አሁንም የኮቪድ 19 ጉዳይ ቀልድ አይደለም

Views: 600

ቦታው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ለቀሪው ቤተሰብ ስንል በትክክል ሰፈር እና መንደሩን ከመግለጽ ተቆጥበናል ምክንያቱ ደግሞ ይዘን የቀረብነው ታሪክ በእጅጉ የሚያሳዝን እና የኮቪድ 19 አስከፊውን ገጽታ የሩቅ አገር ታሪክ አለመሆኑን የሚያስጨብጥ ስለሚሆን በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ አይተነው የምናልፈው ሳይን ጉያችን ውስጥ ያለ ያልተዳፈነ ረመጥ እንደሆነም ማሳያ ነው።

ለዚህ ሳምንት ይዘነው የቀረብነው ታሪክ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመ እና በእርግጥም ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ላይ የቁጣ ጅራፉን እንደፈራነው አላሳረፈም፣ የተፈራው የአስከሬን ብዛት አልተቆጠረም፣ ሐበሻን ኮሮና አይደፍረውም እና ሌሎች አዘናጊ እና እውነታውን እንድንክደው የሚያደርጉ ጉዳዮች በስፋት የሚሰሙ ጉዳዮች ናቸው።

ይህንንም ተከትሎ ታዲያ በሕብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋቶች እና ትኩረት አለመስጠቶች በስፋት ሚታዩ ጉዳዮችም ናቸው። ለዚህም ደግሞ ማጠናከሪያ የሚሆነው ከሳምንታት በፊት ጤና ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ይፋ ባደረጉት ጥናት መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያው የኮቪድ 19 ወራት የአፍ እና አፍንቻ መሸፈኛ ጭንብል የሚደርገው ሰው ቁጥር ከ74 በመቶ አሁን ላይ ያለው ወደ 52 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በእርግጥም በሽታውን መልመድ እና በዙሪያችን የሞተም ሆነ የታመመ ካለመኖር ወይም ደግሞ አስደንጋች ቁጥሮች በሚዲያው ይፋ ለመደረጋቸው እና ብዙ ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት የሚቻልበት ነው።

በአዲስ አበባ የተከሰተው ጉዳይ ግን ከዚህ ይለያል። ዓለምን ሁሉ ባጠቃው እና በምድር ላይ ያለው የሰው ልጅ በሙሉ መሸሸጊያ አጥቶ በተቸገረበት ወቅት ከኹለት ወንድ እና ከሦስት ሴት ልጆቻቸው ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ አረጋዊያን ባል እና ሚስት ወቅቱን ሁኔታ እና እርጅናቸውንም ታሳቢ አድርገው ከሰው ርቀው እና ተቆጥበው ይኖሩ ነበር። ይሁን እንጂ በምን እንደገባ ያልታወቀው በከፍተኛ ጥንቃቄ ለሚኖሩት እንኳን ከባድ ችግርን ከማስከተል ያልጎለደው ይኸው አለም አቀፋዊ ወረርሽኝ ይህን ቤተሰብ በምን መንገድ እንደገባ ሳይታወቅ ጎብኝቶታል።

በመጀመሪያዎቹ ኹለት ቀናት ቀድሞም አይናቸው እይታ እምብዛም ሆነው አባት ናቸው ብርድ ብርድ ሚል ስሜት ተሰምቷቸው ቤት ውስጥ ቀድሞውንም የሚውሉትን አባውራ ነበር የያዛቸው። በእርግጥ የመጀመሪያዎቹ ኹለት ቀናት ቤተሰቡ ዘንድ የተለመዱ ለጉንፋን እና መሰል በሽታዎች መድኃኒትነት የሚውሉ ባህላዊ ነገሮችን ነበር ሲደረግላቸው የቆየው። ነገር ግን መሽቶ በነጋ ቁጥር ጭራሹኑ ከመሻሻል ይልቅ የጤናቸው ጉዳይ መባባስ እንጂ መሻሻል ሳያሳይ ይቀራል። ይህን ጊዜ ግን የቤቱ የመጀመሪ ልጅ ጉዳዮን ሕክምና ባለሙያዎች እንዲያውቁት በማድረግ በሔደበት መንገድም አባቱ በኮቪድ 19 መጠቃታቸውን ከሕክማነ ባለሙያዎች መረዳት ተቻለ።

