በደቡብ ኦሞ ዞን የሴቶችን መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ ከፍተኛ የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ

Views: 152

በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ ማህበረሰቦች ዉስጥ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች

እንዲወገዱ እንዲሁም የዞኑን ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ስር ነቀል ለዉጥ ለማምጣት የሚያግዝ

ከፍተኛ የንቅናቄ መድረክ (High Level Advocacy Forum) ቅዳሜ ታህሳስ 17 / 2013  በጂንካ ከተማ

ተካሄዷል፡፡

የኃይለማርያምና ሮማን ፋዉንዴሽን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት፣ ከደቡብ ኦሞ ዞን

አስተዳደርና ከፊንላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀዉ የንቅናቄ መድረክ ከፌደራል እስከ ወረዳ ያሉ ተቋሞች

ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 200 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳትፈዉበታል፡፡ የንቅናቄ መድረኩ ዋና ዓላማ በዞኑ

የልማት መርሃ ግብሮች ሴቶችን እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም በሴቶች እና ህጻናት ላይ

የሚፈጸሙትን አስከፊ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ አመራሩና ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስ

የሚያስችል ንቅናቄን መፍጠር ነዉ፡፡ ባለፉት አስርት አመታት የሴቶችን መሰረታዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች

ለማስከበር በርካታ ስራዎች ቢሰሩም የደቡብ ኦሞ ዞንን ጨምሮ ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በትምህርት፣ በጤና፣

በስርዓተ ምግብ፣ በገቢ እና በመሰረታዊ መብቶች መከበር ዙሪያ እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ያለመቻላቸዉ በመድረኩ

ላይ ተገልጿል፡፡

ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር  እና የኃይለማርያምና ሮማን ፋዉንዴሽን

የባለአደራ ቦርድ ሊቀመንበር በንቅናቄ መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር “በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደማይቻል

ሁሉ በግማሽ ጉልበት፤ ዕውቀት እና ጥረት የሚደረግ እንቅስቃሴ በሀገራችን በሚፈለገው ደረጃ የኢኮኖሚ ውጤት

ስለማያመጣ የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አረጋግጠን፣ ጉልበታችንን አስተባብረን፣ በአመራር

ቁርጠኝነት ተደግፈን ለደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶች እና ህጻናት እንዲሁም ለመላዉ ህብረተሰብ የሚበጅ ለዉጥ ለማምጣት

በጋራ እንስራ” ያሉ ሲሆን ስር ነቀል ለዉጥ ማምጣት የሚቻለዉ ለዘመናት በሴቶች ስብዕና እና መብት ላይ አሉታዊ

ተፅዕኖ የፈጠረዉን የልማዳዊ አስተሳሰቦች የብረት በር በተቀናጀ ትግል በመስበር ነዉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኃይለማርያምና ሮማን ፋዉንዴሽን ከደቡብ ኦሞ ዞን ጋር በመተባበር ያደረገዉ የዳሰሳ ጥናት ዉጤት

የቀረበ ሲሆን በጥናቱ ተለይተዉ የታወቁ ለሴቶች መሰረታዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበር ማነቆ የሆኑ

ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ መፍትሔዎች ላይ ዉይይት ተካሄዷል፡፡ የደቡብ ብሔር ብሔርሰቦች እና ህዝቦች

ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳዉ ኢትዮጵያ በምታደርገዉ የብልጽግና ጉዞ ሴቶች እኩል

ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት የሆኑባቸዉ ችግሮች በጥናት መታወቃቸዉ ወደ መፍትሔ የሚደረገዉ

ጉዞ የመጀመርያ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዉ መላዉ የክልሉ አመራሮች ኃላፊነታቸዉን በብቃት በመወጣት እና

አርአያ በመሆን የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶች ያሉባቸዉን ዘርፈ ብዙና ከባድ ችግሮች ለማቃለል በጋራ እንደሚሰሩ ቃል

ገብተዋል፡፡ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ከበደ ሳህሌ በበኩላቸዉ ዞኑ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት

እና የቱሪዝም መስህብነት በአግባቡ በማልማት ሴቶችና ወንዶች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፍትኃዊ ማህበረሰብ

ለመፍጠር ከኃይለማያም ሮማን ፋዉንዴሽን ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸዉን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com