የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ይቀጥላል ተባለ

Views: 224

በኢትዮጵያ የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደማይቆም እና ፓርኮችን መገንባቱ እንደሚቀጥል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መንግስት አይገነባም የሚባለው መረጃ በተገቢው መልኩ ማህበረሰቡ ጋር እንዳልደረሰ መንግስት የሰራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ እና ሌሎችም እንደሚገነባ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሀላፊ ሳንዶካን ደበበ እንደተናገሩት ፓርኮችን መንግስት መገንባት ያቆማል የሚለው መረጃ ልክ እንዳልሆነና በመሰረቱ አዳዲስ ፓርኮች መገንባት አለመገንባቱን የሚወስነው መንግስት ሳይሆን የገበያው ሁኔታ ነው ፍላጎት ካለ መገንባቱ ይቀጥላል ብለዋል።

ፓርኮች የት የት ቦታ መገንባት አለባቸው ፣ ሲገነቡ ምን ሊያሟሉ ይገባል ፣ ምን ሲሟላለት ነው ፓርክ የሚገነባው የት ወረዳ ፣ የት ቀበሌ እና ምን ያሟላ የሚለው የሚያፀና ጥናት እየተጠና እንዳለ እና አልቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል ፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ፓርኮች አይገነቡም የሚባልበት አግባብ የለም ብለዋል።

በፓርኮች ውስጥ ያለ ዋነኛ ችግር የመሰረተ ልማት ችግር ነው ለአብነትም የመንገድ ፣ የቴሎኮም ፣ የመብራት ፣ የውሀ ችግሮች ይስተዋላሉ በተለይም የመንገድ ችግር ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድራል በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አንድን ምርት ከተመረተ በኋላ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር መንገድ ወሳኝነት እንዳለው ይታወቃል በዚህም ብዙ የኢንድስትሪያል ፓርኮች ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲያነሱ ይስተዋላል ጥያቄውም አግባብነት አለው ብለዋል።

እነዚህ ችግሮች ካለው ነባራዊ ሁኔታ እና ትኩረት ካለመስጠት የተነሳ የሚመጡ ሲሆኑ ለዚህም መሰረተ ልማት የሚያቀርቡ ተቋማት ጋር በመተባበር ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግስት ፓርኮችን ገንብቶ ባለሀብቶችን አስመጥቶ ያልተሟላ መሰረተ ልማት ሲኖር ያስቸግረናል ብለዋል።
ፓርክ የመገንባት መሰረታዊ አላማው መሰረተ ልማቶች በተቀናጀ ሁኔታ በማቅረብ ባለ ሀብቶች መሰረተ ልማት ለማግኘት የሚሄዱባቸውን መንገዶች መቀነስ ነው ፤ ይሁን እንጂ ፓርኮች ተገንብተው መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው አሉ ፤ መሰረተ ልማቱን የሚያቀርቡት የመንግስት ተቋማት በሚፈለገዉ ፍጥነት እና ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ፓርክ ገንብተህ መሰረተ ልማት አላሟላህም ማለት ባለሀብት አይመጣም ፣ ባለሀብት ካመጣ የስራ ዕድል አይፈጠርም ፣ የውጪ ምንዛሬ አይገኝም ስለዚህ ጥቅም አይኖረውም ብለዋል።

መሰረተ ልማት ከሚያቀርቡ ተቋማት ጋር ለፓርኮች አስፈላጊነቱን እና አሳሳቢነቱን የማስረዳት ስራ እየሰራን ነው በዚህም ባለሀብቶች በእነዚህ ችግሮች እንዳይጉላሉ እየሰራን ነው ችግሮቹም በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ይታመናል ብለዋል።

የኮቪድ 19 መምጣት ጉዳት ያላደረሰበት ዘርፍ የለም የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ምርቶቻቸውን በብዛት ወደ ውጪ አገራት ስለሚልኩ ተቀባይ አገራት በመዘጋታቸው ምክንያት ትእዛዞች የሰረዙ አገራት ነበሩ ብለዋል።

በዚህም በኮቪድ 19 ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ባይጠፉም ዋነኞቹ ተጎጂዎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ነበሩ።
ይሁን እንጂ መንግስት ምርቶቻቸውን ወደ አገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ሌሎች ለኮቪድ 19 መከላከያ የሚሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ በማድረግ በዘርፉ የነበረውን ጉዳት ለመቀነስ ሞክሯል ብለዋል።

በሌላ በኩል ሰራተኛ እንዳይቀንሱ በማድረግ ረገድም መንግስት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም ተናግረዋል።
በአገራችን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ሎጀስቲክ እና ጉምሩክ ጉዳይ ሁሉም ባለሀብቶች ቅድሚያ የሚነሷቸው ችግሮች ናቸው። የዚህ መንስኤው አለም አቀፍ ውድድር ያለበት ዘርፍ ነው ስለዚህ በፈለገው ሰዓት እንደምታቀርብለት እግጠኛ ካልሆነ እድሉን አይሰጥህም በዚህም ሎጀስቲክ ላይ ያለው ክፍተት ዘርፉን ያስተጓጉለዋል ብለዋል።

ወደ ውጭ ለሚልኩ የባቡር ትራንስፖርት እንዲጠቀሙ ተደርጓል ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቡ ወይም በገቢ ንግዱ ላይ ለተሰማሩ ግን አይጠቀሙም ነበር በዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች ላይ 13 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዳሉና ከእነርሱ መካከል 11 የሚሆኑት የኢንደስትሪ ፓርኮች እየሰሩ እንደሆነ የቀሩት ኹለቱ ደግሞ አንደኛው በግንባታ ላይ ሲሆን አንደኛው ደግሞ ባለሀብት ገብቶ የማሽን ግንባታዎች እየገቡ እንዳሉ አዲስ ማለዳ ካየቻቸው መረጃዎች ለማወቅ ችላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com