የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች ረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጀ ነው

Views: 202

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የሞተር አልባ ባለሦስት እና ባለኹለት እግር ተሽከርካሪዎች ምን ዓይነት ነገሮችን ሊያሟሉ እንደሚገባ የሚያሳይ ረቂቂ ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ይህ የሚዘጋጀው ረቂቂ ደረጃ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ሲሆን ከአገር ውጪ የሚሰሩትንም ሆነ በአገር ውስጥ የሚመረቱትን ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች ምን አይነት ደረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑንን ተናግረዋል።

ደረጃው በኤሌክትሪክ ፣ በጸሐይ ኃይል እንዲሁም በሰው ጉልበት (ፔዳል) የሚሰሩትን ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች ያማከለ ነው ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይስማ ጅሩ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት እየተዘጋጀ ያለው ረቂቅ ደረጃ የብስክሌት እንደሆነ ተናግረዋል።

የሚወጣው ረቂቅ ደረጃ የብስክሌት ደረጃው ምን ማሟላት አለበት የሚለውን የሚያሳይ ሲሆን ይህንንም ለመስራት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ከብስክሌት አስመጪዎች ፣ አምራቾች ጋር ከተወጣጡ ባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ነው ብለዋል።

አገራችን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ነድፋ ወደ ሥራ እንደገባች ይታወቃል ፤ በዚህም መሠረት በኤሌክትሪክ የሚሰራ የከተማ የባቡር ትራንስፖርት በአዲስ አበባ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ያሉት ይስማ ይህም የካርበን ልቀት መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

መኪኖችም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ እንዲሆኑ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል በዚህም ይህ መመሪያም የዚሁ እስትራቴጂ አካል የሆነ የሞትር አልባ ትራንስፖርት ለማበረታታት በእጅም ሆነ በእግር ለሚንቀሳቀሱ ባለኹለት ጎማና ባለ ሶስት ጎማ ብስክሌቶች ረቂቅ ደረጃ መዘጋጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይህ መመሪያ ለህፃናት የሚመረቱ ምን መሆን አለባቸው ፣ ለአዋቂዎችች የሚመረቱት ምን መሆን አለባቸው ፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚመረቱት ምን አይነት መሆን አለባቸው የሚለውን የጎማውን ሁኔታ ፣ የመቀመጫውን ፣ የመብራቶቹን በአጠቃላይ ሁሉንም የብስክሌቱን አካል ደረጃው ምን መሆን እንዳለበት ይወስናል ብለዋል።

ደረጃ ማለት ለአንድ ምርት ወይንም አገልግሎት ማሟላት ያለበት ዝርዝር መስፈርት ፣ የአሰራር ስረዓት የማጓጓዣ ሁኔታ ስለምርቱ ይዘት መገለፅ አለበት የሚሉ ዝርዝር ነገሮችን የያዘ ነው ያሉት ይስማ ይህ መመሪያም እነዚህን የያዘ ነው ከአገራችን የአየር ንብረት ሁኔታ ጋር ምን መሆን አለበት የሚለውን እና እንዴት አይነት ደረጃ ሊኖረው ይገባል የሚለውን አስቀምጦ የተጣጣመ ሁኔታ እንዲኖር ያስችላል በማለት አስረድተዋል።

ሁሉም የተስማማበትና በብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት የሚፀድቅ ይሆናል በቅርቡም ረቂቅ ደረጃው ተሰርቶ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።
በዋናነት የዚህ ደረጃ መፅደቅ ሰው ይህን ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች በሚጠቀምበት ወቅት የካርቦን ልቀትን ይቀንሳል ፣ ደረጃውን የጠበቀ ብስክሌት እንዲኖር ያደርጋል ፣ የትራንስፖርት ችግርንም በመጠኑ ሊቀንስ ይችላል ፣ አደጋን ከመቀነስ አንፃርም ይጠቅማል ተብሎ ታምኖበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የመንግሥትን አርንጓዴ ፖሊሲ ከማስፈፀም አንፃር የካርበን ልቀትን የሚቀንሱ ምርቶች እንዲበዙ ስለሚፈለግ ይህ ደረጃ መሰራቱ ካለሞተር የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ተጠቃሚ ያበዛል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የብስክሌት መንገዶች እየተሰሩ በመሆኑ ረቂቅ ደረጃ መዘጋጀቱ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
ለአብነትም ከጀሞ -ለቡ ፣ አያት እና ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ጅምር የባለ ኹለት እግር ተሽከርካሪ መንገዶች እየተሰሩ መኖራቸው ጠቁመው ደረጃውን የጠበቀ ተሽከርካሪ ሳይኖር መንገዱ መሰራቱ ስለማይጠቅም አስቀድሞ ግን ደረጃውን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል።

አሁን ላይ የሚሰሩት አዳዲሶቹ መንገዶች ለብስክሌት ያማከለ እንዲሆን ተደርገው እየተሰሩ ስለሆነ ደረጃውን የጠበቀ ተሽከርካሪ መኖር እንዳለበት ለዚህም መመሪያው አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

በረቂቅ ደረጃ ዝግጅቱ ላይ ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ፣ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ፣ ከብስክሌት አስመጪ ድርጅቶች እና በዋናነት ኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የተወጣጡ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን እንደሚያወጡም የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com