ቸል የተባለው የመተከል ጉዳይ

Views: 216

የንጹሃን ሞት እና መፈናቀል ያላባራበት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ97 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በጫካ እና በመጠለያ ጣቢያ ተደብቀው እና ተጠልለው ይገኛሉ።
ለዚህ ሁሉ የዜጎች ሰቆቃ የመንግሥት ቸልተኝነት እና በፍትህ አደባባይ የሚጠየቅ ባለሥልጣን መጥፋቱ ነው። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የችግሩ ሰለባዎችን እና በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድረጎታል።

በኢትዮጵያ ላለፉት ኹለት ዓመታት ሰላም ከራቃቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን አንዱ ነው። መተከል ከወትሮውም ችግር የማያጣው አካባቢ እንደነበር ይነገርለታል። ታዲያ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሉትን ሆነና ነገሩ እየተባባሰ በየቀኑ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት የሚቀጠፍበት ቦታ መሆን ከጀመረ ሰነባበ።

መተከል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥር የሚተዳደር ዞን ይሁን እንጂ፤ በዞኑ ጉምዝ ውጪ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሺናሻና አገው ብሔሮች ተሰባጥረው የሚኖሩበት አካባቢ እንደሆነ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ችግር የማያጣው አካባቢ እነዲሆን አድርጎታል።

በዞኑ በየጊዜው ለሚያልፈው የንጹሐን ዜጎች ሕይወት ማቆሚያ አልተገነለትም። ቢሆንም መንግሥት ችግሩን ለማስቆም ቁርጠኛ አይደለም የሚሉ ትችቶች በብዛት ይሰማሉ። ይህንኑ ቸልተኝነት የሚጠናክሩ ሐሳቦች በብዛት ከየአቅጣጫው በመውጣታቸው ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህምድ ከዞኑ ኗሪዎች ጋር ባሳለፍነው ታኅሳስ 13/2013 በመተከል ዞን የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት መክረው ነበር።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተመራው ልዑክ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሃሰን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

በውይይቱ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ የአገር ሽማግሌች ቡድን በማቋቋም ለማስታረቅ ፣የተጎዱ ዜጎችን ለማገዝ እና እሴቶችን ማዳበር፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት በቀጠናው የሕግ የበላይነትን የማስከበሩን ሥራ ማጠናከር፣ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ አማካኝነት ቀርበው በመነጋገር መገፋፋትን ለማስቀረት ችግር ፈቺ ውይይት ማድረግና በክልሉ የልማት ሥራዎችን ማጠናከር የሚሉትን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቅጣጫ የሰጡባቸው ጉዳዮች ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው ወደ አዲስ አባባ ከተመለሱ በሰዓታት ልዩነት፤ በዞኑ ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ ከ100 በላይ ንጹሐን ዜጎች መገደላቸው ተሰማ። በወቅቱ መንግሥት በቦታው ላይ የሞቱትን ዜጎች ቁጥር 100 ነው መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ከቀናት በኋላ ግን የሟቾች ቁጥር ከ200 በላይ መሆኑ ተሰማ። የሟቾች የቀብር ሁኔታ ግን በእስካባተር በጅምላ መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል።
በብዙዎች ዘንድ መንግሥት የመተከልን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ አይደለም የሚለውን ትችል የሚጠናክር በሚመስል መልኩ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከኗሪዎች ጋር በተወያዩበት ማግሥት የብዙዎች ሕይወት ማለፍ መንግሥትን ትልቅ ነጥብ ያስጣለ ነበር። በድርጊቱ እንደ መግለጫ ካወጡት ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢዜማ ባወጣው መግለጫ ክስተቱ የመንግሥትን ቸልተኝነት አጉልቶ የሚሳይ መሆኑ ይገልጻል።

ቁርጠኝነት የጎደለው የመንግሥት እርምጃ
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግፍና ጭፍጫፋ ማስቆሙ ቀርቶ ከዕለት ዕለት ችግሩ እየተባባሰ መሆኑን እንደ ምክንያት በማንሳት በበርካቶች ዘንድ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ቁርጠኛ እንዳልሆነ ይነገራል።

አዲስ ማለዳ በመተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ችግሮች ሲከሰቱ የችግሩ ሰለባና ሌሎች ምንጮችን በመጠቀም በምታገኛቸው መረጃዎች የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኝነት እንደሌለው በርካታ ማሳያዎችን በማንሳት አስረድተዋል።

