ንብረት የወደመባቸው የሻሸመኔ ነዋሪዎች የግብር እፎይታ አልተሰጠንም አሉ

Views: 204

በሻሸመኔ ከተማ በተፈጠሩ ግጭቶች አማካኝነት ንብረቶቻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ነጋዴዎች የግብር እፎይታ ይሰጣቸዋል ተብለው ቃል የተገባላቸው ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን ግብር ካልከፈላችሁ ንግድ ፍቃድ ማደስም ሆነ ‹‹ክሊራንስ›› መውሰድ አትችሉም እየተባሉ እንደሆነ ሻሸመኔ የሚገኙ ጉዳት የደረሰባቸው ነጋዴዎች ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

እንደ ነጋዴዎቹ ገለፃ ሰኔ 23/ 2012 የታዋቂው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተነሱ ግጭቶች ለረጅም አመታት ያፈሯቸው ንብረቶቻቸው ላይ በማቃጠል እና በመሰባበር ሻሸመኔ ከተማ ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የግብር እፎይታ ይሰጣቸዋል ተብሎ እንደነበርና አሁን ግን ግብር ካልከፈላችሁ የንግድ ፍቃዳችሁን ማደስም ሆነ ክሊራንስ መውሰድ አትችሉም እየተባሉ እንዳሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ለአዲስ ማለዳ ጉዳያቸውን ያጋሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሻሻመኔ ነዋሪ እንደተናገሩት በደረሰው ውድመት ለ20 አመታት ያህል ያፈሩትን 80 ሚሊየን ገደማ የሚገመት ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ እንደተቃጠለባቸው ተናግረዋል።

በዚህም መንግስት በተለያየ ጊዜ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የግብር እፎይታ መስጠትን ጨምሮ ሌሎች ብድርን የምናገኝበት ሁኔታ እንደሚመቻችልን ካሳ እንደሚሰጠን ሲነገር የነበረ ቢሆንም አንዱም ነገር አልተደረገልንም ብለዋል።

እንደ ነጋዴው ገለፃ ንብረቶቻችን ወድመው ጠግነን ወደ ስራ ለመመለስ ባልቻልንበት ሁኔታ ግብር ክፈሉ መባሉ በሻሸመኔ ያሉ ንብረት የወደመባቸውን ሰዎች ችግር ውስጥ ከቷል ያሉ ሲሆን ፤ እንደውም አንዳንድ ነጋዴዎች ገንዘብ ስለሌላቸው ማደሱን ትተው ቁጭ እንዳሉ ተናግረዋል።

የሻሸመኔን ገቢዎች ቢሮ ስንጠይቅ ከፖሊስ ማስረጃ ካመጣችሁ መውሰድ ትችላላችሁ እንደሚሉና ነገር ግን ከፖሊስ ማስረጃውን አውጥተን ስንሄድ ሙሉውን ባይሆን የተወሰነ መክፈል አለባችሁ እየተባልን ነው ብለዋል።

ሌላኛዋ ንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነጋዴ እንደተናገሩት ታህሳስ 30 ድረስ ንግድ ፈቃድ ማደስ እንዳለባቸው እና ንግድ ፈቃድ ለማደስ ደግሞ ያለፈው አመት ከከፈሉት ግብር የግዴታ የተወሰነ መክፈል እንዳለባቸው እንደተነገራቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለአብነትም በባለፈው አመት 20 ሺሕ ብር ግብር እንደከፈሉ የተናገሩት ነጋዴዋ አሁን ደግሞ አምስት ሺሕ ብር ክፈሉ እንደተባሉ ተናግረዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ንብረቶቻቸው ለወደሙባቸው የግብር እፎይታ ይሰጣቸዋል ተብሎ እንደነበር ነገር ግን አሁን ላይ ሻሸመኔ ያለ ንብረት ወድሞበት የነበረ ነጋዴ ንግድ ፈቃዱን ለማደስ ሲሄድ ክፍያ እየተጠየቀ መሆኑን አስረድተዋል።

በአገራችን ላይ ሰርተን መለወጥ ያልቻልንበት ሁኔታ ነው ያለው በዚህም በጣም እናዝናለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሻሸመኔ ከተማ ገቢዎች ኃላፊ ከድር ገመቹ እንደተናገሩት ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች ከፖሊስ ንብረታቸው እንደወደመባቸው ማረጋገጫ ካመጡ ክሊራንስ እየሰጡ እንዳሉ ተናግረዋል። በዚህም የሚቀርበው ቅሬታ አግባብነት የሌለው እንደሆነ እና ከፖሊስ ንብረታቸው እንደወደመባቸው ማረጋገጫ ላመጡ ሰዎች ግብር ሳይጠየቁ ክሊራንስ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በዚህ ሁኔታ ማረጋገጫው ኖሮት ክሊራንስ ያልተሰጠው ካለ መጠየቅ ይችላል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ኃላፊው አክለውም ውድመት ደርሶብኛል ብሎ ከፖሊስ ማደስረጃ የሌለው ሰው ግን ማረጋገጫ ስለሌለው ውድመት እንደደረሰበት መለየት ስለማይቻል እንደማያስተናግዱም አስረድተዋል።

መቃጠሉን ከፖሊስ ማረጋገጫ ይዘው ገቢዎች ቢሮ ሰጥተው ክሊራንስ እንዲወስዱ እያደረጉ እንዳሉ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ከግብር ነፃ ይሁን አይሁን የሚለውን የሚወስነው መንግስት እንደሆነና ገና መረጃን አሰባስቦ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እንደሚገመት ነገር ግን የክሊራንስ መስጫ ጊዜው የሚያበቃው ታህሳስ 30 ስለሆነ ጉዳት ለደረሰባቸው ክሊራንስ መሰጠት እንዳለበት እና እየተሰጠም እንዳለ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com