“የማስረጃ ሕግ መዘጋጀት በፍትሕ አስተዳደር ላይ ያለውን ክፍተት ይሸፍናል” ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር)

Views: 60

የኢፌዴሪ ረቂቅ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት መሻሻሉ እና ከዚህ ቀደም ያልነበረው የማስረጃ ሕግ መውጣቱ በተጠርጠጣሪዎች ላይ የሚደርሰውን የህግ ጥሰት ይቀንስላል ሲሉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽር ዳንኤል በቀለ ዶክተር ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

ከዚህ ቀደም የማስረጃ ህግ ባለመኖሩ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ ይህ የማስረጃ ሕግ መዘጋጀቱ እንደ አንድ ጥሩ እርምጃ ነው ብለዋል።

የፍትህ አስተዳደርን ፍትሀዊ ለማድረግ ፣ እውነትን ከማውጣት አንፃር ፣ የታሳሪዎችን መብቶች ከመጠበቅ ፣ ፍትህን ከማስፈን እና የፍትህ አስተዳደርን ቀልጣፋ ለማድረግ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት ላይ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀፆች በውስጡ እንዳሉ ስለታመነበት ማሻሻያ እየተዘጋጀለት መሆኑ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሰብአዊ ጥሰት እንዳይኖር ያደርጋል ብለዋል።

ነገር ግን የተሻሻለው ረቂቅ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት ከሰብአዊ መብት አንፃር በደንብ ተፈትሾ ክፍተቶች ስለተገኙበት ረቂቁ ላይ ያለው ክፍት ተለይቶ እንዲሻሻል ለምክር ቤት እና ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አክለው ተናግረዋል።

በሕግ ሂደት ውስጥ ብዙ መጉላላቶች እንዳሉና የማስረጃ ህግ አለመኖሩ የተጠርጣሪዎችን መብት ለማስከበር ኣዳጋች ሁኔታዎች ነበሩ አሁን ላይ ግን እነዚህ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት መሻሻል እንዲሁም የማስረጃ ሕግ መኖሩ ይበል የሚያስብል ጥሩ ለውጥ ነው ብለዋል።

ይህ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት እና የማስረጃ ሕግ ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ተሻሽለው ወደ ስራ ሲገባ የሚቀይራቸው ነገሮች በርካታ ናቸው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ጠበቃ እና ወንጀል ፍትህ አስተዳደር አባል እንዲሁም ረቂቁን በማዘጋጀት ላይ የተሳተፉ ያለለት ተሾመ እንደተናገሩት ይህ ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱ እና ማሻሻያ መደረጉ አግባብነት አለው ብለዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቂ መመሪያ ላይ መካተት የሚገባቸው ግን ሳያካትታቸው የቀሩ ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል።
እንደ ጠበቃው ገለፃ በፊት ከነበረው የሥነ ስርዓት ሕግ አሁን እየተዘጋጀ ያለው ረቂቅ የተጠርጣሪውን መብት ከማስከበር አንፃር ከፍተኛ መሻሻል እንዳለው አስረድተዋል።

በዋናነት አሁን እየወጣ ያለው ረቂቅ ሕግ ላይ መሻሻል ካለባቸው ነጥቦች መካከል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ሲይዝ ያለመናገር መብት እንዳለው እና በጠበቃ የመወከል መብት እንዳለው ማስረዳት እንዳለበት መካተት አለበት ብለዋል።

ፖሊስ የሚፈልገውን መረጃ ለማግኘት የሚያደርጋቸው ተደጋጋሚ መጠየቅ ፣ በሌሊት ከእንቅልፍ እየቀሰቀሱ መጠየቅ እንዲሁም ምግብ እና ውሀ በመከልከል መረጃውን የሚያገኝበት መንገድ በግልፅ መገደብ አለበት ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አንድ ተጠርጣሪ ናሙና መሰጠት አልፈልግም ካለ ወንጀሉን አንደፈፀመ ይቆጠራል የሚል ረቂቁ ላይ እንደተካተተ እና ይህም የተጠርጣሪውን በነፃ የመገመት መብቱን የሚጎዳ ስለሆነ መሻሻል እንዳለበት ተናግረዋል።

የማስረጃ ሕግ በፊት በአገራች የለም ነበር ያሉት ጠበቃው ይህ የማስረጃ ሕግ መምጣቱ የተከሳሽን መብት ከመጠበቅ አንፃር ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ፅሕፈት ቤት ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያ ኪነጥበብ አረጋ እንደተናገሩት ይህ ረቂቂ መመሪያ በርካታ ነገሮች ላይ ማሻሻያ እንዳደረገ እና የወንጅል ሥነ ስርዓት ህጉ አላማ ምንእንደሆነ ለይቶ በተለይም ፍትሀዊነትን ማረጋገጥን እንደ መርህ እንደስቀመጠ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ተናግረዋል።

በተለይም የማስረጃ ሕግ በአገራችን ያልነበረ ሲሆን መዘጋጀቱም በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ መብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ያስቀራል ብለዋል።
በተለይም ሰው በኃይል በማስገደድ የሚመጣን ማስረጃ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያሳያል ያሉት ባለሙያው በዚህም ሰውን በማሰቃየት በመደብደብ እንዲያምን ማድረግ ይቀራል በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ ረቂቅ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት መሻሻያም ሆነ የማስረጃ ሕግ መውጣቱ በተጠርጠጣሪዎች ላይ የነበረን እንግልት ፣ የፍትህ አካላት ተጠርጣሪን ወንጀሉን እንዲያምን ሳይሆን እውነቱ እንዲታወቅ ማድረግን ጨምሮ በሕግ አካላት ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከላከላል ሲሉ ኮሚሽር ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com