በዞኑ በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ችግሮች ሰለባ የሆኑ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዜጎች እንደሚሉት ከሆነ የአካባቢው አመራርም ይሁን የክልሉ መንግሥት ለችግሮች እልባት ከመስጠት ይልቅ ተባባሪ ሆነውብናል ይላሉ። እንደ ማሳያነት የሚነሱትም የጸጥታ ስጋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ጥቆማ ሲሰጥ የሚሰማ አካል የለም፣ በዚህም ስጋቱ እየታወቀ ጭምር ችግር ይፈጠራል ሲሉ አብራርተዋል።

በቅርቡ በቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ የተከሰተው የዜጎች ግድያ የዞኑ አመራሮች ቁርጠኝነት ማጣት መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ችግሩ ሊከሰት በዋዜማው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከኗሪዎች ጋር በተወያዩበት ጊዜ የበኩጅ ቀበሌ አስተዳደር በአካባቢው የታጠቁ ኃይሎች መግባታቸውን በመግለጽ የጸጥታ ኃይል ወደ ቦታው እንዲገባላቸው እየተናገሩ የሚሰማቸው ጠፍቶ ክስተቱ ለብዙዎች ሕይወት ማለፍና መፈናቀል ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መለስ በየነ ከዚህ ቀደም የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረው ነበር። ኃላፊው አክለውም ችግሩን ከስሩ ለማስወገድ በታጠቁ ኃይሎች ላይ የመጨረሻ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የክልሉ መንግሥት በዝግጅት ላይ መሆኑን ቢገልጹም የተባለው ነግር ግን አስካሁን አልሆም።

“የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልዊ መንግሥት የዜጎች መሰረታዊ መብት የሆነውን በሕይወት የመቆየት መብት ማስከበር ባለመቻሉ እና ድርጊቱ እየተደጋገመ በመምጣቱ ኢዜማ በኢፌደሪ በሕገ መንግሥት አንቀፅ 51/14፣ እና ይሄን ለማስፈጸም በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሰረት ጉዳዩን በአስቸኳይ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማምጣት እስካሁን የተፈጸሙት አሰቃቂ ወንጀሎችን ማስቆም ያልቻለበትን እውነተኛ መንስኤ የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቁሞ በአፋጣኝ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን እና የፌደራል መንግሥት በሕግ አግባብ ጣልቃ በመግባት የዜጎቹን ሕይወት የመጠበቅ እና ሕግ የማስከበር ሥራውንእንዲወጣ አሳስቦ ነበር።

በተጨማሪ አጥፊዎችን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሥራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮችን ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲል መግለጫ ያወጣው ኢዜማ ክልሉ መንግሥት ለዜጎች የሰላም ከለላ መሆን አለመቻሉን አመላክቷል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በበኩሉ በመተከል የተከሰተው የንጹሐን ዜጎች ግድያ በመንግሥት ጥላ ሥር ባሉ አካላቶች ጭምር የተደገፈ መሆኑን አስታውቋል። የአብን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሐመድ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግሥት የመተከልን ችግር ለማስታገስ የተጓዘበት መንገድ ትክክል ባለመሆኑ መፍትሔ ማምጣት ሳይችል ቀርቷል የሚል ሐሳብ አላቸው።

ላለፉት ስድስት ወራት በመተከል ዞን የማያባራ የዜጎች ሰቆቃ የበረታበት መሆኑን የሚገልጹት ጣሂር በአካባቢው የመዋቅር ችግር እስካሁን ድረስ ሳይፈታ ችግሩ እልባት ሳያገኝ ቆይቷል ብለዋል።

ክልሉ ውስብስብ ችግር ያለበት መሆኑን የሚነሱት ጣሂር የክልሉና የዞኑ አመራሮች የችግሩ ውስብስብነት ይበልጥ እንዲባባስ አድርገዋል ባይ ናቸው። ለዚህም እንደ ማሳያነት የሚያነሱት ሰሞኑን በዞኑ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ከፌደራል እስከ ዞን ድረስ ያሉ አመራሮችን ነው።
የክልሉ መንግሥት የመተከልን ጉዳይ ጉዳዩ አድርጎ አሰራሩን በቁርጠኝነት ከሠራ ችግሩን ማስቆም እንደሚቻል ጣሂር ጠቁመዋል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በተፈጠረው ችግር ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪ ችግሩን ለማስቆም ቁርጠኛ አይደለም በሚል የፌደራል መንግሥቱም ትችትን ሲስተናግድ ሰንብቷል።የፌደራል መንግሥት በዞኑ የሚፈጠረውን ችግር ለመፍታት የቁርጠኝነት ችግር አለበት ብለው የሚተቹ አካላት ከሚነሱት ሐሳብ አንዱ “የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ለምን መተከል ላይ መድገም አቃተው” የሚለው ተጠቃሽ ነው።

