ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት የተፈናቀሉ 27 ሺሕ ዜጎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል

Views: 218

በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ ታኅሳስ 14/2013 በተፈጸመ ጥቃት ተፈናቅለው ቡለን ከተማ የሚገኙ ከ27 ሺሕ በላይ ዜጎች አስፈላጊው እርዳታ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ በምግብ ዕጦት መቸገራቸውን ገለጹ።

በንጹሓን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት አካባቢያቸውን ለቀው ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ቡለን ከተማ የሚገኙ ከ27 ሺሕ በላይ የኩጅ ቀበሌ ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ መግባት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ እስከገለጹበት ስዓት ድረስ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከየቤቱ ምግብ አሰባስቦ እየመገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ነገር ግን መንግሥት ያቀረበላቸው አስቸኳይ የምግብና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እንዳልቀረበላቸው ተናግረዋል።

የከተማዋ በጎ ፈቃድ ወጣቶች ተፈናቃዮችን ከማኅበረሰቡ የበሰለ ምግብ በማሰባሰብ እየመገቡ መሆኑን ስማቸው አንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተባባሪ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከማኅበረሰቡ የሚያገኙትን ድጋፍ ለተጎጂዎች እያደረሱ ቢሆንም ካሳለፍነው ሐሙስ ምሽት ጀምሮ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።

አስተባባሪው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት መንግሥት ለተፈናቃዮች አስቸኳይ ምግብ እንዲያቀርብላቸው ጥሪ አቅርበዋል። ከማኅበረሰቡ የሚለገሱ የበሰሉ ምግቦች እየቀነሱ በመሆኑ አስተባባሪዎች አንደ አማራጭ በቆሎ አበስለን እያቀረብን ነው ብለዋል።

የተጠቀሰው የተፈናቃዮች ቁጥር ከ27 ሺሕ የደረሰው እስከ ሐሙስ ምሽት የተመዘገበ ሲሆን ሌሎችም በእግራቸው በጉዞ ላይ ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ እያቀኑ መሆኑን በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪዎቹ ጠቁመዋል። በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪዎቹ መንግሥት በአስቸኳይ ለተፈናቃዮች ምግብ እንዲያቀርብ ቢጠይቁም የተሰጣቸው ምላሽ ከሚመለከተው አካል ትዕዛዝ አልተላለፈም የሚል መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪ ወጣቶቹ ወደ ቡለን ከተማ ሸሽተው የገቡ ዜጎችን የምግብ አቅርቦት ከማስተባበር በተጨማሪ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን አስከሬን ለማንሳትና የቀብር ስነ ስርዓት ለማከናወን ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መለሰ በየነ ችግሩን በአስቸኳይ ለመፍታት በዞኑ ያለው የጽጥታ ችግር እና የመንገድ መዘጋጋት እንቅፋት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ኃላፊው አክለውም በዞኑ ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ለተፈናቃዮች የሚደርሰው ሰብዓዊ ድጋፍ በጸጥታ ኃይሎች አጀብ ያስፈልገዋል ብለዋል። ነገር ግን በዞኑ በሚታየው የጸጥታ ችግር የጸጥታ ኃይሉ ተበታትኖ ስለሚገኝ ችግሩን በአስቸኳይ ለመፍታት ክልሉ ከዞኑ ኮማንድ ፖስት ጋር በጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

ችግሩ የመንገድ መዘጋጋትና የጸጥታ ስጋት መሆኑን የጠቆሙት መለሰ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ እጥት አለመኖሩን ተናግረዋል። የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ችግሩን ለመፍታት ለዞኑ ኮማንድ ፖስት የእጀባ ጥያቄ እንደሚያቀርብም ተመላክቷል።

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ በታጠቁ ኃይሎች ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር አንድ መቶ መድረሱን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል። ኮማንድ ፖስቱ አንድ መቶ ዜጎች በጥቃቱ መሞታቸውን ይግለጽ እንጅ አመነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ ከ አንድ መቶ በላይ ዜጎች ሞተዋል ብሏል።

አዲስ ማለዳ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለመቅበር ከቡለን ከተማ ወደ በኩጅ ቀበሌ ያቀኑ በጎ ፈቃደኞች የማቾች ቁጥር እስከ ታኅሳስ 14/2013 ምሽት ድረስ 167 መድረሱን ገልጸዋል። እንደ በጎ ፈቃደኞቹ ገልጻ 167 ዜጎች ሕይወታቸው አልፎ የተገኙት በመኖሪያ ቤታቸው ከተቃጠሉት ውጭ ነው ተብሏል።
ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው በደረሰው ጥቃት የሰዎች ሞት እና ንብረት መውደም እስካሁን ያለው መረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ትክክለኛውን መረጃ የማጣራቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁሟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com