በአንበጣ መንጋ ለተጎዱ የወረባቦ ወረዳ አርሶ አደሮች የሚቀርበው ድጋፍ ፍትሐዊ አይደለም ተባለ

Views: 202

በበረሃ አንበጣ መንጋ ሰብላቸው የወደመባቸው የደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ አርሶ አደሮች በመንግሥትና በበጎ ፈቃደኞች የሚቀርቡ ድጋፎች ለተጎጅ አርሶ አደሮች በእኩል እየተሰራጩ አለመሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አሰሙ።

በወረባቦ ወረዳ ቀበሌ 17 አርሶ አደር የሆኑት መሀመድ ሲራጅ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በወረዳው ተከስቶ በነበረው የበረሃ አንበጣ ሁሉም አርሶ አደር የጉዳቱ ሰለባ ቢሆንም ከመንግሥት፣ ከበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚቀርቡ ድጋፎች በፍትሐዊነት እየተሰራጩ አለመሆኑን ተናግረዋል። በግብርና የሚተዳደሩት መሀመድ በወረዳው በበረሃ አንበጣ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ ከወደመባቸው አርሶ አደሮች አንዱ ቢሆኑም ለአርሶ አደሩ ከቀረበው ድጋፍ የደረሳቸው ከሌሎች የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

መሀመድ የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነገር ግን የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ሆነው ለአንዳንድ መሰል አርሶ አደሮች የቀበሌው አስተዳደር ሦስት ሺሕ ብር ሲሰጣቸው ለርሳቸው እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል። አርሶ አደሩ መሀመድ በዘንድሮው የምርት ዘመን አልምተውት የነበረው አምስት ሄክታር ማሽላ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የበረሃ አንበጣ ሰለባ ስለሆነባቸው የአንድ ዓመት የሙሉ ቤተሰብ ምግብ ያስፈልገኛል ብለዋል።

ሌላኛው ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያቀረቡት አርሶ አደር አህመድ ሰይድ ሲሆኑ መንግሥት ለአርሶ አደሩ የላከው ድጋፍ በተገቢው መንገድ እየደረሰን አይደለም ብለዋል። አህመድ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት ከሆነ የቀበሌው አመራሮች ለአርሶ አደሩ የቀረበውን ድጋፍ በኮታ እጥረት ሰበብ እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረጉ ነው ብለዋል።

“የበረሃ አንበጣ የጎዳው ሁላችንንም ሆኖ ሳለ የቀበሌ አመራሮች የቀረበውን ድጋፍ እከሌ ከከሌ ይሻላል በማለት በኮታ ድልድል ሁላችንም እኩል ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም።” ሲሉ አህመድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የወረባቦ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የሱፍ መሀመድ የአርሶ አደሮቹን ቅሬታ ትክክል መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። የእርዳታ ስርጭት በባህሪው ቅሬታ የሚጠፋበት አይደለም ያሉት ምክትል ኃላፊው በአንዳንድ ቀበሌዎች ላይ የስርጭት ችግር እንዳለ ተናግረዋል።

የስርጭት ችግሩ የተከሰተው በወረዳ ደረጃ አለመሆኑን የጠቆሙት የሱፍ ችግሩ የተፈጠረው ቀበሌ ላይ ለአርሶ አደሩ በቀጥታ በሚሰራጩ የቀበሌ አመራሮች መሆኑን ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ ቅሬታቸውን ለወረዳው ማቅረባቸውንም የሱፍ አክለው ገልጽዋል። ቅሬታ በቀረበባቸው ቀበሌዎች ወረዳው የስርጭት ሥራውን እየተከታተለ እንደሆነ ተመላክቷል። በሥርጭት ሥራው ላይ የሚታዩ ችግሮችን ወረዳው በቀረበለት ቅሬታ መሰረት ለማስተካከል እየሠራ መሆኑን የሱፍ አብራርተዋል።

በወረዳው ከስርጭት ፍትሐዊነት በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ በቂ የሚባል አቅርቦት እንደሌለ የሱፍ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አሁን ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ያለው እርዳታ የማኅበረሰቡን ተስፋ መቁረጥ ያረገበ እንጅ በቂና ዘላቂ ነው ለማለት እንደሚቸግር ነው ምክትል ኃላፊው አክለው የገለጹት።
በወረዳው ከሚገኙ 23 ቀበሌዎች በ13 ቀበሌዎች የበረሃ አንበጣ ተከስቶ ሙሉ በሙሉ የሰበል እና እንሰሳት መኖ ማውደሙን አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ መዘገቧ የሚታወስ ነው።

የአካባቢው ማኅበረሰብ በደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ የስነ-ልቦና ችግር ውስጥ ገብቶ አንደነበረም የሱፍ አስታውሰዋል። በወረባቦ ወረዳ ከሚኖረው 140 ሺሕ ዜጋ ውስጥ 54 ሺሕ ያክሉ ለርሃብ አደጋ የተጋለጠ መሆኑ የሚታወስ ነው። በስፍራውም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተገኝተው በበርሃ አንበጣ ጉዳት የደረሰበትን ሰብል እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ማነጋገራቸው የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com