የፌደራል መንግሥት ወይም ብልጽግና በራሱ የእርስ በእርስ ሽኩቻ ውስጥ ሆኖ የዜጎችን ድህንነት ለማስጠበቅ ተጨማሪ መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን እንዳልሰራ የሚናገሩት የአብኑ ጣሂር ናቸው።

የኢዜማ የኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዘላለም ወርቃአገኘሁ በበኩላቸው “የመተከል ጉዳይ ከትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ በእጅጉ የቀደመ ችግር ነበር። ችግሩን ለመስወገድ የኃይል ማነስ ሳይሆን የትኩረት ማነስ ነው።” ሲሉ የፌደራል መንግሥቱን ቸልተኝነት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
በዞኑ ለሚፈጠረው ችግር የመጀመሪያ መነሻው የመንግሥት አሰራር መሆኑን የሚገልጹት ዘላለም ኢዜማ በዞኑ ያለውን ችግር ለማወቅ ባደረገው የመረጃ ማጣራት ሥራ የመንግሥት አወቃቀሮች የችግሩ ተሳታፊ ሆነው አግኝተናቸዋል ሲሉ ጠቁመዋል።

መንግሥት መተከልን ችላ ብሎታል ስንል በምክንያት ነው የሚሉት ዘላለም የችግሩን ምንጭ ለይቶ መፍትሔ የሚሰጥ አካል በዞኑ ባደረግነው ማጣራት አረጋግጠን ነው ብለዋል። እንዲሁም እስካሁን በዞኑ ለተፈጠሩት ግድያዎችና እንግልቶች ምክንያት የሆኑ አመራሮች ተፈትሸው ተጠያቂ ማድረግም ሌላኛው መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል።

ተጠያቂነትን መሸሽ
ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት አካላት በችግር ጊዜ ከኃላፊነት የመሸሽና እኔን አይመለከተኝም ሌላ አካል ጠይቁ የሚል ምላሽ ለሚዲያዎች መስጠት የተለመደ ነው። በመተከል ጉዳይ “አያገባኝ” አይነት መልሶችን ለሚዲያዎች የሚሰጡ ከፍተኛ አመራሮች ታይተዋል።አያገባኝም አይነት መልስ ከሰጡ አመራሮች መካከል ቀድሞው የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት መሪ ኮሌኔል አያሌው በየነ አንደኛው ናቸው።

ኮለኔሉ በመተከል ጉዳይ ከአማራ ቲቪ ጋዜጠኛው “የመተከልን እልቂት ለምን ወታደሮቹ ማቆም አልቻሉም?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላቸው። ኮለኔል አያሌው በምላሻቸው “እኔን አይመለከተኝም ሄዳችሁ የመንግሥት አካልን ጠይቁ” ብለው ዝግ ምላሽ በአማራ ቲቪ አየር ላይ ውሏል። የአያገባኝም ምላሹ አንደምታ የመንግሥትን ቸልተኝነት አጉልቶ ያሳየ ነው በማለት ብዙዎች ጉዳዩን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲቀባበሉት ሰንብተዋል።

በሌላ በኩል አዲስ ማለዳ በመተከል የጸጥታ ጉዳይ እና የተፈናቃዮችን ሁኔታ በተመለከተ መረጃ ፍለጋ ወደ ክልሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መለሰ በየነ ስልክ ስትደው “በመተከል ጉዳይ እኔን አትጠይቁኝ አዲስ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ብቻ ነው መረጃ የሚሰጠው” በማለት አጭር ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
የአብኑ ጣሂር የ”አያገባኝም” ጉዳይ ከኃላፊነት መሸሽና ጉዳዩን በመግፋት ሰበብ ተጨማሪ ራስን ከተጠያቂነት ማሸሽ እና ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ያላቸውን ቸልተኝነት ምን ያህል እንደሆነ ያሳይ ነው ብለውታል።ከዚህም አልፎ የገዢው ፓርቲ አመራሮችም እሰጥ አገባ ውሥጥ የከተተ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝና የአማራ ክልል ብልጽግና እሰጥ አገባ
የኹለቱ መንግሥታት ብልጽግና ፓርቲ በመተከል ጉዳይ ከረር ያለ ይዘት ያለው መግለጫ መለዋወጣቸው የሚታወስ ነው። በመተከል ጉዳይ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እና የአማራ ክልል መንግሥት የመግለጫ ልውውጥና እሰጣገባ በዜጎች ላይ ቀድሞ ከነበረው ችግር በላይ ውጥረት እንደፈጠረባቸው አዲስ ማለዳ ከኗሪዎች አረጋግጣ መዘገቧ የሚታወስ ነው።

