ከአትክልት ተራ የተነሱ ነጋዴዎች የተሰጠን ስፍራ ቀድሞ በሰዎች የተያዘ ነው አሉ

Views: 280

ከፒያሳ አትክልት ተራ በጊዜያዊነት ወደ ጃን ሜዳ ተዛውረው የነበሩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የንግድ ቦታ ተሰርቶላችኋል ተብለን ከጃን ሜዳ ብንነሳም ቦታውን ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከመጋቢት 28/2012 ጀምረን ከፒያሳ ተነስተን ወደ ጃን ሜዳ በመሄድ ሥራችን ሥንሠራ ቆይተናል። ካለፈው 15 ቀን ወዲህ ደግሞ ኃይሌ ጋርመንት ሂዱ ስንባል ወደ ሥፍራው ብናመራም ለእናንተ ተሠርተዋል የተባሉ እና የእጣ ቁጥር የተሰጠን ሱቆች ውስጥ ሌሎች ሰዎች ገብተውበታል ሲሉ ተናግረዋል።

ከኹለት መቶ በላይ ቅሬታ አቅራቢዎች ወደ አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመሄድ ጥያቄዎቻችንን አቅርበን ምንም አይነት ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል።
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ ቅሬታ አቅርበው ጉዳያችሁን በደብዳቤ አቅርቡ እንደተባሉ ተናግረዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ፒያሳ በሚገኘው የአትክልት ተራ ከ 40 ዓመታት በላይ የሠራን በዚህ ሥራ ቤተሰቦቻችን የምናስተዳድር እና ሕይወታችንን የምንመራ ብንሆንም አሁን ላይ ችግር ውስጥ ወድቀናል ብለዋል።

በዚህ ምክንያትም ላለፉት 15 ቀናት ያለሥራ እያሳለፍን ሲሆን ቤተሰቦቻችንም ችግር ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል። እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች በማኅበር የተደራጀን ስንሆን አንዳንዶቹ ማኅበራት በአክሲዮን ተደራጅተው እዚያው ፒያሳ የቀድሞው አትክልት ተራ አቅራቢያ ሕንፃ እንደሰሩም ገልጸው ሕንፃው ውስጥ ግን ገብተው ሥራ መጀመር አለመቻላቸውንም ተናግረዋል። ነጋዴዎቹ ሕጋዊ የሆንን ግብር የምንከፍል እና የንግድ ፍቃድ ያለን ነን ለዚህ ማስረጃዎችን ማቅረብ እንችላለን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአትክልት ተራ ግብይት ጃንሜዳ እንዲሆን የወሰነው በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንደነበረ ይታወሳል። ከተማ አስተዳደሩ በወቅቱ የፒያሳው አትክልት ተራ ለነጋዴዎች ዕቃ ማስቀመጫ መጋዘን ብቻ ሆኖ እንደሚያገለግል ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጃንሜዳን ለጥምቀት በዓል የማፅዳት ሥራን አስመልክተው በሰጡት መግለጫም በኮቪድ19 ምክንያት በጊዜያዊነት በጃን ሜዳ ሲከናወን የቆየውን የአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኃይሌ ጋርመንት የገበያ ማዕከል እንደሚዘዋወር ተናግረዋል። ከንቲባዋ አክለውም በገርጅ፣ ጀሞ፣ አቃቂ፣ ጉለሌ እና ሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ አዳዲስ ሌሎች የአትክልት መገበያያ ሥፍራዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲገልጹ ከፒያሳ አትክልት ተራ ተነስተን ወደ ጃን ሜዳ ስንሄድ ከነበሩን ደንበኞች ጋር ተራርቀናል ብዙ ደንበኞችም ለማግኘት ስለተቸገርን እና የምንሸጣቸው አትክልት እና ፍራፍሬዎች በቶሎ የሚበላሹ ስለሆኑ ኪሳራ ውስጥ ነን ብለዋል ኃይሌ ጋርመንት ደግሞ የበለጠ ሩቅ ይሆንብና ብለዋል።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ እና የቅሬታ ሰሚ ሰብሳቢ ዳንኤል ሚኤሶ ከፒያሳ አትክልት ተራ ወደ የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴዎችን ወደ ጃን ሜዳ ስንወስድ 680 የሚሆኑ ሕጋዊ የሆነ የታደሰ የንግድ ፈቃድ ያላቸውን የመምረጥ ሥራ በመሥራት እና በመለየት ነው ብለዋል።

አትክልት ተራ በፒያሳ በነበረበት ወቅት በአንድ ሰው የንግድ ፈቃድ ተደርበው የሚነግዱ ነጋዴዎች መኖራቸውን አረጋግጠናል ይህ ማለት በአንድ ሱቅ ከአንድ በላይ ሁነው ሲሰሩ ቆይተዋል። አሁን ሕጋዊ የሆኑ አካላትን የመለየት ሥራ ሥንሰራ እነዚህ አካላትን ነው አየር ላይ እያዋልን ያለነው በማለት ገልጸዋል።

አሁን በኃይሌ ጋርመንት የሱቅ እደላ ስናደርግ ከ2006 ወዲህ የታደሰ ሕጋዊ የሆነ የንግድ ፍቃድ ያለው በአክሲዮን የተደራጀ እና ከአክሲዮን ማሕበሩ ውስጥ የስም ዝርዝሩ ያለ የአትክልት ነጋዴ ለሆነ ሁሉ ሱቆች ሰጥተናል ይህንን ሁሉ አሟልቶ ሱቅ አላገኘሁም የሚል አካል ግን ቅሬታ ማቅረብ አለበት ዛሬ ታህሳስ 15 ወደ አንድ መቶ የሚሆኑ ቅሬታዎችን ማየት ጀምረናል ቅሬታ ላቀረቡ አካላት ውሳኔ እንሰጣለን በማለት ተናግረዋል።

ኀላፊው አክውም ውሳኔ እንሰጣለን ስንል ቅሬታቸው ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን እና ከኹለት ዓመት በላይ የንግድ ፈቃዳቸው የቆየ ነው አይደለም የሚለውን እንዲሁም በአክሲዮን የተደራጁ ከሆኑ አባላት መሆናቸውን አይተን በዚህ መንገድ ቅሬታቸውን ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com