ይህን ጊዜ ታዲያ ቤተሰቡ በታላቅ ድንጋጤ ተመታ አባትም ወደ ለይቶ ማቆያ ሚሊኒየም አዳራሽ ተወሰዱ ቤተሰቡም ለየለት ችንቀት ውስጥ ገባ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በአባት ሕመም የተደናገጠው ቤተሰብ እናትን ለማስተዋል እና በምን የጤና ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አለማረጋገጥ እንኳን ለማስታወስ አልቻለም። እናትም በሕይወት ዘመን የውሃ አጣጫቸው መታመም ድንጋጤ ይዟቸው እንጂ እርሳቸውም ደከመኝ ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። አባታቸውን ወደ ለይቶ ማቆያ የላኩት ልጆች ቅርብ ንክኪ የነበራቸውን እናትን (በእርግጥ በኋላ ላይ ሁሉም የቤተሰብ አባል ምርመራ አድርጓል) ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግ ችሎ ውጤታቸውም እንደ ባለቤታቸው የኮቪድ 19 ቫይረስ እንደተጠቁ የሚያመላክት ነበርና እናትም ባላቸው ወደሚገኙበት የሚሊኒየም አዳራሽ አምርተው ባለቤታቸውን ተቀላቀሉ። ይሁን እንጂ ባል ቆይታ ከሳምንት በላይ መዝለቅ ሳይችል ቀርቶ ይህቺን ምድር ተሰናብተው አሸለቡ።

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት አስከሬኑን ለቤተሰብ አስረክቦ ቤተሰብም አስፈላጊውን ነገር አሟልተው አባታቸውን ቀብር በልጆች ተፈጽሞ ወደ ቤት በሚመለሱበት ወቅት የእናታቸው አስከሬን በደጅ ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአኮቪድ 19 መከላከል ግብረ ኃይል ጋር ታጅቦ መድረሱ ነበር። ሀዘናቸው እንዴት ሊበረታ እና የሐዘንን ጥግ ሊነኩት እንደሚችሉት መገመት የሚቻል አይመስልም። አዲስ ማለዳ ከልጆች ጋር ባደረገችው ቆይታ ጉዳዮ ኹለት ወራትን መሻገሩን ቢነግሩንም ትናንት የተፈጠረ ያህል ነው ሐዘናቸው በርትቶ መታዘብ የቻለችው ።

አሁንም የኮቪድ 19 ጉዳይ ቀልድ አለመሆኑን በየቀኑ የሚረግፈው የሰው ሕይወት በትክክል ማስረጃ ሊሆነን ይገባል። በተለይም ደግሞ የኹለተኛ ዙር ወላፈን በመንደርደር ላይ በመሆኑ እና የመጀመሪያውን ሳንከላከል የኹለተኛውን ለመመከት ምን ያህል ዝግጁ መሆናችን አይታወቅም። ከአሳሳቢነቱ የተነሳም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በግላቸው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ኮቪድን በተመለከተም መልዕክት አስተላልፈዋል።

‹‹የኮቪድ-19 ታማሚዎች ቁጥር በማሻቀብ ላይ ነው። የጽኑ ሕሙማን ክፍል ያለውን ዐቅም ሁሉ አሟጦ እየሠራ ይገኛል። በዚህ ወቅት፣ በፍጹም የጥንቃቄ ርምጃዎችን ቸል ልንል አይገባም። የራሳችንን ሕይወት እንታደግ፣ የሌሎችንም ሕይወት እናትርፍ! የአፍ እና የአፍንጫ ጭንብሎችን በአግባቡ በመጠቀም የጤና ባለሞያዎቻችንን እናግዝ››። የሚል መልእክት ማስተላለፋቸው ችግሩ በምን ያህል ደረጃ እየተወነጨፈ መስፋፋቱን እንደቀጠለ ማሳያም ነው። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው ደግሞ በቅርቡ በአገረ እንግሊዝ የታየው አዲሱ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከቀዳሚው ይልቅ በ70 በመቶ የስርጭት አቅሙ እንደሚበልጥ ይፋ አድርጓል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com