የኹለቱ ክልል መንግሥታት የመግለጫ ልውውጥ እና እሰጥአገባ ለመተከል ኗሪዎች የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር የአብኑ ጣሂር ተናግረዋል። “የመግለጫ እሰጥአገባ ዛቻ ሕዝብን ከሞት አይታደግም” የሚሉት ጣሂር የኹቱም ክልል መግለጫ ለውውጥ ተገቢ እንዳልሆነ አስታውሰዋል። ችግሮች በሕጋዊ መንገድ በትብብር ሊፈቱ እንደሚገባም ጣሂር ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት የተሳሳተ መግለጫ ከማውጣት ይልቅ ከፌደራል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን መፍትሔ ሊመጡ የሚችሉ ሥራዎች መሥራት አለበት እንደሚገባው ኃላፊው አመላክተዋል። እንዲሁም ክልሉን ማገዝ በሚችለው መንገድ ማገዝ ይሻላል ብለዋል።

የኢዜማው ዘላለም በበኩላቸው የኹለቱ ክልሎች መጎሻሸም በዜጎች ላይ የባሰ ውጥረት ይጨምር እንደሆን እንጂ አማራጭ መፍትሔ ሊሆን አይችልም ብለዋል። በመሆኑም ክልሎቹ መጎሻሸሙን ወደ ጎን ትተው በጋራ መሥራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በመተከል የደረሱ ጉዳቶች
በመተከል ዞን በተፈጸሙት ተደጋጋሚ ግድያዎች እና መፈናቀሎች በመንግሥት በኩል የሚወጡ መረጃዎች ትክክለኛ የሟቾችንና ተጎጂዎችን ቁጥር ለመጥቀስ ብዙም ፈቃደኛ እንዳልነበረ አዲስ ማለዳ መረጃዎችን በምታጣራበት ጊዜ ከክልሉ አመራሮች ምላሽ በተደጋጋሚ አረጋግጣለች። ችግሩን እንደቀላል ጉዳይ አይቶ የማለፉ ነገር በመንግሥት በኩል የተለመዱ ዝንባሌዎች ሆነዋል።

በቅርቡ በተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በመተከል ዞን ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ መካሄዱን እንዳረጋገጠ ታኅሳስ 16/2013 ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ተቋሙ እንዳስታወቀው በመተከል ዞን እየደረሰ ባለው የዜጎች ጭፍጨፋ፣ የንብረት ውድመትና ከቤት መፈናቀል፣ የክልሉ መንግሥትና የጸጥታ መዋቅር ድርጊቱን መከላከልና ማስቆም ለምን እንዳልቻሉ ጥናት አድረጊለሁ ብሏል።

ጉዳዩን የሚመረምረው የጥናትና ቁጥጥር ቡድን ወደ አካባቢው በመላክ ባደረገው ጥናትም በዞኑ ማንዱራ፣ ዳንጉር፣ ጉባ፣ ድባጤ፣ ቡለንና ወንበራ ወረዳዎች ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጿል።

“እስከ ታህሳስ 14/2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ163 በላይ ዜጎች ህይወት ያለፈ መሆኑን እንዲሁም ከ31 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ለመረዳት ተችሏል” ብሏል በመግለጫው። በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት የክልሉ መንግሥት አስተዳደር አካላት፣ የፓርቲ አመራሮችና የጸጥታ መዋቅር አካላት እንደተሳተፉም ተቋሙ ጠቁሟል።
የሰላም ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት ላይ የተጠቀሰው መረጃ እንዲሚያመላክተው ደግሞ በመተከል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ97 ሺህ በላይ መድረሱን ሰላም ሚንስቴር አስታውቋ። እንዲሁም በቅርቡ በኩጅ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ከ170 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል።

እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት የነበራቸው ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ እንደነበር ገልጾ፤ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የኮማንድ ፖስት ከችግሩ ክብደትና ስፋት አንጻር የሠራው የጸጥታ ማስከበር ሥራና በአጥፊዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ደካማ እንደነበር የተቋሙ የጥናትና የቁጥጥር ቡድኑ ለይቷል” ብሏል። ተቋሙ የክልሉ የአስተዳደር አካላትና የጸጥታ መዋቅር በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው እንዳለበት እንደሚያምን ገልጿል።

የአዲሱ ግብረ ኃይል የቤት ሥራ
በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተው የዜጎች ግድያና መፈናቀል እልባት ባለማግኘቱ ዞኑ በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲተዳደር መደረጉ የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት የዞኑን ኮማንድ ፖስት የሚመራ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ በሥራ ላይ እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም ኮማንድ ፖስቱ ችግሮችን ማስቆም እንዳልተቻለ በብዙዎች ዘንድ ትችት ቀርቦበታል። ኮማንድ ፖስት ዞኑን በሚመራበት ጊዜም ከአካባቢው ኗሪዎች በተጨማሪ ሰላም ለማስከበር በተሰማሩ የጸጥታ አካላት ላይ ጭምር ግድያ መፈጸሙን አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጣ ዘግባ ነበር።

የበርካቶች ሕይወት በጥፋቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በዞኑ የተቋቋመውን ኮማንድፖስት የሚመራ አዲስ ግብረ ኃይል አቋቋሙ። አዲሱ ግብረ ኃይል የመተከልን ጉዳይ በበላይነት እንደሚመራ የክልሉ መንግሥት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መለስ በየነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ከአዲሱ ግብረ ኃይል ውጪ በመተከል ጉዳይ ሌላ አካል ምንም ማለት እንደማይችል ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ሥራ መረከቡን ሌፍተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመውና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች የተካተቱበት ግብረ ኃይል በዞኑ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ጀምሯል ተብሏል።

ሌፍተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ “በመተከል ዞን የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተልዕኮ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል” ብለዋል።
እንደ መፍትሔ የዞኑን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩን መንስኤ መለየት ተገቢ ነው የሚሉት የአብኑ ጣሂር የክልሉን አወቃቀር መፈተሽ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል። በዞኑ ከስር ከመሰረቱ የችግሮቹ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን በትኩረት የመለየት ሥራ ለችግሩ የመፍትሔ አካል መሆኑንም ጣሂር ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዞኑ የተለየ ፍላጎት ያለው አካል ማነው? የሚለውን ጉዳይ ማጥናት አስፈላጊ ነጥብ መሆኑን ጣሂር አክለዋል። ይህ መደረግ ያለበት ቦታው በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉልና በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ስለሚገኝ ነው ብለዋል። በዞኑ ውስጥ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የሱዳን ድንበርን ጥሶ መግባት የክልሉን ችግር የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ያስፈልጋል ሲሉም ጣሂር ጠቁመዋል።

አዲሱ ግብረ ኃይል የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮ ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተጨባጭ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባው የሚጠቁሙት ደግሞ የኢዜማው ዘላለም ናቸው። ዘላለም አንደሚሉት ከሆነ ችግሩን ከስር ከመሰረቱ ለመፍታት የክልሉን የጸጥታ መዋቅር በጥልቀት ገምግሞ ማሻሻል ቀዳሚ ሥራ መሆን አለበት ሲሉ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ችግሮችን ለመፍታት በተናጠል የሚመጣ መፍትሔ አመርቂ ሊሆን ስለማይችል የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ተናብበው መሥራት እንዳባቸው ዘላለም አመላክተዋል።ተጠያቂነትንም ለማረጋገጥ እየተሄደበት ያለው ርቀት ብዙ ቢቀረውም መልካም ጅማሮ ነው ማለት ይገባል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ታኅሳስ 21/2013 ባካሄደው አምስተኛ ዓመት ስድስተኛ የሥራ ዘመን ስድስተኛ አስቸኳይ ጉባዔ የአራት የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።በምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሱትም አድጎ አምሳያ፣ ሽፈራው ጨሊቦ፣ ግርማ መኒና አረጋ ባልቢድ ናቸው።

በተፈፀመው ጭፍጨፋ አመራር የተሳተፈበት መሆኑን የጠቆሙት የምክር ቤቱ አባላት፣ ዞኑን ከመረጋጋት አልፎ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ በድርጊቱ በተሳተፉ አካላት ላይ የተጀመረው የህግ የበላይነት የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።ይህም ቀጣዩ የአዲሱ ግብረ ኃይል የቤት ሥራ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com