩ በተጨማሪ የከሰል ጭስ ሙሉ ቀን የሚጨስባቸው ምግብ አብሳዮቹ ላይ የጤና ችግር እንደሚፈጥርባቸው ተመላክቷል።

የሲሊንደር ዋጋ ለመጨመሩና በአንዳንድ ነዳጅ መሽጫ ሱቆች የዋጋ ጭማሪው ለመታየቱ ዋነኛው ምክንያት በቂ የሆነ የአቅርቦት ችግር በመከሰቱ መሆኑን እሽቱ ለማ የግዮን ጋዝ አከፋፋይ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጧል። የአቅርቦት ችግር በመታየቱ ዋና አከፋፋዮች ለቸርቻሪዎች ወይም በቀጥታ ለተጠቃሚ ለሚሸጡ ነጋደዎች ሲሊንደር ጋዝ መሽጥ ማቆማቸው ነው ተብሏል።

ዋና አከፋፋዮች ሲሊንደር ጋዝ እጥረት በሚታይበት ጊዜ ለቸርቻሪዎች ከመሸጥ ይልቅ እራሳቸው ቸርቻሪ ነጋደዎች በሚሸጡበት ዋጋ ለመሸጥ ለቸርቻሪዎች የለም በማለት የዋጋ ጭማሪው እንዳሻቅብ እንዳደረጉት አዲስ ማለዳ ያጋገረቻቸው ሲሊንደር ጋዝ ቸርቻሪ የሆኑት ኃይሉ ተክለ ጊወርጊስ ተናግረዋል።
እንዲሁም እሸቱ ለማ የጊዎን ጋዝ አከፋፋይ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ዋና አከፋፋዮች ሲሊንደር ጋዝ እያለ ለራሳቸው በማከማቸት ተጠቃሚ በሚገዛበት ዋጋ እየሸጡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዳንኤል ሜኤሳ ከአዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቢሮው መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ በመጥቀስ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ አይመለከተንም ሲሉ ምለሻቸውን ሰጥተዋል። የንግድ ውድድር እና ሽማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ የኔ ስልጣን ዋጋ መቆጣጠር አይደለም ብሏል። ይሁን እንጂ ይህን ጉዳይ በቅርቡ የማይፈታ ከሆነ እና ኃላፊነት የመሸሽ ጉዳዮች እየታዩ በመሆኑ በምግብ ቤቶች ላይ ዋጋ ጭማሪ እንደሚያጋጥም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች እና ምግብ ቤት ባለቤቶች አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com