በቀጣይ 10 ዓመት ሥራ አጥነት ወደ ዘጠኝ በመቶ ዝቅ እንደሚል ተገለጸ

Views: 187

የኢትዮጵያ የ 10 ዓመት ብሔራዊ የልማት ዕቅድ በ2013 ተጀምሮ በ 2022 ሲጠናቀቅ ተፈፃሚ ይሆናሉ ከተባሉ የዕቅዱ ዋና ዋና ግቦች መካከል አንዱ አገራዊ የከተማ ሥራ አጥነት ምጣኔን ከ 18.7 በመቶ ወደ 9 በመቶ ዝቅ ማድረግ እንደሆነ ተጠቆመ።

በኢትዮጵያ አጠቃላይ የሥራ አጥነትን ካየን ትልቁን ቁጥር የምናገኘው በከተሞች ላይ ነው። በሚቀጥለው 10 ዓመት ይህንን ቁጥር ከግማሽ በላይ ለመቀነስ ወይንም ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ ታቅዷል ሲሉ የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነመራ ገበየሁ(ዶ/ር) ተናግረዋል።

እንደ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማሕበር (ወወክማ) ሪፖርት ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል 70 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ 30 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው የሚሉት ነመራ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ደግሞ ከ 32 ሺሕ በላይ ሥራ የሌላቸው ወጣቶች መመዝገቡን አስታውቋል። በኢትዮጵያ ያለው የሥራ አጥ ቁጥር እንደ ፈረንጎቹ አቆጣጠር በ 2009 2 ነጥብ 34 በመቶ የነበረ ሲሆን ከ 10 ዓመት በኋላ በ2019 ወደ 2 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ እንዳለ የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ጥናት ያሳያል።

ሌላው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አሁን ካለው የማመንጨት አቅም 4 ሺሕ 478 ሜጋ ዋት ወደ 17 ሺሕ 056 ሜጋ ዋት ከፍ ማድረግ ማለትም በ 2012 ካለው 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ከሆኑ ደንበኞች በ 2022 ወደ 24 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ማድረግ ከልማት ዕቅዱ ዋና ዋና ግቦች መካካል ተቀምጧል። የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎችን ሳይጨምር በኢትዮጵያ 3.4 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

በፕላን እና ልማት ኮሚሽን የተዘጋጀው እና የመገናኛ ብዙኃንን ሃሳብ ለመጨመር የቀረበውን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አራተኛ ክንድ በመሆኑ ከዕቅዱ ጀምሮ ተሳታፊ ከሆኑ ሥራው ሳይሠራ ከቀረ ለተጠያቂነት ያመቻል ሲሉ የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የልማት ዕቅዱን የዝግጅት ሂደት እና የባለ ድርሻ አካላትን ተሳትፎ እንዲሁም አተገባበር ያስረዱት የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነመራ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የ 10 ዓመት መሪ ብሔራዊ የልማት ዕቅድ ከመታቀዱ በፊት ከ12 በላይ የሚሆኑ መነሻ ጥናቶች ተደርገዋል ብለዋል።

እንዲሁም የተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች ተወስደዋል ከግሉ ዘርፍ ከመቶ በላይ የየዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል እንዲሁም ከአሁን በፊት እንደተለመደው ብሄራዊ የፕላን እና የልማት ኮሚሽን ብቻ አላቀደውም። እንዲሁም የ 10 ዓመቱን ዕቅድ የጋራ ዕቅድ እንደመሆኑ መጠን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መሳተፋቸው በጣም አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ ለመጀመርያ ጊዜ ለ 10 ዓመታት በታቀደ ብሔራዊ የልማት ዕቅዱ መሠረት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ባለው ጊዜ በአማካይ 10 በመቶ እንደሚያድግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ማደግ ያለባት በኢኮኖሚ ብቻ አይደለም ሲሉ ነመራ(ዶ/ር) ገልጸዋል። በመልካም አስተዳደር በፍትሕ ተደራሽነት በአገር ውስጥ ሰላም ግንባታ እና ከጎረቤት አገራት ጋር በሚኖር መልካም የሆነ ግንኙነት እና ቀጠናዊ የልማት ትብብርን ከፍ ማድረግ እንደ አንድ የልማት ምሶሶ ልናየው ይገባል ብለዋል።

ሌላው ደግሞ የዚህ የ10 ዓመት ዕቅድ ምሶሶ የሆነውን የኢትዮጵያን የገንዘብ ምንጭ ማሳደግ ነው። ይህንን ለማረግ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ከጥቃቅን ጀምሮ እስከ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የግሉን ዘርፍ ተሳታፊ ማድረግ ይገባል። ሌላው ደግሞ ትኩረት ያልተሰጣቸውን ዘርፎች ትኩረት በመስጠት ገንዘብ ማምጣት ነው። ከእነዚህ መካከል የማዐድን ዘርፍ፣ ቱሪዝም ዘርፍ እና ከተሜነትን መሰረት ያደረገ ICT ዘርፍ እንደሆነ አሳውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com